ሁለተኛ ነገሥት 25:1-30
25 ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት፣ በአሥረኛው ወር፣ ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር+ ሠራዊቱን ሁሉ አስከትሎ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ።+ በዙሪያዋም ሰፈረ፤ ደግሞም በዙሪያዋ የአፈር ቁልል ቆለለ፤+
2 ከተማዋም እስከ ንጉሥ ሴዴቅያስ 11ኛ ዓመት ድረስ ተከበበች።
3 በአራተኛው ወር፣ ዘጠነኛ ቀን በከተማዋ ውስጥ ረሃቡ እጅግ ከፋ፤+ በምድሪቱ የሚኖሩትም ሰዎች የሚላስ የሚቀመስ አጡ።+
4 የከተማዋ ቅጥር ተደረመሰ፤+ ከለዳውያን ከተማዋን ከበው ሳለም ወታደሮቹ ሁሉ በንጉሡ የአትክልት ቦታ አቅራቢያ ባለው መንገድ፣ በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በሚገኘው በር በኩል በሌሊት ወጥተው ሸሹ፤ ንጉሡም ወደ አረባ በሚወስደው መንገድ ሄደ።+
5 ይሁንና የከለዳውያን ሠራዊት ንጉሡን አሳደደ፤ እሱንም በኢያሪኮ በረሃማ ሜዳ ላይ ደረሱበት፤ ወታደሮቹም ሁሉ ጥለውት ተበታተኑ።
6 ከዚያም ንጉሡን ይዘው+ በሪብላ ወደነበረው የባቢሎን ንጉሥ አመጡት፤ ደግሞም ፈረዱበት።
7 የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች ዓይኑ እያየ አረዷቸው፤ ከዚያም ናቡከደነጾር የሴዴቅያስን ዓይን አሳወረ፤ በመዳብ የእግር ብረት አስሮም ወደ ባቢሎን ወሰደው።+
8 በአምስተኛው ወር፣ ከወሩም በሰባተኛው ቀን ይኸውም ንጉሥ ናቡከደነጾር በነገሠ በ19ኛው ዓመት፣ የዘቦች አለቃና የባቢሎን ንጉሥ አገልጋይ የሆነው ናቡዛራዳን+ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።+
9 እሱም የይሖዋን ቤት፣+ የንጉሡን ቤትና*+ በኢየሩሳሌም የሚገኙ ቤቶችን በሙሉ አቃጠለ፤+ የታዋቂ ሰዎችንም ቤቶች ሁሉ በእሳት አጋየ።+
10 ከዘቦቹ አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለውን ቅጥር አፈረሰ።+
11 የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን በከተማዋ የቀሩትን በሕይወት የተረፉ ሰዎች፣ ከድተው ወደ ባቢሎን ንጉሥ የሄዱትን ሰዎችና የቀረውን ሕዝብ በግዞት ወሰደ።+
12 ሆኖም የዘቦቹ አለቃ በምድሪቱ ከነበሩት ያጡ የነጡ ድሆች መካከል አንዳንዶቹ የወይን አትክልት ሠራተኞች ሆነው እንዲያገለግሉና የግዳጅ አገልግሎት እንዲሰጡ እዚያው ተዋቸው።+
13 ከለዳውያኑም የይሖዋን ቤት የመዳብ ዓምዶች+ እንዲሁም በይሖዋ ቤት ውስጥ የነበሩትን የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎችና+ የመዳብ ባሕር+ ሰባብረው መዳቡን ወደ ባቢሎን አጋዙ።+
14 በተጨማሪም አመድ ማጠራቀሚያዎቹን፣ አካፋዎቹን፣ የእሳት ማጥፊያዎቹን፣ ጽዋዎቹንና ለቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚውሉትን የመዳብ ዕቃዎች ሁሉ ወሰዱ።
15 የዘቦቹ አለቃ ከንጹሕ ወርቅና ብር የተሠሩትን መኮስተሪያዎችና ጎድጓዳ ሳህኖች ወሰደ።+
16 ንጉሥ ሰለሞን ለይሖዋ ቤት ያሠራቸው ሁለቱ ዓምዶች፣ ባሕሩና የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎቹ የተሠሩበት መዳብ ከብዛቱ የተነሳ ሊመዘን የሚችል አልነበረም።+
17 የእያንዳንዱ ዓምድ ቁመት 18 ክንድ* ነበር፤+ በዓምዱ አናት ላይ ያለው ጌጥ ከመዳብ የተሠራ ሲሆን የጌጡ ርዝማኔ ሦስት ክንድ ነበር፤ በጌጡ ዙሪያ ያሉት ሮማኖችና መረቡ በሙሉ ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ።+ ሁለተኛው ዓምድና መረቡም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነበር።
18 በተጨማሪም የዘቦቹ አለቃ የካህናት አለቃ የሆነውን ሰራያህን፣+ ሁለተኛውን ካህን ሶፎንያስንና+ ሦስቱን የበር ጠባቂዎች ወሰዳቸው።+
19 ደግሞም ከከተማዋ የወታደሮቹ ኃላፊ የሆነን አንድ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን፣ በከተማዋ ውስጥ የነበሩትን አምስቱን የንጉሡ የቅርብ ሰዎች፣ የምድሪቱን ሕዝብ የሚያሰልፈውን የሠራዊቱን አለቃ ጸሐፊ እንዲሁም ከተማዋ ውስጥ የተገኙትን በምድሪቱ የሚኖሩ 60 ተራ ሰዎች ወሰደ።
20 የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን+ እነዚህን ሰዎች ይዞ በሪብላ ወዳለው ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጣቸው።+
21 የባቢሎን ንጉሥ በሃማት+ ምድር ባለችው በሪብላ ሰዎቹን መትቶ ገደላቸው። በዚህ መንገድ ይሁዳ ከምድሩ በግዞት ተወሰደ።+
22 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር በይሁዳ ምድር በተዋቸው ሰዎች ላይ የሳፋን+ ልጅ፣ የአኪቃም+ ልጅ የሆነውን ጎዶልያስን+ አለቃ አድርጎ ሾመው።+
23 የሠራዊቱ አለቆች በሙሉና አብረዋቸው ያሉት ሰዎች የባቢሎን ንጉሥ ጎዶልያስን አለቃ አድርጎ እንደሾመው ሲሰሙ ወዲያውኑ በምጽጳ ወደሚገኘው ወደ ጎዶልያስ መጡ። እነሱም የነታንያህ ልጅ እስማኤል፣ የቃሬሃ ልጅ ዮሃናን፣ የነጦፋዊው የታንሁመት ልጅ ሰራያህና የማአካታዊው ልጅ ያአዛንያህ እንዲሁም አብረዋቸው የነበሩት ሰዎች ናቸው።+
24 ጎዶልያስ ለእነሱና አብረዋቸው ለነበሩት ሰዎች “የከለዳውያን አገልጋይ መሆን አያስፈራችሁ። በምድሪቱ ላይ ኑሩ፤ የባቢሎንንም ንጉሥ አገልግሉ፤ መልካምም ይሆንላችኋል”+ ሲል ማለላቸው።
25 በሰባተኛውም ወር፣ ከንጉሣውያን ቤተሰብ* የሆነው የኤሊሻማ ልጅ፣ የነታንያህ ልጅ እስማኤል+ ከሌሎች አሥር ሰዎች ጋር መጣ፤ እነሱም ጎዶልያስን መቱት፤ እሱም በምጽጳ አብረውት ከነበሩት አይሁዳውያንና ከለዳውያን ጋር ሞተ።+
26 ከዚያ በኋላ የሠራዊቱን አለቆች ጨምሮ ትልቅ ትንሽ ሳይባል ሕዝቡ ሁሉ ተነስተው ወደ ግብፅ ሄዱ፤+ ከለዳውያንን ፈርተው ነበርና።+
27 የባቢሎን ንጉሥ ኤዊልሜሮዳክ በነገሠበት ዓመት የይሁዳን ንጉሥ ዮአኪንን+ ከእስር ቤት ፈታው፤* ይህም የሆነው የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በግዞት በተወሰደ በ37ኛው ዓመት፣ በ12ኛው ወር፣ ከወሩም በ27ኛው ቀን ነበር።+
28 በርኅራኄም አናገረው፤ ዙፋኑንም በባቢሎን ከእሱ ጋር ከነበሩት ከሌሎች ነገሥታት ዙፋን ይበልጥ ከፍ ከፍ አደረገለት።
29 በመሆኑም ዮአኪን የእስር ቤት ልብሱን አወለቀ፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ በቋሚነት ከንጉሡ ማዕድ ይመገብ ነበር።
30 ንጉሡም ለዮአኪን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሳያቋርጥ ቀለቡን በየዕለቱ ይሰጠው ነበር።