አንደኛ ነገሥት 20:1-43

  • ሶርያውያን በአክዓብ ላይ ጦርነት አወጁ (1-12)

  • አክዓብ ሶርያውያንን ድል አደረገ (13-34)

  • ስለ አክዓብ የተነገረ ትንቢት (35-43)

20  በዚህ ጊዜ የሶርያ+ ንጉሥ ቤንሃዳድ+ ጦር ሠራዊቱን በሙሉ አሰባሰበ፤ በተጨማሪም ሌሎች 32 ነገሥታትን ከነፈረሶቻቸውና ከነሠረገሎቻቸው አሰባሰበ፤ ወጥቶም ሰማርያን+ በመክበብ+ ውጊያ ከፈተባት።  ከዚያም በከተማዋ ውስጥ ወደሚገኘው ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ+ መልእክተኞች ልኮ እንዲህ አለው፦ “ቤንሃዳድ እንዲህ ይላል፦  ‘ብርህና ወርቅህ እንዲሁም ከሚስቶችህና ከልጆችህ መካከል ምርጥ የሆኑት የእኔ ናቸው።’”  በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ አንተ እንዳልከው እኔም ሆንኩ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነን” ሲል መለሰለት።+  በኋላም መልእክተኞቹ ተመልሰው በመምጣት እንዲህ አሉት፦ “ቤንሃዳድ እንዲህ ይላል፦ ‘እንዲህ የሚል መልእክት ልኬብህ ነበር፦ “ብርህን፣ ወርቅህን፣ ሚስቶችህንና ልጆችህን ትሰጠኛለህ።”  ሆኖም ነገ በዚህ ሰዓት ገደማ አገልጋዮቼን ወደ አንተ እልካለሁ፤ እነሱም የአንተን ቤትና የአገልጋዮችህን ቤት አንድ በአንድ ይበረብራሉ፤ ለአንተ ትልቅ ዋጋ ያለውን ነገር ሁሉ እጃቸው በማስገባት ይወስዳሉ።’”  በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ በምድሪቱ ያሉትን ሽማግሌዎች በሙሉ ጠርቶ “እንግዲህ ይህ ሰው በእኛ ላይ መከራ ለማምጣት ቆርጦ እንደተነሳ ልብ በሉ፤ ሚስቶቼን፣ ልጆቼን፣ ብሬንና ወርቄን እንድሰጠው ላከብኝ፤ እኔም አልከለከልኩትም” አላቸው።  ከዚያም ሽማግሌዎቹ ሁሉና ሕዝቡ በሙሉ “እሺ አትበለው፤ በዚህ አትስማማ” አሉት።  በመሆኑም የቤንሃዳድን መልእክተኞች “ጌታዬ ንጉሡን እንዲህ በሉት፦ ‘እኔ አገልጋይህ መጀመሪያ ላይ የጠየቅከኝን ነገር ሁሉ እፈጽማለሁ፤ ይህን ግን መፈጸም አልችልም’” አላቸው። መልእክተኞቹም ይህን መልእክት ይዘው ወደ እሱ ሄዱ። 10  ቤንሃዳድም “የሰማርያ አፈር ለሚከተለኝ ሕዝብ ሁሉ አንድ አንድ እፍኝ እንኳ ቢደርሰው አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የከፋም ያምጡብኝ!” የሚል መልእክት ላከበት። 11  የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ “ቤንሃዳድን እንዲህ በሉት፦ ‘ለጦርነት እየታጠቀ ያለ ሰው ጦርነቱን ድል አድርጎ ትጥቁን እንደሚፈታ ሰው መደንፋት የለበትም’” አለ።+ 12  ቤንሃዳድና ነገሥታቱ በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው እየጠጡ ሳለ ቤንሃዳድ ይህን ምላሽ ሲሰማ አገልጋዮቹን “ጥቃት ለመሰንዘር ተዘጋጁ!” አላቸው። በመሆኑም በከተማዋ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ተዘጋጁ። 13  ሆኖም አንድ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ+ ቀርቦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ይህን እጅግ ብዙ ሕዝብ ትመለከታለህ? እኔ ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃለህ’” አለው።+ 14  አክዓብም “በማን አማካኝነት?” ሲል ጠየቀ፤ እሱም መልሶ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በአውራጃዎቹ መኳንንት አገልጋዮች አማካኝነት’” አለው። ስለሆነም አክዓብ “ታዲያ ውጊያውን የሚያስጀምረው ማን ነው?” አለ፤ እሱም “አንተ ነህ!” አለው። 15  ከዚያም አክዓብ የአውራጃዎቹን መኳንንት አገልጋዮች ቆጠረ፤ እነሱም 232 ነበሩ፤ በመቀጠልም የእስራኤልን ወንዶች በሙሉ ቆጠረ፤ እነሱም 7,000 ነበሩ። 16  እነሱም እኩለ ቀን ላይ ቤንሃዳድ ረዳቶቹ ከሆኑት 32 ነገሥታት ጋር በድንኳኖቹ ውስጥ ሆኖ ሰክሮ ሳለ ወደዚያ ሄዱ። 17  የአውራጃዎቹ መኳንንት አገልጋዮች ቀድመው በወጡ ጊዜ ቤንሃዳድ ወዲያውኑ መልእክተኞችን ላከ። እነሱም “ከሰማርያ የመጡ ሰዎች አሉ” ብለው ነገሩት። 18  በዚህ ጊዜ ቤንሃዳድ “ሰዎቹ የመጡት ለሰላም ከሆነ በሕይወት እንዳሉ ያዟቸው፤ የመጡት ለጦርነት ከሆነም በሕይወት እንዳሉ ያዟቸው” አለ። 19  ሆኖም እነዚህ ማለትም የአውራጃዎቹ መኳንንት አገልጋዮችና እነሱን ይከተላቸው የነበረው ሠራዊት ከከተማዋ ሲወጡ 20  እያንዳንዳቸው ሊገጥማቸው የመጣውን ሰው ገደሉ። ከዚያም ሶርያውያን ሸሹ፤+ እስራኤላውያንም አሳደዷቸው፤ የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ ግን በፈረስ ላይ ሆኖ ከተወሰኑ ፈረሰኞች ጋር አመለጠ። 21  ሆኖም የእስራኤል ንጉሥ ወጥቶ ፈረሶቹንና ሠረገሎቹን መታ፤ በሶርያውያንም ላይ ታላቅ ድል ተቀዳጀ።* 22  በኋላም ነቢዩ+ ወደ እስራኤል ንጉሥ ቀርቦ “የሶርያ ንጉሥ በሚቀጥለው ዓመት መባቻ* ላይ ስለሚመጣብህ+ ሄደህ ራስህን አጠናክር፤ ምን ማድረግ እንደምትችልም አስብ”+ አለው። 23  በዚህ ጊዜ የሶርያን ንጉሥ አገልጋዮቹ እንዲህ አሉት፦ “አምላካቸው የተራሮች አምላክ ነው። በእኛ ላይ ያየሉብንም ለዚህ ነው። ሆኖም ሜዳ ላይ ብንገጥማቸው እናሸንፋቸዋለን። 24  በተጨማሪም እንዲህ አድርግ፦ ነገሥታቱን በሙሉ ከቦታቸው አንስተህ+ በምትካቸው አስተዳዳሪዎች አስቀምጥ። 25  ከዚያም ከተደመሰሰብህ ሠራዊት ጋር የሚመጣጠን ሠራዊት ሰብስብ፤* በፈረሱ ፋንታ ፈረስ፣ በሠረገላውም ፋንታ ሠረገላ ተካ። ከዚያም ሜዳ ላይ እንግጠማቸው፤ ያለምንም ጥርጥር እናሸንፋቸዋለን።” ንጉሡም የሰጡትን ምክር ሰማ፤ እንዳሉትም አደረገ። 26  በዓመቱ መባቻ* ላይም ቤንሃዳድ ሶርያውያንን አሰባስቦ ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ወደ አፌቅ+ ወጣ። 27  የእስራኤል ሰዎችም ከተሰባሰቡና ስንቅ ከተሰጣቸው በኋላ እነሱን ለመግጠም ወጡ። የእስራኤል ሰዎች ፊት ለፊታቸው ሰፍረው ሲታዩ ሁለት ትናንሽ የፍየል መንጋ ይመስሉ ነበር፤ ሶርያውያኑ ግን መላውን ምድር አጥለቅልቀውት ነበር።+ 28  ከዚያም የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደ እስራኤል ንጉሥ ቀርቦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሶርያውያን “ይሖዋ የተራሮች አምላክ እንጂ የሜዳ አምላክ አይደለም” ስላሉ ይህን እጅግ ብዙ ሕዝብ በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤+ እናንተም እኔ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ታውቃላችሁ’”+ አለው። 29  እነሱም ለሰባት ቀን ያህል እንደተፋጠጡ ቆዩ። በሰባተኛውም ቀን ውጊያው ተጀመረ። የእስራኤል ሰዎችም በአንድ ቀን 100,000 ሶርያውያን እግረኛ ወታደሮችን ገደሉ። 30  የተረፉትም ወደ ከተማዋ ወደ አፌቅ+ ሸሹ። ሆኖም ከተረፉት ሰዎች መካከል በ27,000ዎቹ ላይ ቅጥሩ ተንዶ ወደቀባቸው። ቤንሃዳድም ሸሽቶ ወደ ከተማዋ ገባ፤ አንድ ክፍል ውስጥ ገብቶም ተሸሸገ። 31  በመሆኑም አገልጋዮቹ እንዲህ አሉት፦ “የእስራኤል ቤት ነገሥታት መሐሪዎች እንደሆኑ* ሰምተናል። እንግዲህ ወገባችንን በማቅ ታጥቀንና ራሳችን ላይ ገመድ አስረን ወደ እስራኤል ንጉሥ እንውጣ። ምናልባት ሕይወትህን* ያተርፍልህ ይሆናል።”+ 32  ስለሆነም ወገባቸውን በማቅ ታጥቀውና ራሳቸው ላይ ገመድ አስረው ወደ እስራኤል ንጉሥ በመምጣት “አገልጋይህ ቤንሃዳድ ‘እባክህ፣ ሕይወቴን* አታጥፋ’ ይላል” አሉት። ንጉሡም “እስካሁን በሕይወት አለ? ወንድሜ እኮ ነው” አለ። 33  ሰዎቹ ይህን እንደ ጥሩ ገድ በመመልከትና ንጉሡ የተናገረውን በማመን “አዎ፣ ቤንሃዳድ እኮ ወንድምህ ነው” አሉ። ንጉሡም “በሉ ሄዳችሁ አምጡት” አለ። ከዚያም ቤንሃዳድ ወደ እሱ መጣ፤ እሱም ወዲያውኑ ሠረገላው ላይ እንዲወጣ አደረገው። 34  ቤንሃዳድም “አባቴ ከአባትህ ላይ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልሳለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገው ሁሉ አንተም በደማስቆ ለራስህ ገበያ ማቋቋም* ትችላለህ” አለው። አክዓብም “በዚህ ስምምነት* መሠረት አሰናብትሃለሁ” አለው። በዚህም መሠረት ከእሱ ጋር ስምምነት አድርጎ አሰናበተው። 35  ከነቢያት ልጆች*+ አንዱ በይሖዋ ቃል ታዞ ጓደኛውን “እባክህ ምታኝ” አለው። ሰውየው ግን ሊመታው ፈቃደኛ አልሆነም። 36  ስለዚህ “የይሖዋን ቃል ስላልሰማህ ከእኔ ተለይተህ እንደሄድክ አንበሳ አግኝቶ ይገድልሃል” አለው። ከእሱ ተለይቶም ሲሄድ አንበሳ አግኝቶ ገደለው። 37  ከዚያም ሌላ ሰው አግኝቶ “እባክህ ምታኝ” አለው። በመሆኑም ሰውየው መትቶ አቆሰለው። 38  ከዚያም ይህ ነቢይ ሄዶ ንጉሡን መንገድ ዳር ቆሞ ጠበቀው፤ ማንነቱም እንዳይታወቅ ዓይኖቹን በመጠምጠሚያ ሸፍኖ ነበር። 39  ንጉሡም በዚያ ሲያልፍ ነቢዩ ጮክ ብሎ ንጉሡን በመጣራት እንዲህ አለ፦ “እኔ አገልጋይህ ወደተፋፋመው ጦርነት ገብቼ ነበር፤ በዚህ ጊዜ አንድ ሰው ከዚያ ወጥቶ የሆነ ሰው ወደ እኔ ይዞ መጣ፤ እንዲህም አለኝ፦ ‘ይህን ሰው ጠብቀው። ይህ ሰው ቢጠፋ በእሱ ሕይወት ፋንታ የአንተ ሕይወት ይተካል፤*+ ወይም ደግሞ አንድ ታላንት* ብር ትከፍላለህ።’ 40  ታዲያ እኔ አገልጋይህ ሥራ በዝቶብኝ ወዲያ ወዲህ ስል ሰውየው ድንገት አምልጦ ሄደ።” የእስራኤልም ንጉሥ “እንግዲህ በራስህ ላይ ፈርደሃል፤ አንተው ራስህ ውሳኔውን አስተላልፈሃል” አለው። 41  ከዚያም ፈጠን ብሎ መጠምጠሚያውን ከዓይኖቹ ላይ አነሳ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ይህ ሰው ከነቢያት አንዱ+ መሆኑን አወቀ። 42  ነቢዩም “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እኔ መጥፋት አለበት ያልኩት ሰው ከእጅህ እንዲያመልጥ ስላደረግክ+ በእሱ ሕይወት ፋንታ የአንተ ሕይወት ይተካል፤*+ በእሱም ሕዝብ ፋንታ የአንተ ሕዝብ ይተካል’”+ አለው። 43  በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ፊቱ ጠቁሮና አዝኖ ወደ ቤቱ ወደ ሰማርያ+ ሄደ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ሶርያውያንንም ክፉኛ ጨፈጨፋቸው።”
ቀጣዩን የበልግ ወቅት ያመለክታል።
ቃል በቃል “ቁጠር።”
የበልግን ወቅት ያመለክታል።
ወይም “ታማኝ ፍቅር እንደሚያሳዩ።”
ወይም “ነፍስህን።”
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “ጎዳና መሰየም።”
ወይም “ቃል ኪዳን።”
“የነቢያት ልጆች” የሚለው አገላለጽ ነቢያት ትምህርት የሚቀስሙበትን ትምህርት ቤት ወይም የነቢያትን ማኅበር የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
ወይም “በእሱ ነፍስ ፋንታ የአንተ ነፍስ ትተካለች።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በእሱ ነፍስ ፋንታ የአንተ ነፍስ ትተካለች።”