ሁለተኛ ሳሙኤል 7:1-29

  • ዳዊት ቤተ መቅደሱን እንደማይሠራ ተነገረው (1-7)

  • ለዳዊት የመንግሥት ቃል ኪዳን ተገባለት (8-17)

  • ዳዊት ያቀረበው የምስጋና ጸሎት (18-29)

7  ንጉሡ በራሱ ቤት* መኖር በጀመረና+ ይሖዋም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ እረፍት በሰጠው ጊዜ 2  ነቢዩ ናታንን+ “የእውነተኛው አምላክ ታቦት በድንኳን ውስጥ+ ተቀምጦ ሳለ ይኸው እኔ ከአርዘ ሊባኖስ በተሠራ+ ቤት ውስጥ እየኖርኩ ነው” አለው። 3  ናታንም ንጉሡን “ይሖዋ ከአንተ ጋር ስለሆነ ሄደህ በልብህ ያለውን ነገር ሁሉ አድርግ” አለው።+ 4  በዚያው ሌሊት የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ናታን መጣ፦ 5  “ሂድና አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “አንተ የምኖርበትን ቤት መሥራት ይኖርብሃል?+ 6  እስራኤላውያንን ከግብፅ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ ድንኳን እጓዝ ነበር እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርኩም።+ 7  ከእስራኤላውያን* ሁሉ ጋር በተጓዝኩበት ጊዜ በሙሉ ሕዝቤን እስራኤልን እረኛ ሆነው እንዲጠብቁ ከሾምኳቸው የነገድ መሪዎች መካከል ‘በአርዘ ሊባኖስ ቤት ያልሠራህልኝ ለምንድን ነው?’ ያልኩት ማን አለ?”’ 8  አሁንም አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንድትሆን+ መንጋ ከምትጠብቅበት ስፍራ+ ወሰድኩህ። 9  እኔም በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤+ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋለሁ፤+ ስምህንም በምድር ላይ እንዳሉ ታላላቅ ሰዎች ስም ገናና አደርገዋለሁ።+ 10  ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጣቸዋለሁ፤ ተረጋግተው እንዲቀመጡም አደርጋለሁ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ከእንግዲህም የሚረብሻቸው አይኖርም፤ ክፉዎች እንደቀድሞው ዳግመኛ አይጨቁኗቸውም፤+ 11  በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሳፍንትን ከሾምኩበት+ ጊዜ አንስቶ ሲያደርጉ እንደነበሩት አያደርጉባቸውም። እኔም ከጠላቶችህ ሁሉ እረፍት እሰጥሃለሁ።+ “‘“በተጨማሪም ይሖዋ ቤት* እንደሚሠራልህ ይሖዋ ራሱ ነግሮሃል።+ 12  የሕይወት ዘመንህ አብቅቶ+ ከአባቶችህ ጋር በምታንቀላፋበት ጊዜ ከአንተ በኋላ ከአብራክህ የሚወጣውን ዘርህን አስነሳለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ።+ 13  ለስሜ የሚሆን ቤት የሚሠራልኝ እሱ ነው፤+ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ።+ 14  አባት እሆነዋለሁ፤ እሱም ልጄ ይሆናል።+ ጥፋት በሚያጠፋበት ጊዜም በሰዎች በትር፣ በሰው* ልጆች አለንጋ እቀጣዋለሁ።+ 15  ከፊትህ ካስወገድኩት ከሳኦል ላይ ታማኝ ፍቅሬን እንደወሰድኩ+ ከእሱ ላይ አይወሰድም። 16  ቤትህና መንግሥትህ ለዘላለም በፊትህ ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም ለዘላለም የጸና ይሆናል።”’”+ 17  ናታንም ይህን ቃል ሁሉና ይህን ራእይ በሙሉ ለዳዊት ነገረው።+ 18  በዚህ ጊዜ ንጉሥ ዳዊት ገብቶ በይሖዋ ፊት ተቀመጠ፤ እንዲህም አለ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ኧረ ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ? እስከዚህ ድረስ ያደረስከኝስ ቤቴ ምን ስለሆነ ነው?+ 19  ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ይህ ሳያንስ ስለ አገልጋይህ ቤት ገና ወደፊት የሚሆነውንም ነገር ተናገርክ፤ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ይህ ለሰው ዘር ሁሉ የተሰጠ መመሪያ* ነው። 20  ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ታዲያ አገልጋይህ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? አንተ በሚገባ ታውቀኝ የለ?+ 21  ለቃልህ ስትል፣ ከልብህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ* እነዚህን ሁሉ ታላላቅ ነገሮች ፈጽመሃል፤ እንዲሁም ለአገልጋይህ ገልጠህለታል።+ 22  ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ በእርግጥም ታላቅ+ የሆንከው ለዚህ ነው። እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤+ ከአንተ በቀር አምላክ የለም፤+ በጆሯችን የሰማነው ነገር ሁሉ ይህን ያረጋግጣል። 23  በምድር ላይ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ሌላ ብሔር ማን አለ?+ አምላክ ሄዶ ለእነሱ ሲል ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን+ በመፈጸም እንዲሁም ስሙን በማስጠራት+ ሕዝቡ አድርጎ ዋጃቸው።+ ከግብፅ ለዋጀኸው ሕዝብ ስትል ብሔራትንና አማልክታቸውን አባረርክ። 24  ሕዝብህን እስራኤልን እስከ ወዲያኛው የራስህ ሕዝብ አድርገህ አጸናኸው፤+ ይሖዋ ሆይ፣ አንተም አምላኩ ሆንክ።+ 25  “አሁንም ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ አገልጋይህንና ቤቱን በተመለከተ የገባኸውን ቃል እስከ ወዲያኛው ፈጽም፤ ቃል እንደገባኸውም አድርግ።+ 26  ሰዎች ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በእስራኤል ላይ አምላክ ነው’ እንዲሉ ስምህ ለዘላለም ከፍ ከፍ ይበል፤+ የአገልጋይህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሁን።+ 27  የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ‘ለአንተ ቤት* እሠራልሃለሁ’+ በማለት ለአገልጋይህ ራእይ ገልጠህለታል። አገልጋይህ ይህን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ ድፍረት* ያገኘው በዚህ ምክንያት ነው። 28  አሁንም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ እውነተኛው አምላክ አንተ ነህ፤ ቃልህ እውነት ነው፤+ ለአገልጋይህም እነዚህን መልካም ነገሮች ለማድረግ ቃል ገብተህለታል። 29  በመሆኑም የአገልጋይህን ቤት እባክህ ባርክ፤ በፊትህም ለዘላለም የጸና ይሁን፤+ ምክንያቱም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ራስህ ቃል ገብተሃል፤ በአንተም በረከት የአገልጋይህ ቤት ለዘላለም የተባረከ ይሁን።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በቤተ መንግሥቱ።”
ቃል በቃል “ከእስራኤል ወንዶች ልጆች።”
ወይም “ሥርወ መንግሥት።”
“በአዳም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ሕግ።”
ወይም “ከፈቃድህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ።”
ወይም “ሥርወ መንግሥት።”
ቃል በቃል “ልብ።”