አንደኛ ነገሥት 5:1-18

  • ንጉሥ ኪራም የግንባታ ቁሳቁሶችን ለሰለሞን ላከ (1-12)

  • ሰለሞን የግዳጅ ሥራ የሚሠሩ ሰዎችን መለመለ (13-18)

5  የጢሮስ+ ንጉሥ ኪራም ሰለሞን በአባቱ ምትክ ንጉሥ ሆኖ እንደተቀባ ሲሰማ አገልጋዮቹን ወደ እሱ ላከ፤ ምክንያቱም ኪራም ምንጊዜም የዳዊት ወዳጅ ነበር።*+  ሰለሞንም በምላሹ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ኪራም+ ላከ፦  “አባቴ ዳዊት ከተለያየ አቅጣጫ ጦርነት ይከፈትበት ስለነበር ይሖዋ ጠላቶቹን ከእግሩ በታች እስኪያደርግለት ድረስ ለአምላኩ ለይሖዋ ስም የሚሆን ቤት መሥራት እንዳልቻለ በሚገባ ታውቃለህ።+  አሁን ግን አምላኬ ይሖዋ በዙሪያዬ ካሉ ጠላቶቼ ሁሉ እረፍት ሰጥቶኛል።+ የሚቃወመኝም ሆነ እየተፈጸመ ያለ ምንም መጥፎ ነገር የለም።+  በመሆኑም ይሖዋ ለአባቴ ለዳዊት ‘ለስሜ ቤት የሚሠራልኝ በአንተ ምትክ በዙፋንህ ላይ የማስቀምጠው ልጅህ ነው’ ሲል በገባው ቃል መሠረት ለአምላኬ ለይሖዋ ስም ቤት ለመሥራት አስቤአለሁ።+  ስለሆነም አገልጋዮችህ አርዘ ሊባኖስ+ እንዲቆርጡልኝ ትእዛዝ ስጥ። አገልጋዮቼም ከአገልጋዮችህ ጋር ይሠራሉ፤ የአገልጋዮችህንም ደሞዝ አንተ በወሰንከው መሠረት እከፍላለሁ፤ መቼም ከመካከላችን እንደ ሲዶናውያን ዛፍ መቁረጥ የሚችል አንድም ሰው እንደሌለ ታውቃለህ።”+  ኪራም የሰለሞንን መልእክት ሲሰማ እጅግ በመደሰቱ “ይህን ታላቅ* ሕዝብ እንዲመራ ለዳዊት ጥበበኛ ልጅ ስለሰጠው ዛሬ ይሖዋ ይወደስ!” አለ።+  ስለዚህ ኪራም እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ሰለሞን ላከ፦ “የላክብኝ መልእክት ደርሶኛል። የአርዘ ሊባኖስና የጥድ ሳንቃዎች በማቅረብ ረገድ የፈለግከውን ሁሉ አደርጋለሁ።+  አገልጋዮቼ ሳንቃዎቹን ከሊባኖስ ወደ ባሕሩ ያወርዷቸዋል፤ እኔም በባሕር ላይ ተንሳፈው አንተ ወደምትለኝ ቦታ እንዲደርሱ አንድ ላይ አስሬ እልካቸዋለሁ። እዚያም ሲደርሱ እንዲፈቱ አደርጋለሁ፤ ከዚያ ልትወስዳቸው ትችላለህ። አንተ ደግሞ በምላሹ የጠየቅኩህን ቀለብ ለቤተሰቤ ታቀርባለህ።”+ 10  በመሆኑም ኪራም፣ ሰለሞን የፈለገውን ያህል የአርዘ ሊባኖስና የጥድ ሳንቃ አቀረበለት። 11  ሰለሞን ደግሞ ለኪራም ቤተሰብ ቀለብ እንዲሆን 20,000 የቆሮስ መስፈሪያ* ስንዴና 20 የቆሮስ መስፈሪያ ምርጥ የወይራ ዘይት* ለኪራም ሰጠው። ሰለሞን ለኪራም በየዓመቱ ይህን ይሰጠው ነበር።+ 12  ይሖዋም ቃል በገባለት መሠረት ለሰለሞን ጥበብ ሰጠው።+ በኪራምና በሰለሞን መካከል ሰላም ነበር፤ እንዲሁም የስምምነት ውል ተዋዋሉ።* 13  ሰለሞንም ከመላው እስራኤል የግዳጅ ሥራ የሚሠሩ ሰዎችን መለመለ፤ የተመለመሉትም ሰዎች ብዛታቸው 30,000 ነበር።+ 14  እነሱንም በየወሩ አሥር አሥር ሺህ እያደረገ በየተራ ወደ ሊባኖስ ይልካቸው ነበር። እነሱም ለአንድ ወር በሊባኖስ፣ ለሁለት ወር ደግሞ ቤታቸው ይቀመጡ ነበር፤ የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ የተመለመሉት ሰዎች አለቃ አዶኒራም+ ነበር። 15  ሰለሞን በተራሮቹ ላይ 70,000 ተራ የጉልበት ሠራተኞችና* 80,000 ድንጋይ ጠራቢዎች+ ነበሩት፤+ 16  በተጨማሪም ከሰለሞን መኳንንት መካከል አስተዳዳሪዎች+ ሆነው የሚያገለግሉት 3,300 ሰዎች ሠራተኞቹን ይቆጣጠሩ ነበር። 17  የቤቱን መሠረት በተጠረቡ ድንጋዮች ለመጣል+ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ውድ የሆኑ ትላልቅ ድንጋዮችን+ ፈልፍለው አወጡ።+ 18  ስለዚህ የሰለሞን ግንበኞች፣ የኪራም ግንበኞችና ጌባላውያን+ ድንጋዮቹን ጠረቡ፤ እንዲሁም ቤቱን ለመገንባት የሚያስፈልጉትን ሳንቃዎችና ድንጋዮች አዘጋጁ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ዳዊትን ይወደው ነበር።”
ወይም “ብዙ።”
ቃል በቃል “የተጨቀጨቀ ዘይት።”
አንድ ቆሮስ 220 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቃል ኪዳን ተጋቡ።”
ወይም “ተሸካሚዎችና።”