አንደኛ ዜና መዋዕል 10:1-14

  • ሳኦልና ሦስት ወንዶች ልጆቹ ሞቱ (1-14)

10  ፍልስጤማውያንም ከእስራኤል ጋር እየተዋጉ ነበር። የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጤማውያን ፊት ሸሹ፤ ብዙዎቹም በጊልቦአ ተራራ ላይ ተገደሉ።+ 2  ፍልስጤማውያን ሳኦልንና ወንዶች ልጆቹን እግር በእግር ተከታተሏቸው፤ ፍልስጤማውያንም የሳኦልን ወንዶች ልጆች ዮናታንን፣ አቢናዳብንና ሜልኪሳን+ መተው ገደሏቸው። 3  ውጊያው በሳኦል ላይ በረታ፤ ቀስተኞቹም አገኙት፤ ደግሞም አቆሰሉት።+ 4  ከዚያም ሳኦል ጋሻ ጃግሬውን “እነዚህ ያልተገረዙ ሰዎች መጥተው በጭካኔ እንዳያሠቃዩኝ*+ ሰይፍህን መዘህ ውጋኝ” አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ስለነበር ፈቃደኛ አልሆነም። በመሆኑም ሳኦል ሰይፉን ወስዶ በላዩ ላይ ወድቆ ሞተ።+ 5  ጋሻ ጃግሬው ሳኦል መሞቱን ሲያይ እሱም በራሱ ሰይፍ ላይ ወድቆ ሞተ። 6  ስለዚህ ሳኦልም ሆነ ሦስት ወንዶች ልጆቹ ሞቱ፤ የቤቱም ሰዎች ሁሉ አብረው ሞቱ።+ 7  በሸለቆው ውስጥ የነበሩት* የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ሠራዊቱ መሸሹን እንዲሁም ሳኦልና ልጆቹ መሞታቸውን ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ጥለው ሸሹ፤ ከዚያም ፍልስጤማውያን መጥተው ከተሞቹን ያዙ። 8  በማግስቱ ፍልስጤማውያን የሞቱትን ሰዎች ልብስና ትጥቅ ለመግፈፍ ሲመጡ ሳኦልንና ወንዶች ልጆቹን በጊልቦአ ተራራ ላይ ወድቀው አገኟቸው።+ 9  ስለሆነም ሳኦልን ገፈፉት፤ ራሱን ከቆረጡና የጦር ትጥቁን ከወሰዱ በኋላ ወሬው ለጣዖቶቻቸውና+ ለሕዝቡ እንዲዳረስ ወደ ፍልስጤም ምድር ሁሉ መልእክት ላኩ። 10  ከዚያም የጦር ትጥቁን በአምላካቸው ቤት* አስቀመጡት፤ ራሱን ደግሞ በዳጎን ቤት+ ላይ ቸነከሩት። 11  በጊልያድ በምትገኘው በኢያቢስ+ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ፍልስጤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን ሁሉ ሲሰሙ+ 12  ተዋጊዎቹ ሁሉ ተነሱ፤ የሳኦልንና የልጆቹንም አስከሬን ተሸክመው ወደ ኢያቢስ አመጡ። ከዚያም አፅማቸውን በኢያቢስ በሚገኝ ትልቅ ዛፍ ሥር ቀበሩ፤+ ለሰባት ቀንም ጾሙ። 13  ስለዚህ ሳኦል ለይሖዋ ታማኝ ሳይሆን በመቅረቱ ሞተ፤ ምክንያቱም የይሖዋን ቃል አልታዘዘም፤+ ደግሞም መናፍስት ጠሪን አማከረ፤+ 14  ይሖዋንም አልጠየቀም። ስለሆነም ለሞት አሳልፎ ሰጠው፤ ንግሥናውም ለእሴይ ልጅ ለዳዊት እንዲተላለፍ አደረገ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “እንዳያንገላቱኝ።”
ወይም “በረባዳማው ሜዳ የነበሩት።”
ወይም “ቤተ መቅደስ።”