አንደኛ ዜና መዋዕል 5:1-26

  • የሮቤል ዘሮች (1-10)

  • የጋድ ዘሮች (11-17)

  • አጋራውያን ድል ተመቱ (18-22)

  • የምናሴ ነገድ እኩሌታ (23-26)

5  የእስራኤል የበኩር ልጅ የሆነው የሮቤል+ ወንዶች ልጆች እነዚህ ናቸው። እሱ በኩር ቢሆንም እንኳ የአባቱን መኝታ ስላረከሰ+ የብኩርና መብቱ ለእስራኤል ልጅ ለዮሴፍ+ ወንዶች ልጆች ተሰጠ፤ ከዚህም የተነሳ በትውልድ ሐረግ መዝገቡ ላይ የብኩርና መብት እንዳለው ተደርጎ አልተመዘገበም።  ይሁዳ+ ከወንድሞቹ የሚበልጥ ከመሆኑም ሌላ መሪ+ የሚሆነው የተገኘው ከእሱ ነው፤ ሆኖም የብኩርና መብቱን ያገኘው ዮሴፍ ነበር።  የእስራኤል የበኩር ልጅ የሮቤል ወንዶች ልጆች ሃኖክ፣ ፓሉ፣ ኤስሮን እና ካርሚ+ ነበሩ።  ሸማያህ የኢዩኤል ልጅ ነበር፤ የሸማያህ ልጅ ጎግ፣ የጎግ ልጅ ሺምአይ፣  የሺምአይ ልጅ ሚክያስ፣ የሚክያስ ልጅ ረአያህ፣ የረአያህ ልጅ ባአል፣  የባአል ልጅ ቤኤራህ ነበር፤ የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር+ የሮቤላውያን አለቃ የሆነውን ቤኤራህን በግዞት ወሰደው።  ወንድሞቹ በየቤተሰቦቻቸውና በየዘር ሐረጋቸው ሲዘረዘሩ እንደሚከተለው ነው፦ መሪ የሆነው የኢዔል፣ ዘካርያስ፣  የኢዩኤል ልጅ፣ የሼማ ልጅ፣ የአዛዝ ልጅ ቤላ፤ እሱ ከአሮዔር+ አንስቶ እስከ ነቦ እንዲሁም እስከ በዓልመዖን+ ድረስ ይኖር ነበር።  መንጎቻቸው በጊልያድ ምድር+ እጅግ በዝተው ስለነበር በስተ ምሥራቅ በኤፍራጥስ ወንዝ+ በኩል እስካለው፣ ምድረ በዳው እስከሚጀምርበት ቦታ ድረስ ሰፈረ። 10  በሳኦል ዘመን በአጋራውያን ላይ ጦርነት ከፍተው ድል መቷቸው፤ በመሆኑም ከጊልያድ በስተ ምሥራቅ ባለው ክልል ሁሉ በድንኳኖቻቸው ውስጥ ኖሩ። 11  ከእነሱ ጋር የሚዋሰኑት የጋድ ዘሮች ደግሞ ከባሳን አንስቶ እስከ ሳልካ+ ባለው ምድር ላይ ኖሩ። 12  ኢዩኤል መሪ ነበር፤ ሁለተኛው ሻፋም ሲሆን ያናይ እና ሻፋጥ ደግሞ በባሳን መሪዎች ነበሩ። 13  ከአባቶቻቸው ቤት የሆኑት ወንድሞቻቸውም ሚካኤል፣ መሹላም፣ ሳባ፣ ዮራይ፣ ያካን፣ ዚአ እና ኤቤር ሲሆኑ በአጠቃላይ ሰባት ነበሩ። 14  እነዚህ የቡዝ ልጅ፣ የያህዶ ልጅ፣ የየሺሻይ ልጅ፣ የሚካኤል ልጅ፣ የጊልያድ ልጅ፣ የያሮሃ ልጅ፣ የሁሪ ልጅ፣ የአቢሃይል ወንዶች ልጆች ነበሩ። 15  የአባቶቻቸው ቤት መሪ የጉኒ ልጅ፣ የአብዲዔል ልጅ አሂ ነበር። 16  እነሱም በጊልያድ፣+ በባሳን፣+ በእነሱ ሥር* ባሉት ከተሞች እንዲሁም በሳሮን የግጦሽ መሬቶች ሁሉ እስከ ዳርቻዎቻቸው ድረስ ተቀመጡ። 17  እነዚህ ሁሉ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮዓታም+ እና በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም*+ ዘመን በትውልድ መዝገቡ ላይ ሰፈሩ። 18  ሮቤላውያን፣ ጋዳውያንና የምናሴ ነገድ እኩሌታ 44,760 ኃያላን ተዋጊዎችን ያቀፈ ሠራዊት ነበራቸው፤ እነሱም ጋሻና ሰይፍ የታጠቁ፣ ደጋን ያነገቡና* ለውጊያ የሠለጠኑ ነበሩ። 19  እነዚህ ተዋጊዎች በአጋራውያን፣+ በየጡር፣ በናፊሽ+ እና በኖዳብ ላይ ጦርነት ከፈቱ። 20  በጦርነቱ ወቅት አምላክ እንዲረዳቸው ስለጠየቁ እንዲሁም በእሱ ስለታመኑና+ እሱም ልመናቸውን ስለሰማ ከእነሱ ጋር በሚዋጉበት ጊዜ እርዳታ አገኙ፤ በመሆኑም አጋራውያንና ከእነሱ ጋር የነበሩት ሁሉ እጃቸው ላይ ወደቁ። 21  እነሱም መንጎቻቸውን ይኸውም 50,000 ግመሎች፣ 250,000 በጎችና 2,000 አህዮች እንዲሁም 100,000 ሰዎች* ማረኩ። 22  የተዋጋላቸው እውነተኛው አምላክ ስለነበር+ ተገድለው የወደቁት ብዙ ነበሩ። በግዞት+ እስከተወሰዱበትም ጊዜ ድረስ በእነሱ ቦታ ላይ ኖሩ። 23  የምናሴ ነገድ እኩሌታ+ ዘሮች ከባሳን እስከ በዓልሄርሞን፣ እስከ ሰኒር እንዲሁም እስከ ሄርሞን ተራራ+ ድረስ ባለው ምድር ላይ ኖሩ። ቁጥራቸውም እጅግ ብዙ ነበር። 24  የአባቶቻቸው ቤት መሪዎች እነዚህ ነበሩ፦ ኤፌር፣ ይሽኢ፣ ኤሊዔል፣ አዝርዔል፣ ኤርምያስ፣ ሆዳውያህ እና ያህዲኤል፤ እነዚህ ሰዎች ኃያላን ተዋጊዎችና ስመ ገናና ሲሆኑ የአባቶቻቸው ቤት መሪዎች ነበሩ። 25  ሆኖም ለአባቶቻቸው አምላክ ታማኞች ሳይሆኑ ቀሩ፤ ደግሞም አምላክ ከፊታቸው ካጠፋቸው ከምድሪቱ ሕዝቦች አማልክት ጋር አመነዘሩ።+ 26  በመሆኑም የእስራኤል አምላክ የአሦርን ንጉሥ የፑልን መንፈስ አነሳሳ+ (የአሦርን ንጉሥ የቴልጌልቴልፌልሶርን+ መንፈስ ማለት ነው)፤ እሱም ሮቤላውያንን፣ ጋዳውያንንና የምናሴ ነገድ እኩሌታን በግዞት ወደ ሃላህ፣ ወደ ሃቦር፣ ወደ ሃራ እና ወደ ጎዛን+ ወንዝ ወሰዳቸው፤ እስከ ዛሬም በዚያ ይገኛሉ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ዙሪያ።”
ዳግማዊ ኢዮርብዓምን ያመለክታል።
ቃል በቃል “ደጋን የሚረግጡና።”
ወይም “የሰው ነፍሳት።”