አንደኛ ዜና መዋዕል 14:1-17
14 የጢሮስ ንጉሥ ኪራም+ ለዳዊት ቤት* እንዲሠሩለት መልእክተኞችን እንዲሁም የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎችን፣ ድንጋይ ጠራቢዎችንና* አናጺዎችን ላከ።+
2 ዳዊትም ይሖዋ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው አወቀ፤+ ምክንያቱም አምላክ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤል ሲል ንግሥናውን ከፍ ከፍ አድርጎለት ነበር።+
3 ዳዊት በኢየሩሳሌም ተጨማሪ ሚስቶች አገባ፤+ ደግሞም ተጨማሪ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ።+
4 በኢየሩሳሌም ሳለ የተወለዱለት ልጆች ስም ይህ ነው፦+ ሻሙአ፣ ሾባብ፣ ናታን፣+ ሰለሞን፣+
5 ይብሃር፣ ኤሊሹዓ፣ ኤልፔሌት፣
6 ኖጋ፣ ኔፌግ፣ ያፊአ፣
7 ኤሊሻማ፣ ቤኤልያዳ እና ኤሊፌሌት።
8 ፍልስጤማውያንም በሙሉ ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን+ ሲሰሙ እሱን ፍለጋ ወጡ።+ ዳዊትም ይህን በሰማ ጊዜ ሊገጥማቸው ወጣ።
9 ከዚያም ፍልስጤማውያን መጥተው በረፋይም ሸለቆ* ወረራ አካሄዱ።+
10 ዳዊትም “ወጥቼ ፍልስጤማውያንን ልግጠም? በእጄ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህ?” ሲል አምላክን ጠየቀ። ይሖዋም “አዎ ውጣ፤ እኔም በእርግጥ በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ” አለው።+
11 በመሆኑም ዳዊት ወደ በዓልጰራጺም+ ወጥቶ በዚያ መታቸው። ከዚያም ዳዊት “እውነተኛው አምላክ፣ ውኃ እንደጣሰው ግድብ ጠላቶቼን በእጄ ደረማመሳቸው” አለ። ከዚህም የተነሳ ያን ቦታ በዓልጰራጺም* ብለው ጠሩት።
12 ፍልስጤማውያንም አማልክታቸውን በዚያ ጥለው ሸሹ፤ ዳዊት በሰጠው መመሪያ መሠረትም በእሳት አቃጠሏቸው።+
13 ከጊዜ በኋላ ፍልስጤማውያን ሸለቆውን* እንደገና ወረሩ።+
14 ዳዊት ዳግመኛ አምላክን ጠየቀ፤ ሆኖም እውነተኛው አምላክ እንዲህ አለው፦ “እነሱን ለመግጠም በቀጥታ አትውጣ። ይልቁንም ከኋላቸው ዙርና በባካ* ቁጥቋጦዎቹ ፊት መጥተህ ግጠማቸው።+
15 ደግሞም በባካ ቁጥቋጦዎቹ አናት ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማ ጥቃት ሰንዝር፤ ምክንያቱም ይህ በሚሆንበት ጊዜ እውነተኛው አምላክ የፍልስጤማውያንን ሠራዊት ለመምታት በፊትህ ወጥቷል ማለት ነው።”+
16 ስለዚህ ዳዊት ልክ እውነተኛው አምላክ እንዳዘዘው አደረገ፤+ የፍልስጤማውያንንም ሠራዊት ከገባኦን አንስቶ እስከ ጌዜር+ ድረስ መቷቸው።
17 የዳዊትም ዝና በአገሩ ሁሉ ተሰማ፤ ይሖዋም ብሔራት ሁሉ እንዲፈሩት አደረገ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ቤተ መንግሥት።”
^ ወይም “ቅጥር የሚሠሩ ግንበኞችንና።”
^ ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
^ “በመደረማመስ የተዋጣለት” የሚል ትርጉም አለው።
^ ወይም “ረባዳማውን ሜዳ።”
^ “ባካ” የሚለው ስም የዕብራይስጥ ቃል ነው። የተክሉ ዓይነት በትክክል አይታወቅም።