ሁለተኛ ሳሙኤል 9:1-13
-
ዳዊት ለሜፊቦስቴ ታማኝ ፍቅር አሳየው (1-13)
9 ከዚያም ዳዊት “ለመሆኑ ለዮናታን ስል ታማኝ ፍቅር ላሳየው የምችል ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው ይኖራል?” አለ።+
2 በዚህ ጊዜ የሳኦል ቤት አገልጋይ የሆነ ሲባ+ የሚባል ሰው ነበር። እሱንም ወደ ዳዊት እንዲመጣ ጠሩት፤ ንጉሡም “ሲባ የምትባለው አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው። እሱም “አዎ፣ እኔ አገልጋይህ ሲባ ነኝ” በማለት መለሰ።
3 ከዚያም ንጉሡ “እንደው የአምላክን ታማኝ ፍቅር ላሳየው የምችል ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው ይኖራል?” አለው። ሲባም ንጉሡን “ሁለቱም እግሮቹ ሽባ+ የሆኑ አንድ የዮናታን ልጅ አለ” አለው።
4 ንጉሡም “ለመሆኑ የት ነው ያለው?” አለው። ሲባም ንጉሡን “ሎደባር ባለው በአሚዔል ልጅ በማኪር+ ቤት ይገኛል” አለው።
5 ንጉሥ ዳዊትም ወዲያውኑ መልእክተኞችን ልኮ ሎደባር ከሚገኘው ከአሚዔል ልጅ ከማኪር ቤት አስመጣው።
6 የሳኦል ልጅ፣ የዮናታን ልጅ ሜፊቦስቴ ወደ ዳዊት ሲገባ ወዲያውኑ በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደ። ከዚያም ዳዊት “ሜፊቦስቴ!” ብሎ ጠራው፤ እሱም “አቤት ጌታዬ” አለ።
7 ዳዊትም “ለአባትህ ለዮናታን ስል ታማኝ ፍቅር ስለማሳይህ አትፍራ፤+ የአያትህን የሳኦልንም መሬት በሙሉ እመልስልሃለሁ፤ አንተም ዘወትር ከማዕዴ ትበላለህ”+ አለው።
8 እሱም ከሰገደ በኋላ “እንደ እኔ ላለ የሞተ ውሻ+ ሞገስ ታሳይ ዘንድ ለመሆኑ እኔ አገልጋይህ ማን ነኝ?” አለው።
9 ከዚያም ንጉሡ ለሳኦል አገልጋይ ለሲባ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ “የሳኦልና የቤተሰቡ የሆነውን ነገር ሁሉ ለጌታህ የልጅ ልጅ ሰጥቼዋለሁ።+
10 አንተ፣ ልጆችህና አገልጋዮችህ መሬቱን ታርሱለታላችሁ፤ ምርቱንም ታስገቡለታላችሁ፤ ይህም ለጌታህ የልጅ ልጅ ቤተሰቦች መብል ይሆናል። የጌታህ የልጅ ልጅ ሜፊቦስቴ ግን ዘወትር ከማዕዴ ይመገባል።”+
ሲባ 15 ልጆችና 20 አገልጋዮች ነበሩት።+
11 ከዚያም ሲባ ንጉሡን “እኔ አገልጋይህ፣ ጌታዬ ንጉሡ ያዘዘኝን ሁሉ እፈጽማለሁ” አለው። ስለዚህ ሜፊቦስቴ ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ከዳዊት* ማዕድ በላ።
12 ሜፊቦስቴም ሚካ+ የሚባል ትንሽ ልጅ ነበረው፤ በሲባ ቤት የሚኖሩም ሁሉ የሜፊቦስቴ አገልጋዮች ሆኑ።
13 ሜፊቦስቴም ዘወትር ከንጉሡ ማዕድ ይበላ+ ስለነበር የሚኖረው በኢየሩሳሌም ነበር፤ ሁለቱም እግሮቹ ሽባ ነበሩ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “ከእኔ” ማለትም ሊሆን ይችላል።