ሁለተኛ ሳሙኤል 4:1-12
4 የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ፣*+ አበኔር በኬብሮን መሞቱን+ ሲሰማ ወኔ ከዳው፤* እስራኤላውያንም በሙሉ ተረበሹ።
2 የሳኦል ልጅ የሚመራቸው ወራሪ ቡድኖች አለቃ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ የአንደኛው ስም ባአናህ ሲሆን የሌላኛው ስም ደግሞ ሬካብ ነበር። እነሱም ከቢንያም ነገድ የሆነው የበኤሮታዊው የሪሞን ልጆች ነበሩ። (ምክንያቱም በኤሮት+ ከቢንያም ወገን እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።
3 በኤሮታውያን ወደ ጊታይም+ ሸሹ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ የባዕድ አገር ሰው ሆነው ይኖራሉ።)
4 የሳኦል ልጅ ዮናታን+ እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ ልጅ ነበረው።+ እሱም ስለ ሳኦልና ስለ ዮናታን የሚገልጸው ወሬ ከኢይዝራኤል+ በመጣ ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበር፤ ሞግዚቱም አንስታው መሸሽ ጀመረች፤ ሆኖም በድንጋጤ ሸሽታ ስትሮጥ ከእጇ ላይ ወድቆ ሽባ ሆነ። ስሙም ሜፊቦስቴ+ ነበር።
5 የበኤሮታዊው የሪሞን ልጆች ሬካብ እና ባአናህ ሞቃታማ በሆነው የቀኑ ክፍለ ጊዜ ወደ ኢያቡስቴ ቤት ሄዱ፤ እሱም ቀትር ላይ አረፍ ብሎ ነበር።
6 እነሱም ስንዴ የሚወስዱ ሰዎች መስለው ወደ ቤቱ ውስጥ ዘልቀው ገቡ፤ ኢያቡስቴንም ሆዱ ላይ ወጉት፤ ከዚያም ሬካብ እና ወንድሙ ባአናህ+ ሸሽተው አመለጡ።
7 ወደ ቤት ሲገቡ ኢያቡስቴ መኝታ ቤቱ ውስጥ አልጋው ላይ ጋደም ብሎ ነበር፤ እነሱም መትተው ገደሉት፤ ከዚያም ራሱን ቆርጠው በመውሰድ ወደ አረባ በሚወስደው መንገድ ሌሊቱን ሙሉ ሲጓዙ አደሩ።
8 የኢያቡስቴንም+ ራስ በኬብሮን ወዳለው ወደ ዳዊት አምጥተው ንጉሡን “ሕይወትህን* ሲፈልጋት+ የነበረው የጠላትህ+ የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ራስ ይኸውልህ። ይሖዋ በዛሬው ዕለት ሳኦልንና ዘሮቹን ለጌታዬ ለንጉሡ ተበቀለለት” አሉት።
9 ሆኖም ዳዊት ለበኤሮታዊው ለሪሞን ልጆች ለሬካብ እና ለወንድሙ ለባአናህ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሕይወቴን ከመከራ ሁሉ በታደገልኝ*+ ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣
10 አንድ ሰው ምሥራች ያበሰረኝ መስሎት ‘ሳኦል እኮ ሞተ’+ ብሎ በነገረኝ ጊዜ ጺቅላግ ላይ ገደልኩት።+ መልእክተኛው ከእኔ ያገኘው ሽልማት ይህ ነበር!
11 ታዲያ በገዛ ቤቱ አልጋው ላይ ተኝቶ የነበረውን ጻድቅ ሰው የገደሉ ክፉ ሰዎችማ እንዴት ከዚህ የባሰ ነገር አይጠብቃቸው! እና አሁን ደሙን ከእጃችሁ መጠየቅም+ ሆነ እናንተን ከምድር ገጽ ማጥፋት አይገባኝም?”
12 ከዚያም ዳዊት እንዲገድሏቸው ለወጣቶቹ ትእዛዝ ሰጠ።+ እነሱም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ቆርጠው በኬብሮን በሚገኘው ኩሬ አጠገብ ሰቀሏቸው።+ የኢያቡስቴን ራስ ግን ወስደው በኬብሮን ባለው በአበኔር የመቃብር ቦታ ቀበሩት።