ሁለተኛ ነገሥት 15:1-38

  • አዛርያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ (1-7)

  • መጨረሻ ላይ የነገሡት የእስራኤል ነገሥታት፦ ዘካርያስ (8-12)፣ ሻሉም (13-16)፣ መናሄም (17-22)፣ ፈቃህያህ (23-26)፣ ፋቁሄ (27-31)

  • ኢዮዓታም በይሁዳ ላይ ነገሠ (32-38)

15  የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም* በነገሠ በ27ኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ+ ልጅ አዛርያስ*+ ነገሠ።+  እሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 16 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ52 ዓመት ገዛ። እናቱ ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች።  እሱም አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+  ሆኖም ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች አልተወገዱም ነበር፤+ ሕዝቡ አሁንም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ ይሠዋ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።+  ይሖዋ ንጉሡን ቀሰፈው፤ እስከ ዕለተ ሞቱም ድረስ የሥጋ ደዌ+ በሽተኛ ሆኖ ኖረ፤ በአንድ የተለየ ቤትም ውስጥ ተገልሎ ተቀመጠ፤+ በዚህ ጊዜ የንጉሡ ልጅ ኢዮዓታም+ በቤቱ* ላይ ተሹሞ በምድሪቱ በሚኖረው ሕዝብ ላይ ይፈርድ ነበር።+  የቀረው የአዛርያስ ታሪክ፣+ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?  በመጨረሻም አዛርያስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤+ እነሱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ በእሱም ምትክ ልጁ ኢዮዓታም ነገሠ።  የይሁዳ ንጉሥ አዛርያስ+ በነገሠ በ38ኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ+ በሰማርያ፣ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለስድስት ወርም ገዛ።  አባቶቹ እንዳደረጉት በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሟቸው ካደረጋቸው ኃጢአቶች ዞር አላለም።+ 10  ከዚያም የኢያቢስ ልጅ ሻሉም በእሱ ላይ በማሴር ይብለአም+ ላይ መትቶ ገደለው።+ ከገደለው በኋላ በእሱ ምትክ ነገሠ። 11  የቀረው የዘካርያስ ታሪክ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፏል። 12  ይህም ይሖዋ ለኢዩ “ልጆችህ+ እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ” በማለት የተናገረው ቃል ፍጻሜ ነው።+ የሆነውም ልክ እንደዚሁ ነው። 13  የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያ+ በነገሠ በ39ኛው ዓመት የኢያቢስ ልጅ ሻሉም ነገሠ፤ እሱም በሰማርያ ሆኖ ድፍን አንድ ወር ገዛ። 14  ከዚያም የጋዲ ልጅ መናሄም ከቲርጻ+ ወደ ሰማርያ መጥቶ የኢያቢስን ልጅ ሻሉምን ሰማርያ ላይ መትቶ ገደለው።+ ከገደለውም በኋላ በእሱ ምትክ ነገሠ። 15  የቀረው የሻሉም ታሪክና የጠነሰሰው ሴራ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፏል። 16  በዚያን ጊዜ መናሄም ከቲርጻ ወጥቶ ቲፍሳን እንዲሁም በውስጧና በዙሪያዋ የነበሩትን ሁሉ መታ፤ ይህን ያደረገው በሮቿን ለእሱ ለመክፈት ፈቃደኛ ባለመሆኗ ነው። እሱም ቲፍሳን መታት፤ የነፍሰ ጡሮቿንም ሆድ ቀደደ። 17  የይሁዳ ንጉሥ አዛርያስ በነገሠ በ39ኛው ዓመት የጋዲ ልጅ መናሄም በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያም ሆኖ ለአሥር ዓመት ገዛ። 18  እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። በዘመኑም ሁሉ፣ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሟቸው ካደረጋቸው ኃጢአቶች ዞር አላለም።+ 19  በዚህ ጊዜ የአሦር ንጉሥ ፑል+ ወደ ምድሩ መጣ፤ መናሄምም መንግሥቱን ለማጽናት ድጋፍ እንዲሰጠው ለፑል 1,000 የብር ታላንት* ሰጠው።+ 20  መናሄም ብሩን ያገኘው ከእስራኤላውያን ይኸውም ስመ ጥርና ሀብታም የሆኑ ሰዎች እንዲያዋጡ በማስገደድ ነው።+ በእያንዳንዱ ሰው 50 የብር ሰቅል* አስቦ ለአሦር ንጉሥ ሰጠው። ከዚያም የአሦር ንጉሥ ተመልሶ ሄደ፤ በምድሪቱም አልቆየም። 21  የቀረው የመናሄም+ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 22  በመጨረሻም መናሄም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ፈቃህያህ በእሱ ምትክ ነገሠ። 23  የይሁዳ ንጉሥ አዛርያስ በነገሠ በ50ኛው ዓመት የመናሄም ልጅ ፈቃህያህ በሰማርያ፣ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለሁለት ዓመትም ገዛ። 24  እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሟቸው ካደረጋቸው ኃጢአቶች ዞር አላለም።+ 25  ከዚያም የረማልያህ ልጅ የሆነው የጦር መኮንኑ ፋቁሄ+ ከአርጎብ እና ከአርያ ጋር በማበር በእሱ ላይ አሴረ፤ በሰማርያ፣ በንጉሡ ቤት* በሚገኘው የማይደፈር ማማ ላይ ሳለም መትቶ ገደለው። ከእሱ ጋር 50 የጊልያድ ሰዎች ነበሩ፤ እሱን ከገደለ በኋላም በምትኩ ነገሠ። 26  የቀረው የፈቃህያህ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈዋል። 27  የይሁዳ ንጉሥ አዛርያስ በነገሠ በ52ኛው ዓመት የረማልያህ ልጅ ፋቁሄ+ በሰማርያ፣ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለ20 ዓመትም ገዛ። 28  እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሟቸው ካደረጋቸው ኃጢአቶች ዞር አላለም።+ 29  በእስራኤል ንጉሥ በፋቁሄ ዘመን የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር+ ወረራ በማካሄድ ኢዮንን፣ አቤልቤትማዓካን፣+ ያኖአህን፣ ቃዴሽን፣+ ሃጾርን፣ ጊልያድን+ እንዲሁም ገሊላን ይኸውም መላውን የንፍታሌም+ ምድር ያዘ፤ ነዋሪዎቹንም በግዞት ወደ አሦር ወሰደ።+ 30  በመጨረሻም የኤላህ ልጅ ሆሺአ+ በረማልያህ ልጅ በፋቁሄ ላይ በማሴር መትቶ ገደለው፤ እሱም የዖዝያ ልጅ ኢዮዓታም+ በነገሠ በ20ኛው ዓመት በፋቁሄ ምትክ ነገሠ። 31  የቀረው የፋቁሄ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈዋል። 32  የእስራኤል ንጉሥ የረማልያህ ልጅ ፋቁሄ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያ+ ልጅ ኢዮዓታም+ ነገሠ። 33  እሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ። እናቱም የሩሻ ትባል ነበር፤ እሷም የሳዶቅ ልጅ ነበረች።+ 34  እሱም አባቱ ዖዝያ እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+ 35  ሆኖም ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች አልተወገዱም ነበር፤ ሕዝቡ አሁንም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ ይሠዋ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።+ የይሖዋን ቤት የላይኛውን በር የሠራው እሱ ነበር።+ 36  የቀረው የኢዮዓታም ታሪክና ያደረጋቸው ነገሮች በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 37  በዚያ ዘመን ይሖዋ በይሁዳ ላይ የሶርያን ንጉሥ ረጺንን እና የረማልያህን ልጅ ፋቁሄን+ ላከ።+ 38  በመጨረሻም ኢዮዓታም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማም ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። በእሱም ምትክ ልጁ አካዝ ነገሠ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ዳግማዊ ኢዮርብዓምን የሚያመለክት ነው።
“ይሖዋ ረዳ” የሚል ትርጉም አለው። በ2ነገ 15:13፣ 2ዜና 26:1-23፣ ኢሳ 6:1 እና ዘካ 14:5 ላይ ዖዝያ ተብሎም ተጠርቷል።
ወይም “በቤተ መንግሥቱ።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”