የዮሐንስ የመጀመሪያው ደብዳቤ 3:1-24

  • የአምላክ ልጆች ነን (1-3)

  • የአምላክ ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች (4-12)

    • ኢየሱስ የዲያብሎስን ሥራ ያፈርሳል (8)

  • እርስ በርስ ተዋደዱ (13-18)

  • “አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው” (19-24)

3  የአምላክ ልጆች ተብለን እንድንጠራ+ አብ ምን ያህል ታላቅ ፍቅር እንዳሳየን ተመልከቱ!+ ደግሞም ልጆቹ ነን። ዓለም እኛን የማያውቀን ለዚህ ነው፤+ ምክንያቱም ዓለም እሱን አላወቀውም።+ 2  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እኛ አሁን የአምላክ ልጆች ነን፤+ ሆኖም ወደፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም።+ እሱ በሚገለጥበት ጊዜ እንደ እሱ እንደምንሆን እናውቃለን፤ ምክንያቱም እሱን በእርግጥ እናየዋለን። 3  በእሱ ላይ እንዲህ ያለ ተስፋ ያላቸው ሁሉ እሱ ንጹሕ እንደሆነ እነሱም ራሳቸውን ያነጻሉ።+ 4  በኃጢአት ጎዳና የሚመላለስ ሁሉ ዓመፀኛ ነው፤ ኃጢአትም ዓመፅ ነው። 5  በተጨማሪም እሱ እንዲገለጥ የተደረገው ኃጢአታችንን እንዲያስወግድ መሆኑን ታውቃላችሁ፤+ እሱ ደግሞ ኃጢአት የለበትም። 6  ከእሱ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ የሚኖር ሁሉ በኃጢአት ጎዳና አይመላለስም፤+ በኃጢአት ጎዳና የሚመላለስ ሁሉ እሱን አላየውም ደግሞም አላወቀውም። 7  ልጆቼ ሆይ፣ ማንም አያሳስታችሁ፤ እሱ ጻድቅ እንደሆነ ሁሉ በጽድቅ ጎዳና የሚመላለስ ሰውም ጻድቅ ነው። 8  በኃጢአት ጎዳና የሚመላለስ የዲያብሎስ ወገን ነው፤ ምክንያቱም ዲያብሎስ ከመጀመሪያው አንስቶ* ኃጢአት ሲሠራ ቆይቷል።+ የአምላክ ልጅ የተገለጠው የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ* ነው።+ 9  ከአምላክ የተወለደ ሁሉ በኃጢአት ጎዳና አይመላለስም፤+ የአምላክ ዘር* እንዲህ ባለው ሰው ውስጥ ይኖራልና፤ በኃጢአት ጎዳናም ሊመላለስ አይችልም፤ ይህ ሰው ከአምላክ የተወለደ ነውና።+ 10  የአምላክ ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ በግልጽ ይታወቃሉ፦ በጽድቅ ጎዳና የማይመላለስ ሁሉ የአምላክ ወገን አይደለም፤ ወንድሙን የማይወድም የአምላክ ወገን አይደለም።+ 11  ከመጀመሪያ የሰማችሁት መልእክት እርስ በርሳችን መዋደድ አለብን የሚል ነውና፤+ 12  ከክፉው* ወገን እንደሆነውና ወንድሙን በጭካኔ እንደገደለው እንደ ቃየን መሆን የለብንም።+ ቃየን ወንድሙን በጭካኔ የገደለው በምን ምክንያት ነበር? የእሱ ሥራ ክፉ፣+ የወንድሙ ሥራ ግን ጽድቅ ስለነበረ ነው።+ 13  ወንድሞች፣ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ።+ 14  እኛ ወንድሞችን ስለምንወድ+ ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገርን እናውቃለን።+ ወንድሙን የማይወድ በሞት ውስጥ ይኖራል።+ 15  ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤+ ነፍሰ ገዳይ የሆነ ሁሉ ደግሞ የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ።+ 16  እሱ ሕይወቱን* ለእኛ አሳልፎ ስለሰጠ በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤+ እኛም ሕይወታችንን* ለወንድሞቻችን አሳልፈን የመስጠት ግዴታ አለብን።+ 17  ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ቁሳዊ ንብረት ያለው ሰው ወንድሙ ሲቸገር ተመልክቶ ሳይራራለት ቢቀር ‘የአምላክ ፍቅር በእሱ ውስጥ አለ’ እንዴት ሊባል ይችላል?+ 18  ልጆቼ ሆይ፣ በተግባርና+ በእውነት+ እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።+ 19  ከእውነት ወገን መሆናችንን በዚህ እናውቃለን፤ ልባችንም በፊቱ እንዲረጋጋ* እናደርጋለን፤ 20  ይህን የምናደርገው ልባችን እኛን በሚኮንንበት ነገር ሁሉ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር ያውቃል።+ 21  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ልባችን የማይኮንነን ከሆነ ከአምላክ ጋር በነፃነት መነጋገር እንችላለን፤+ 22  እንዲሁም ትእዛዛቱን ስለምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኙትን ነገሮች ስለምናደርግ የምንጠይቀውን ሁሉ ከእሱ እንቀበላለን።+ 23  በእርግጥም ትእዛዙ ይህ ነው፦ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንድናምንና+ እሱ ባዘዘን መሠረት እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ነው።+ 24  በተጨማሪም ትእዛዛቱን የሚጠብቅ ሰው ከእሱ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ይኖራል፤ እሱም እንዲህ ካለው ሰው ጋር አንድነት ይኖረዋል።+ እሱ ከእኛ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ እንደሚኖር በሰጠን መንፈስ አማካኝነት እናውቃለን።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ለማጥፋት።”
ወይም “ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ።”
ዘር የሚተካን ወይም ፍሬ የሚያፈራን ዘር ያመለክታል።
ሰይጣንን ያመለክታል።
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “ነፍሳችንን።”
ወይም “ሙሉ እምነት እንዲያድርበት።”