ሁለተኛ ነገሥት 24:1-20

  • ኢዮዓቄም ዓመፀ፤ በኋላም ሞተ (1-7)

  • ዮአኪን በይሁዳ ላይ ነገሠ (8, 9)

  • ለመጀመሪያ ጊዜ በግዞት ወደ ባቢሎን ተወሰዱ (10-17)

  • ሴዴቅያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ፤ እንዲሁም ዓመፀ (18-20)

24  በኢዮዓቄም ዘመን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር+ ምድሪቱን ወረረ፤ ኢዮዓቄምም ለሦስት ዓመት የእሱ አገልጋይ ሆነ። ሆኖም ሐሳቡን ለውጦ ዓመፀበት።  ከዚያም ይሖዋ የከለዳውያንን፣+ የሶርያውያንን፣ የሞዓባውያንንና የአሞናውያንን ወራሪ ቡድኖች ይልክበት ጀመር። ይሖዋ አገልጋዮቹ በሆኑት በነቢያት አማካኝነት በተናገረው ቃል መሠረት+ ይሁዳን እንዲያጠፉ እነዚህን ቡድኖች ይልክባቸው ነበር።  ይህ ነገር ይሖዋ ባዘዘው መሠረት በይሁዳ ላይ የደረሰው ይሁዳን ከፊቱ ለማጥፋት ነው፤+ ይህም የሆነው ምናሴ በሠራቸው ኃጢአቶች ሁሉ የተነሳ ነው፤+  ንጹሕ ደም በማፍሰስ ኢየሩሳሌም በንጹሕ ደም እንድትጥለቀለቅ በማድረጉ ነው፤+ ይሖዋም ይቅር ለማለት ፈቃደኛ አልሆነም።+  የቀረው የኢዮዓቄም ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?+  በመጨረሻም ኢዮዓቄም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤+ በእሱም ምትክ ልጁ ዮአኪን ነገሠ።  የባቢሎን ንጉሥ ከግብፅ ደረቅ ወንዝ*+ አንስቶ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ+ ድረስ የሚገኘውን የግብፅን ንጉሥ+ ምድር ሁሉ ወስዶ ስለነበር የግብፅ ንጉሥ ዳግመኛ ከምድሩ ለመውጣት አልደፈረም።  ዮአኪን+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 18 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሦስት ወር ገዛ።+ እናቱ ነሁሽታ ትባል ነበር፤ እሷም የኢየሩሳሌም ሰው የሆነው የኤልናታን ልጅ ነበረች።  አባቱ እንዳደረገው ሁሉ እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። 10  በዚህ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነጾር አገልጋዮች በኢየሩሳሌም ላይ ዘመቱ፤ ከተማዋም ተከበበች።+ 11  የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር አገልጋዮቹ ከተማዋን ከበው ሳሉ ወደ ከተማዋ መጣ። 12  የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን ከእናቱ፣ ከአገልጋዮቹ፣ ከመኳንንቱና ከቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱ+ ጋር ሆኖ ወደ ባቢሎን ንጉሥ+ ወጣ፤ የባቢሎንም ንጉሥ በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ዮአኪንን ማርኮ ወሰደው።+ 13  ከዚያም በይሖዋ ቤትና በንጉሡ ቤት* የነበሩትን ውድ ዕቃዎች ሁሉ ወሰደ።+ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰለሞን ለይሖዋ ቤተ መቅደስ የሠራቸውን የወርቅ ዕቃዎች በሙሉ ሰባበራቸው።+ ይህ የሆነው ይሖዋ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ነው። 14  ኢየሩሳሌምን በሙሉ፣ መኳንንቱን በሙሉ፣+ ኃያላን ተዋጊዎቹን ሁሉ፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችንና አንጥረኞችን*+ በአጠቃላይ 10,000 ሰዎችን በግዞት ወሰደ። በጣም ድሃ ከሆኑት የምድሪቱ ነዋሪዎች በስተቀር በዚያ የቀረ አልነበረም።+ 15  በዚህ መንገድ ዮአኪንን+ ወደ ባቢሎን በግዞት ወሰደው፤+ በተጨማሪም የንጉሡን እናት፣ የንጉሡን ሚስቶች፣ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱንና በምድሪቱ ውስጥ ያሉትን ታላላቅ ሰዎች ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን በግዞት ወሰደ። 16  ደግሞም የባቢሎን ንጉሥ ኃያላን የሆኑና ለጦርነት የሠለጠኑ ወንዶችን በሙሉ ይኸውም 7,000 ተዋጊዎችን እንዲሁም 1,000 የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችንና አንጥረኞችን* ወደ ባቢሎን በግዞት ወሰደ። 17  ከዚያም የዮአኪንን አጎት ማታንያህን+ በእሱ ምትክ አነገሠው፤ ስሙንም ቀይሮ ሴዴቅያስ+ አለው። 18  ሴዴቅያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 21 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ11 ዓመት ገዛ። እናቱ ሀሙጣል ትባል ነበር፤+ እሷም የሊብና ሰው የሆነው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 19  ኢዮዓቄም እንዳደረገው ሁሉ እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 20  እነዚህ ነገሮች በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የተፈጸሙት ከይሖዋ ቁጣ የተነሳ ነው፤ በመጨረሻም ከፊቱ አስወገዳቸው።+ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዓመፀ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ቤተ መንግሥት።”
“ምሽግ የሚገነቡ ሰዎችን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“ምሽግ የሚገነቡ ሰዎችን” ማለትም ሊሆን ይችላል።