ሁለተኛ ነገሥት 18:1-37

  • ሕዝቅያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ (1-8)

  • የእስራኤል አወዳደቅ (9-12)

  • ሰናክሬም ይሁዳን ወረረ (13-18)

  • ራብሻቁ ይሖዋን ተገዳደረ (19-37)

18  የእስራኤል ንጉሥ የኤላህ ልጅ ሆሺአ+ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ+ ልጅ ሕዝቅያስ+ ነገሠ።  እሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ29 ዓመት ገዛ። እናቱ አቢ* ትባል ነበር፤ እሷም የዘካርያስ ልጅ ነበረች።+  አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ እሱም በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+  ከፍ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎች ያስወገደው፣+ የማምለኪያ ዓምዶቹን ያደቀቀውና+ የማምለኪያ ግንዱን* የቆራረጠው እሱ ነበር። በተጨማሪም ሙሴ ሠርቶት የነበረውን የመዳብ እባብ አደቀቀ፤+ የእስራኤል ሕዝብ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ለእባቡ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበርና፤ ይህም ጣዖት የመዳብ እባብ* ተብሎ ይጠራ ነበር።  እሱም በእስራኤል አምላክ በይሖዋ ታመነ፤+ ከእሱ በኋላም ሆነ ከእሱ በፊት ከተነሱት የይሁዳ ነገሥታት መካከል እንደ እሱ ያለ አልተገኘም።  ከይሖዋ ጋር ተጣበቀ።+ እሱንም ከመከተል ዞር አላለም፤ ይሖዋ ለሙሴ የሰጠውን ትእዛዝ ጠብቆ ኖረ።  ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር። የሚያደርገውንም ነገር ሁሉ በጥበብ ያከናውን ነበር። በኋላም በአሦር ንጉሥ ላይ ዓመፀ፤ እሱንም ለማገልገል ፈቃደኛ አልሆነም።+  በተጨማሪም እስከ ጋዛና እስከ ክልሎቿ ድረስ በመዝለቅ ፍልስጤማውያንን+ ከመጠበቂያ ግንቡ አንስቶ እስከተመሸገው ከተማ* ድረስ ድል አደረገ።  ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ማለትም የእስራኤል ንጉሥ የኤላህ ልጅ ሆሺአ+ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር በሰማርያ ላይ ዘምቶ ከበባት።+ 10  በሦስተኛው ዓመት ማብቂያ ላይ ከተማዋን ያዟት፤+ ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት ይኸውም የእስራኤል ንጉሥ ሆሺአ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ሰማርያ ተያዘች። 11  ከዚያም የአሦር ንጉሥ እስራኤላውያንን ወደ አሦር በግዞት ወስዶ+ በሃላህ፣ በጎዛን ወንዝ አጠገብ በምትገኘው በሃቦርና በሜዶናውያን ከተሞች አሰፈራቸው።+ 12  ይህ የሆነው የአምላካቸውን የይሖዋን ድምፅ ከመስማት ይልቅ ቃል ኪዳኑን ስላፈረሱ ይኸውም የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ የሰጣቸውን ትእዛዝ በሙሉ ስላልጠበቁ ነው።+ አልሰሙም፤ ደግሞም አልታዘዙም። 13  ንጉሥ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም+ በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ ዘምቶ ያዛቸው።+ 14  በመሆኑም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በለኪሶ ወደነበረው ወደ አሦር ንጉሥ “በድያለሁ። እባክህ ከእኔ ተመለስ፤ እኔም የምትጠይቀኝን ነገር ሁሉ እሰጣለሁ” የሚል መልእክት ላከ። የአሦርም ንጉሥ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ላይ 300 የብር ታላንትና* 30 የወርቅ ታላንት ቅጣት ጣለበት። 15  በመሆኑም ሕዝቅያስ በይሖዋ ቤትና በንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤቶች የተገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው።+ 16  በዚህ ጊዜ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ራሱ የለበጣቸውን*+ የይሖዋን ቤተ መቅደስ በሮችና+ መቃኖች ነቃቅሎ* ለአሦር ንጉሥ ሰጠው። 17  ከዚያም የአሦር ንጉሥ ታርታኑን፣* ራብሳሪሱንና* ራብሻቁን* ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ+ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ላካቸው።+ እነሱም ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ወደ ልብስ አጣቢው እርሻ በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ በሚገኘው በላይኛው ኩሬ የውኃ መውረጃ ቦይ አጠገብ ቆሙ።+ 18  ንጉሡ እንዲመጣ በተጣሩ ጊዜ የንጉሡ ቤት* ኃላፊ የሆነው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣+ ጸሐፊው ሸብናህ+ እና ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአህ ወደ እነሱ ወጡ። 19  ራብሻቁም እንዲህ አላቸው፦ “እስቲ ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፦ ‘ታላቁ ንጉሥ፣ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ “ለመሆኑ እንዲህ እንድትተማመን ያደረገህ ምንድን ነው?+ 20  ‘የጦር ስልትና ለመዋጋት የሚያስችል ኃይል አለኝ’ ትላለህ፤ ይሁንና ይህ ከንቱ ወሬ ነው። ለመሆኑ በእኔ ላይ ለማመፅ የደፈርከው በማን ተማምነህ ነው?+ 21  እነሆ፣ ሰው ቢመረኮዘው እጁ ላይ ሊሰነቀርና ሊወጋው ከሚችለው ከዚህ የተቀጠቀጠ ሸምበቆ፣ ከግብፅ ድጋፍ አገኛለሁ ብለህ ተማምነሃል።+ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው። 22  ‘እኛ የምንታመነው በአምላካችን በይሖዋ ነው’+ የምትሉኝ ከሆነ ደግሞ፣ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ‘መስገድ ያለባችሁ በኢየሩሳሌም በሚገኘው በዚህ መሠዊያ ፊት ነው’+ ብሎ የእሱን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችና መሠዊያዎች አስወግዶ የለም?”’+ 23  በል እስቲ፣ አሁን ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፦ ጋላቢዎች ማግኘት የምትችል ከሆነ 2,000 ፈረሶች እሰጥሃለሁ።+ 24  አንተ የምትታመነው በግብፅ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ነው፤ ታዲያ ከጌታዬ አገልጋዮች መካከል ዝቅተኛ ደረጃ ያለውን አንዱን አለቃ እንኳ እንዴት መመከት ትችላለህ? 25  ለመሆኑ ይህን አካባቢ ለማጥፋት የመጣሁት ይሖዋ ሳይፈቅድልኝ ይመስልሃል? ይሖዋ ራሱ ‘በዚህ ምድር ላይ ዘምተህ አጥፋው’ ብሎኛል።” 26  በዚህ ጊዜ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ሸብናህ+ እና ዮአህ ራብሻቁን+ እንዲህ አሉት፦ “እባክህ፣ እኛ አገልጋዮችህ ቋንቋውን ስለምናውቅ በአረማይክ* ቋንቋ+ አናግረን፤ በቅጥሩ ላይ ያለው ሕዝብ በሚሰማው በአይሁዳውያን ቋንቋ አታነጋግረን።”+ 27  ራብሻቁ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ጌታዬ ይህን ቃል እንድናገር የላከኝ ለጌታህና ለአንተ ብቻ ነው? ከእናንተ ጋር የገዛ ራሳቸውን እዳሪ ለሚበሉትና የገዛ ራሳቸውን ሽንት ለሚጠጡት በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ሰዎች ጭምር አይደለም?” 28  ከዚያም ራብሻቁ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ በአይሁዳውያን ቋንቋ እንዲህ አለ፦ “የታላቁን ንጉሥ፣ የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ።+ 29  ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ ‘ሕዝቅያስ አያታላችሁ፤ እሱ ከእጄ ሊታደጋችሁ አይችልምና።+ 30  ደግሞም ሕዝቅያስ “ይሖዋ በእርግጥ ይታደገናል፤ ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትወድቅም” እያለ በይሖዋ እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።+ 31  ሕዝቅያስን አትስሙት፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላልና፦ “ከእኔ ጋር ሰላም ፍጠሩ፤ እጃችሁንም ስጡ፤* እያንዳንዳችሁም ከራሳችሁ ወይንና ከራሳችሁ በለስ ትበላላችሁ፤ ከራሳችሁም የውኃ ጉድጓድ ትጠጣላችሁ፤ 32  ይህም የሚሆነው መጥቼ የእናንተን ምድር ወደምትመስለው፣ እህልና አዲስ የወይን ጠጅ፣ ዳቦና የወይን እርሻ፣ የወይራ ዛፍና ማር ወደሚገኝባት ምድር እስክወስዳችሁ ድረስ ነው።+ በዚያን ጊዜ በሕይወት ትኖራላችሁ እንጂ አትሞቱም። ሕዝቅያስን አትስሙት፤ ‘ይሖዋ ይታደገናል’ እያለ ያታልላችኋልና። 33  ከብሔራት አማልክት መካከል ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ ያስጣለ አለ? 34  የሃማትና+ የአርጳድ አማልክት የት አሉ? የሰፋርዊም፣+ የሄና እና የኢዋ አማልክትስ የት አሉ? ሰማርያን ከእጄ ማስጣል ችለዋል?+ 35  ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ ምድሩን ከእጄ ማስጣል የቻለ የትኛው ነው? ታዲያ ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ከእጄ ሊያስጥላት ይችላል?”’”+ 36  ሕዝቡ ግን ንጉሡ “ምንም መልስ አትስጡት” ብሎ አዝዞ ስለነበር ዝም አለ፤ አንድም ቃል አልመለሰለትም።+ 37  ይሁንና የቤቱ* አስተዳዳሪ የሆነው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሐፊው ሸብናህ እና ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአህ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፤ ራብሻቁ ያለውንም ነገሩት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

አቢያህ የሚለው ስም አጭር መጠሪያ ነው።
ወይም “ነሑሽታን።”
ጥቂት ሰዎች የሚኖሩባቸውን ቦታዎችም ሆነ ሰው የሚበዛባቸውን ቦታዎች ሁሉ ያመለክታል።
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
በወርቅ የተለበጡ መሆናቸውን ያመለክታል።
ቃል በቃል “ቆርጦ።”
ወይም “የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃ።”
ወይም “የቤተ መንግሥቱን ዋና ባለሥልጣንና።”
ወይም “አዛዡን።”
ወይም “የቤተ መንግሥቱ።”
ወይም “በሶርያ።”
ቃል በቃል “ከእኔ ጋር ባርኩ፤ እንዲሁም ወደ እኔ ውጡ።”
ወይም “የቤተ መንግሥቱ።”