ሁለተኛ ነገሥት 12:1-21
12 ኢዩ+ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ኢዮዓስ+ ነገሠ፤ እሱም በኢየሩሳሌም ሆኖ 40 ዓመት ገዛ። እናቱ ጺብያ የተባለች የቤርሳቤህ ተወላጅ ነበረች።+
2 ኢዮዓስ ካህኑ ዮዳሄ ያስተምረው በነበረበት ዘመን ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።
3 ይሁን እንጂ ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች+ አልተወገዱም፤ ደግሞም ሕዝቡ አሁንም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ ይሠዋ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።
4 ኢዮዓስ ካህናቱን እንዲህ አላቸው፦ “ቅዱስ መባ+ ሆኖ ወደ ይሖዋ ቤት የሚመጣውን ገንዘብ በሙሉ ማለትም እያንዳንዱ ሰው የሚጠበቅበትን ገንዘብ፣+ አንድ ሰው* እንዲከፍል የተተመነበትን ገንዘብና እያንዳንዱ ሰው ልቡ አነሳስቶት ወደ ይሖዋ ቤት የሚያመጣውን ገንዘብ በሙሉ ውሰዱ።+
5 ካህናቱ በግል ቀርበው ገንዘቡን ከለጋሾቻቸው* ላይ መቀበል ይችላሉ፤ ከዚያም በቤቱ ውስጥ የፈረሰውን* ሁሉ ለመጠገን ይጠቀሙበት።”+
6 ንጉሥ ኢዮዓስ በነገሠ በ23ኛው ዓመት ካህናቱ በቤቱ ውስጥ የፈረሰውን ነገር ገና አልጠገኑም ነበር።+
7 በመሆኑም ንጉሥ ኢዮዓስ ካህኑን ዮዳሄንና+ ሌሎቹን ካህናት ጠርቶ “በቤቱ ውስጥ የፈረሰውን ነገር ያልጠገናችሁት ለምንድን ነው? ስለዚህ ገንዘቡ ቤቱን ለማደስ ሥራ ላይ እስካልዋለ ድረስ ከለጋሾች ላይ ከዚህ በላይ ገንዘብ አትቀበሉ” አላቸው።+
8 በዚህ ጊዜ ካህናቱ ከሕዝቡ ላይ ተጨማሪ ገንዘብ ላለመቀበልና ቤቱን የማደሱን ኃላፊነት ላለመውሰድ ተስማሙ።
9 ከዚያም ካህኑ ዮዳሄ አንድ ሣጥን+ ወስዶ መክደኛው ላይ ቀዳዳ አበጀ፤ ሣጥኑንም አንድ ሰው ወደ ይሖዋ ቤት ሲገባ በስተ ቀኝ በኩል በሚያገኘው መሠዊያ አጠገብ አስቀመጠው። በር ጠባቂዎች ሆነው የሚያገለግሉት ካህናት ወደ ይሖዋ ቤት የሚመጣውን ገንዘብ በሙሉ እዚያ ይጨምሩት ነበር።+
10 እነሱም ሣጥኑ ውስጥ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ የንጉሡ ጸሐፊና ሊቀ ካህናቱ መጥተው ይሰበስቡታል፤* ከዚያም ወደ ይሖዋ ቤት የመጣውን ገንዘብ ይቆጥሩታል።+
11 የተቆጠረውን ገንዘብ በይሖዋ ቤት በሚከናወነው ሥራ ላይ ለተሾሙት ሰዎች ይሰጧቸዋል። እነሱ ደግሞ ገንዘቡን በይሖዋ ቤት ለሚሠሩት አናጺዎችና የግንባታ ባለሙያዎች ይከፍሉ ነበር፤+
12 በተጨማሪም ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ይከፍሉ ነበር። ደግሞም በይሖዋ ቤት ውስጥ የፈረሰውን ለመጠገን የሚውሉ ሳንቃዎችንና ጥርብ ድንጋዮችን ለመግዛት እንዲሁም ቤቱን ለመጠገን የሚያስፈልጉትን ሌሎች ወጪዎች ለመሸፈን ያውሉት ነበር።
13 ይሁን እንጂ ወደ ይሖዋ ቤት ከገባው ገንዘብ ውስጥ ለይሖዋ ቤት የሚሆኑ የብር ገንዳዎችን፣ የእሳት ማጥፊያዎችን፣ ጎድጓዳ ሳህኖችን፣ መለከቶችን+ አሊያም ማንኛውንም ዓይነት የወርቅ ወይም የብር ዕቃ ለመሥራት የዋለ ገንዘብ አልነበረም።+
14 ገንዘቡን የሚሰጡት ሥራውን ለሚሠሩት ሰዎች ብቻ ነበር፤ እነሱም በገንዘቡ የይሖዋን ቤት ጠገኑ።
15 ለሠራተኞቹ እንዲከፍሉ ገንዘብ በሚሰጧቸው ሰዎች ላይ ቁጥጥር አያደርጉም ነበር፤ ምክንያቱም ሰዎቹ እምነት የሚጣልባቸው ነበሩ።+
16 ይሁን እንጂ ለበደል መባዎች+ የሚሰጠው ገንዘብና ለኃጢአት መባዎች የሚሰጠው ገንዘብ የካህናቱ ንብረት+ ስለሆነ ወደ ይሖዋ ቤት እንዲገባ አይደረግም ነበር።
17 የሶርያ ንጉሥ ሃዛኤል+ ጌትን+ ለመውጋት የወጣው በዚህ ጊዜ ነበር፤ እሱም በቁጥጥር ሥር አዋላት፤ ከዚያም በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ወሰነ።*+
18 በዚህ ጊዜ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮዓስ የይሁዳ ነገሥታት የነበሩት አባቶቹ ኢዮሳፍጥ፣ ኢዮራምና አካዝያስ የቀደሷቸውን ቅዱስ መባዎች ሁሉ፣ የራሱን ቅዱስ መባዎች እንዲሁም በይሖዋ ቤትና በንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤቶች የተገኘውን ወርቅ ሁሉ ወስዶ ለሶርያ ንጉሥ ለሃዛኤል ላከለት።+ በመሆኑም ሃዛኤል ኢየሩሳሌምን ከመውጋት ተመለሰ።
19 የቀረው የኢዮዓስ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?
20 ይሁንና አገልጋዮቹ በኢዮዓስ ላይ በማሴር+ ወደ ሲላ ቁልቁል በሚወስደው መንገድ ላይ በጉብታው+ ቤት* ገደሉት።
21 ኢዮዓስን መትተው የገደሉት፣ አገልጋዮቹ የነበሩት የሺምዓት ልጅ ዮዛካር እና የሾሜር ልጅ የሆዛባድ ነበሩ።+ እነሱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ በእሱም ምትክ ልጁ አሜስያስ ነገሠ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ነፍስ።”
^ ወይም “ከሚያውቋቸው ሰዎች።”
^ ወይም “ያሉትን ስንጥቆች።”
^ ወይም “ከረጢቶች ውስጥ ይጨምሩታል።” ቃል በቃል “ያስሩታል።”
^ ቃል በቃል “በኢየሩሳሌም ላይ ለመውጣት ፊቱን አቀና።”
^ ወይም “ቤተ መንግሥት።”
^ ወይም “በቤትሚሎ።”