ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 6:1-18
6 ደግሞም ከእሱ ጋር አብረን የምንሠራ+ እንደመሆናችን መጠን የአምላክን ጸጋ ከተቀበላችሁ በኋላ ዓላማውን እንዳትስቱ እናሳስባችኋለን።+
2 እሱ “ሞገስ በማሳይበት ጊዜ ሰምቼሃለሁ፤ በመዳንም ቀን ረድቼሃለሁ” ይላልና።+ እነሆ፣ አምላክ ሞገስ የሚያሳይበት ልዩ ጊዜ አሁን ነው። እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው።
3 አገልግሎታችን እንከን እንዳይገኝበት በምንም መንገድ ማሰናከያ እንዲኖር አናደርግም፤+
4 ከዚህ ይልቅ በሁሉም ነገር ራሳችንን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገን እናቀርባለን፤+ ይህን የምናደርገው በብዙ ነገር በመጽናት፣ በመከራ፣ በእጦት፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች፣+
5 በድብደባ፣ በእስር፣+ በሁከት፣ በከባድ ሥራ፣ እንቅልፍ አጥቶ በማደርና ጾም በመዋል ነው።+
6 የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንን በንጽሕና፣ በእውቀት፣ በትዕግሥት፣+ በደግነት፣+ በመንፈስ ቅዱስ፣ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፣+
7 እውነት የሆነውን በመናገርና በአምላክ ኃይል እናሳያለን።+ እንዲሁም በቀኝ እጅና* በግራ እጅ* የጽድቅ መሣሪያዎችን በመያዝ፣+
8 ክብርንም ሆነ ውርደትን እንዲሁም ነቀፋንም ሆነ ምስጋናን በመቀበል የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንን እናስመሠክራለን። እውነተኞች ሆነን ሳለን እንደ አታላዮች ተቆጥረናል፤
9 በሚገባ የታወቅን ሆነን ሳለን እንደማንታወቅ ተቆጥረናል፤ የምንሞት ስንመስል* እነሆ፣ ሕያዋን ነን፤+ ብንቀጣም ለሞት አልተዳረግንም፤+
10 ሐዘንተኞች ተደርገን ብንታይም ምንጊዜም ደስተኞች ነን፤ እንደ ድሆች ብንቆጠርም ብዙዎችን ባለጸጋ እያደረግን ነው፤ ምንም የሌለን ብንመስልም ሁሉ ነገር አለን።+
11 የቆሮንቶስ ወንድሞች ሆይ፣ በግልጽ ነግረናችኋል፤ ልባችንም ወለል ብሎ ተከፍቶላችኋል።
12 እኛ ፍቅራችንን አልነፈግናችሁም፤+ እናንተ ግን ጥልቅ ፍቅራችሁን ነፍጋችሁናል።
13 ስለዚህ ልጆቼን እንደማናግር ሆኜ አናግራችኋለሁ፤ እናንተም በአጸፋው ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱ።+
14 ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ።*+ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ኅብረት አለው?+ ወይስ ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ያገናኘዋል?+
15 በተጨማሪም በክርስቶስና በቤልሆር* መካከል ምን ስምምነት አለ?+ ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ድርሻ አለው?+
16 እንዲሁም የአምላክ ቤተ መቅደስ ከጣዖቶች ጋር ምን ስምምነት አለው?+ እኛ የሕያው አምላክ ቤተ መቅደስ ነንና፤+ አምላክ “በመካከላቸው እኖራለሁ፤+ ከእነሱም ጋር እሄዳለሁ፤ እኔ አምላካቸው እሆናለሁ፣ እነሱ ደግሞ ሕዝቤ ይሆናሉ” ብሎ እንደተናገረው ነው።+
17 “‘ስለዚህ ከመካከላቸው ውጡና ራሳችሁን ለዩ’ ይላል ይሖዋ፤* ‘ርኩስ የሆነውንም ነገር አትንኩ’”፤*+ “‘እኔም እቀበላችኋለሁ።’”+
18 “‘እኔ አባት እሆናችኋለሁ፤+ እናንተ ደግሞ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትሆኑኛላችሁ’+ ይላል ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ።”*
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ጥቃት ለመሰንዘር ሊሆን ይችላል።
^ ለመከላከል ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ሞት ይገባቸዋል ስንባል።”
^ ወይም “አትቆራኙ።”
^ “የማይረባ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ሲሆን ሰይጣንን ያመለክታል።
^ ወይም “መንካት አቁሙ።”