ሁለተኛ ነገሥት 21:1-26

  • ምናሴ በይሁዳ ላይ ነገሠ፤ ብዙ ደምም አፈሰሰ (1-18)

    • ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ ተነገረ (12-15)

  • አምዖን በይሁዳ ላይ ነገሠ (19-26)

21  ምናሴ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 12 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ55 ዓመት ገዛ።+ የእናቱ ስም ሄፍጺባ ነበር።  እሱም ይሖዋ ከእስራኤል ሕዝብ ፊት ያባረራቸው ብሔራት ይፈጽሟቸው የነበሩትን አስጸያፊ ልማዶች በመከተል በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+  አባቱ ሕዝቅያስ አስወግዷቸው የነበሩትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች መልሶ ገነባ፤+ እንዲሁም የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው ለባአል መሠዊያዎችን አቆመ፤+ የማምለኪያ ግንድም* ሠራ።+ ለሰማይ ሠራዊትም ሁሉ ሰገደ፤ እነሱንም አገለገለ።+  በተጨማሪም ይሖዋ “ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ”+ ብሎ በተናገረለት በይሖዋ ቤት ውስጥ መሠዊያዎችን ሠራ።+  ደግሞም በይሖዋ ቤት በሚገኙት በሁለቱ ግቢዎች+ ውስጥ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ።+  የገዛ ልጁን ለእሳት አሳልፎ ሰጠ፤ አስማተኛና መተተኛም ሆነ፤+ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ቀጠረ።+ ይሖዋን ያስቆጣው ዘንድ በእሱ ፊት በጣም ብዙ መጥፎ ነገሮችን ሠራ።  የሠራውንም የማምለኪያ ግንድ* የተቀረጸ ምስል ይሖዋ ለዳዊትና ለልጁ ለሰለሞን እንዲህ ብሎ በተናገረለት ቤት ውስጥ አስቀመጠው፦+ “በዚህ ቤትና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጥኳት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘለቄታው አኖራለሁ።+  እነሱ ያዘዝኳቸውን ሁሉ ይኸውም አገልጋዬ ሙሴ እንዲከተሉት ያዘዛቸውን ሕግ በሙሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ+ እንጂ ከእንግዲህ የእስራኤላውያን እግር ለአባቶቻቸው ከሰጠሁት ምድር ወጥቶ እንዲንከራተት አላደርግም።”+  እነሱ ግን አልታዘዙም፤ ምናሴም ይሖዋ ከእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው ብሔራት የበለጠ ክፉ ነገር እንዲሠሩ አሳታቸው።+ 10  ይሖዋ አገልጋዮቹ በሆኑት ነቢያት አማካኝነት በተደጋጋሚ እንዲህ ይላቸው ነበር፦+ 11  “የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ እነዚህን ሁሉ አስጸያፊ ነገሮች አድርጓል፤ ከእሱ በፊት ከነበሩት አሞራውያን+ ሁሉ ይበልጥ ክፉ ድርጊት ፈጽሟል፤+ አስጸያፊ በሆኑ ጣዖቶቹም* ይሁዳ ኃጢአት እንዲሠራ አድርጓል። 12  ስለዚህ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ለሚሰማው ሰው ሁሉ ጆሮ የሚሰቀጥጥ* ጥፋት በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ።+ 13  በሰማርያ ላይ ተጠቅሜበት የነበረውን የመለኪያ ገመድ+ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ፤+ እንዲሁም በአክዓብ ቤት+ ላይ ተጠቅሜበት የነበረውን ውኃ ልክ* በእሷ ላይ እጠቀማለሁ፤ አንድ ሰው ሳህኑን እንደሚወለውል ሁሉ እኔም ኢየሩሳሌምን ከወለወልኩ በኋላ እገለብጣታለሁ።+ 14  የርስቴን ቀሪዎች እተዋቸዋለሁ፤+ በጠላቶቻቸውም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እነሱም በጠላቶቻቸው ሁሉ ይበዘበዛሉ፤ እንዲሁም ለጠላቶቻቸው ምርኮ ይሆናሉ፤+ 15  ይህን የማደርገው አባቶቻቸው ከግብፅ ከወጡበት ቀን አንስቶ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ በፊቴ መጥፎ የሆነውን ነገር ስላደረጉና በተደጋጋሚ ስላስቆጡኝ ነው።’”+ 16  ምናሴ፣ ይሁዳ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር በመፈጸም ኃጢአት እንዲሠራ በማድረግ ከሠራው ኃጢአት በተጨማሪ ኢየሩሳሌም ከዳር እስከ ዳር በደም እስክትሞላ ድረስ እጅግ ብዙ ንጹሕ ደም አፍስሷል።+ 17  የቀረው የምናሴ ታሪክና ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ እንዲሁም የሠራው ኃጢአት በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 18  በመጨረሻም ምናሴ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቤቱም በሚገኘው የአትክልት ስፍራ ይኸውም በዑዛ የአትክልት ስፍራ ተቀበረ፤+ ልጁም አምዖን በእሱ ምትክ ነገሠ። 19  አምዖን+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 22 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሁለት ዓመት ገዛ።+ እናቱ ሜሹሌሜት ትባል ነበር፤ እሷም የዮጥባ ሰው የሆነው የሃሩጽ ልጅ ነበረች። 20  አምዖን አባቱ ምናሴ እንዳደረገው በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 21  አባቱ በሄደበት መንገድ ሁሉ ተመላለሰ፤ ደግሞም አባቱ ያገለግላቸው የነበሩትን አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶች አገለገለ፤ ለእነሱም ሰገደ።+ 22  የአባቶቹንም አምላክ ይሖዋን ተወ፤ በይሖዋም መንገድ አልሄደም።+ 23  ከጊዜ በኋላም የንጉሥ አምዖን አገልጋዮች በእሱ ላይ አሲረው በገዛ ቤቱ ውስጥ ገደሉት። 24  ሆኖም የምድሪቱ ሕዝብ በንጉሥ አምዖን ላይ ያሴሩትን ሁሉ ገደላቸው፤ በእሱም ምትክ ልጁን ኢዮስያስን አነገሠው።+ 25  የቀረው የአምዖን ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 26  እሱንም በዑዛ የአትክልት ስፍራ በሚገኘው መቃብሩ ቀበሩት፤+ ልጁም ኢዮስያስ+ በምትኩ ነገሠ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ቃል በቃል “ጆሮ የሚነዝር።”
ወይም “ቱምቢ።”