ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 2:1-17
2 እንደገና በምመጣበት ጊዜ ለሐዘን ምክንያት የሚሆን ነገር እንዳይፈጠር ወስኛለሁ።
2 ምክንያቱም የደስታዬ ምንጭ የሆናችሁትን እናንተን ካሳዘንኳችሁ እንግዲህ እኔን ማን ሊያስደስተኝ ነው?
3 ባለፈው ጊዜ የጻፍኩላችሁ በምመጣበት ጊዜ ልደሰትባቸው በሚገባ ሰዎች እንዳላዝን ነው፤ ምክንያቱም የእኔ ደስታ የእናንተ የሁላችሁም ደስታ እንደሚሆን እተማመናለሁ።
4 ልቤ በብዙ መከራና ጭንቀት ተውጦ በብዙ እንባ የጻፍኩላችሁ እንድታዝኑ ሳይሆን+ ለእናንተ ያለኝን ጥልቅ ፍቅር እንድታውቁ ነው።
5 ለሐዘን የሚዳርግ ነገር ያደረገ ማንም ቢኖር+ ያሳዘነው እኔን ሳይሆን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሁላችሁንም ነው፤ እንዲህ ያልኩት ግን ነገሩን ለማክበድ ብዬ አይደለም።
6 እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከእናንተ አብዛኞቻችሁ የሰጣችሁት ተግሣጽ ይበቃዋል፤
7 አሁን ይህ ሰው ከልክ በላይ በሐዘን እንዳይዋጥ+ በደግነት ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባል።+
8 ስለዚህ ለእሱ ያላችሁን ፍቅር እንድታረጋግጡለት አሳስባችኋለሁ።+
9 የጻፍኩላችሁም በሁሉም ነገር ታዛዥ መሆናችሁን ታሳዩ እንደሆነ ለማረጋገጥ ነው።
10 በደሉ ምንም ይሁን ምን እናንተ ይቅር ያላችሁትን ማንኛውንም ሰው እኔም ይቅር እለዋለሁ። እንዲያውም ሁሉንም ነገር በክርስቶስ ፊት ይቅር ያልኩት (ይቅር ያልኩት ነገር ካለ) ለእናንተ ስል ነው፤
11 ይህም ሰይጣን መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ* ነው፤+ እሱ የሚሸርበውን ተንኮል* እናውቃለንና።+
12 ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች ለማወጅ ጥሮአስ+ በደረስኩ ጊዜ የጌታን ሥራ ለማከናወን በር ተከፍቶልኝ ነበር፤
13 ይሁንና ወንድሜን ቲቶን+ ስላላገኘሁት መንፈሴ ተረብሾ ነበር። በመሆኑም በዚያ ያሉትን ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ+ ሄድኩ።
14 በድል ሰልፍ ከክርስቶስ ጋር አብረን እንድንጓዝ በማድረግ ዘወትር ለሚመራንና የእውቀቱ መዓዛ በእኛ አማካኝነት በሁሉም ቦታ እንዲናኝ ለሚያደርገው አምላክ ምስጋና ይድረሰው!
15 እኛ ወደ መዳን በሚወስደው ጎዳና ላይ ባሉት መካከልና ወደ ጥፋት እያመሩ ባሉት መካከል ለአምላክ የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤
16 ወደ ጥፋት እያመሩ ላሉት ለሞት የሚዳርግ የሞት ሽታ፣*+ ወደ መዳን በሚወስደው ጎዳና ላይ ላሉት ደግሞ ወደ ሕይወት የሚመራ የሕይወት መዓዛ ነን። እንዲህ ላለው አገልግሎት ብቃት ያለው ማን ነው?
17 እኛ ነን፤ ምክንያቱም እኛ እንደ ብዙዎቹ ሰዎች የአምላክን ቃል አንሸቃቅጥም፤*+ ከዚህ ይልቅ በአምላክ የተላክን እንደመሆናችን መጠን በቅንነት እንናገራለን፤ ይህን የምናደርገው በአምላክ ፊት ሆነን እንዲሁም ከክርስቶስ ጋር በመተባበር ነው።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “በሰይጣን እንዳንታለል።”
^ ወይም “የእሱን ሐሳብ፤ የእሱን ዕቅድ።”
^ ወይም “መዓዛ።”
^ ወይም “አንነግድም፤ በአምላክ ቃል አናተርፍም።”