ሁለተኛ ነገሥት 16:1-20

  • አካዝ በይሁዳ ላይ ነገሠ (1-6)

  • አካዝ ለአሦር ንጉሥ ጉቦ ሰጠ (7-9)

  • አካዝ የአረማውያንን መሠዊያ ንድፍ ወሰደ (10-18)

  • አካዝ ሞተ (19, 20)

16  የረማልያህ ልጅ ፋቁሄ በነገሠ በ17ኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮዓታም ልጅ አካዝ+ ነገሠ።  አካዝ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 20 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ። አባቱ ዳዊት እንዳደረገው በአምላኩ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አላደረገም።+  ከዚህ ይልቅ የእስራኤልን ነገሥታት መንገድ ተከተለ፤+ ይሖዋ ከእስራኤላውያን ፊት ያባረራቸው ብሔራት ይፈጽሙ የነበረውን አስጸያፊ ድርጊት በመከተል+ የገዛ ልጁን እንኳ ሳይቀር ለእሳት አሳልፎ ሰጠ።+  ደግሞም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች፣+ በኮረብቶቹና በእያንዳንዱ የለመለመ ዛፍ ሥር+ ይሠዋ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።  የሶርያ ንጉሥ ረጺንና የእስራኤል ንጉሥ የሆነው የረማልያህ ልጅ ፋቁሄ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ የመጡት በዚህ ጊዜ ነበር።+ አካዝንም ከበቡት፤ ሆኖም ከተማዋን መያዝ አልቻሉም።  በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ረጺን አይሁዳውያንን* ከኤላት+ ካባረረ በኋላ ኤላትን ለኤዶም መለሰ። ኤዶማውያንም ወደ ኤላት ገቡ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ ይኖራሉ።  በመሆኑም አካዝ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር+ መልእክተኞች ልኮ “እኔ አገልጋይህና ልጅህ ነኝ። መጥተህ በእኔ ላይ ጥቃት ከሚሰነዝሩት ከሶርያ ንጉሥ እጅና ከእስራኤል ንጉሥ እጅ አድነኝ” አለው።  ከዚያም አካዝ በይሖዋ ቤትና በንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤቶች ያለውን ብርና ወርቅ በመውሰድ ለአሦር ንጉሥ ጉቦ ሰጠ።+  የአሦርም ንጉሥ ልመናውን በመስማት ወደ ደማስቆ ወጥቶ ከተማዋን ያዛት፤ ሕዝቧንም ወደ ቂር በግዞት ወሰደ፤+ ረጺንንም ገደለው።+ 10  ከዚያም ንጉሥ አካዝ የአሦርን ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶርን ለማግኘት ወደ ደማስቆ ሄደ። በደማስቆ የነበረውን መሠዊያ ባየ ጊዜ ንጉሥ አካዝ የመሠዊያውን ንድፍና እንዴት እንደተሠራ የሚያሳይ መግለጫ ለካህኑ ለዑሪያህ ላከለት።+ 11  ካህኑ ዑሪያህ+ ንጉሥ አካዝ ከደማስቆ በላከለት መመሪያ መሠረት መሠዊያውን ሠራ።+ ካህኑ ዑሪያህ ንጉሥ አካዝ ከደማስቆ ከመመለሱ በፊት ሠርቶ አጠናቀቀ። 12  ንጉሡ ከደማስቆ በተመለሰ ጊዜ መሠዊያውን አየው፤ ወደ መሠዊያውም ቀርቦ በላዩ ላይ መባ አቀረበ።+ 13  እንዲሁም በመሠዊያው ላይ የሚቃጠል መባውና የእህል መባው እንዲጨስ አደረገ፤ የመጠጥ መባውንም አፈሰሰ፤ የኅብረት መሥዋዕቶቹንም ደም ረጨ። 14  ከዚያም በይሖዋ ፊት የነበረውን የመዳብ መሠዊያ+ ከቤቱ ፊት ለፊት ከነበረበት ቦታ ይኸውም እሱ ከሠራው መሠዊያና ከይሖዋ ቤት መሃል አንስቶ ከእሱ መሠዊያ በስተ ሰሜን አስቀመጠው። 15  ንጉሥ አካዝም ካህኑን ዑሪያህን+ እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ጠዋት ላይ የሚቀርበውን የሚቃጠል መባ፣ ማታ ላይ የሚቀርበውን የእህል መባ፣+ የንጉሡን የሚቃጠል መባና የእህል መባ እንዲሁም የሕዝቡን ሁሉ የሚቃጠል መባ፣ የእህል መባና የመጠጥ መባ በታላቁ መሠዊያ ላይ አቅርብ።+ በተጨማሪም የሚቃጠለውን መባ ደም ሁሉና የሌሎቹን መሥዋዕቶች ደም ሁሉ በመሠዊያው ላይ እርጭ። የመዳቡን መሠዊያ በተመለከተ ግን ምን እንደማደርግ እወስናለሁ።” 16  ካህኑ ዑሪያህም ንጉሥ አካዝ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።+ 17  በተጨማሪም ንጉሥ አካዝ የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎቹን+ የጎን መከለያዎች ቆራረጠ፤ የውኃ ገንዳዎቹንም ከላያቸው ላይ አነሳ፤+ ባሕሩንም ከተቀመጠበት የመዳብ በሬዎች+ ላይ አውርዶ በድንጋይ ንጣፍ ላይ አስቀመጠው።+ 18  እንዲሁም በይሖዋ ቤት ውስጥ ሠርተውት የነበረውን ለሰንበት ቀን የሚያገለግለውን መጠለያና በውጭ ያለውን የንጉሡን መግቢያ በአሦር ንጉሥ የተነሳ ወደ ሌላ ቦታ ወሰደው። 19  የቀረው የአካዝ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?+ 20  በመጨረሻም አካዝ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ ሕዝቅያስ*+ ነገሠ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የይሁዳን ሰዎች።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
“ይሖዋ ያበረታል” የሚል ትርጉም አለው።