ሁለተኛ ነገሥት 3:1-27
3 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ በነገሠ በ18ኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ ኢዮራም+ በሰማርያ ሆኖ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ እሱም ለ12 ዓመት ገዛ።
2 ኢዮራም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤ ሆኖም አባቱ ወይም እናቱ ያደረጉትን ያህል ክፉ ድርጊት አልፈጸመም፤ አባቱ የሠራውን የባአል የማምለኪያ ዓምድ አስወግዶ ነበርና።+
3 ይሁንና የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን ኃጢአት እንዲሠሩ በማድረግ+ የተከተለውን የኃጢአት ጎዳና የሙጥኝ አለ። ከዚያ ፈቀቅ አላለም።
4 የሞዓብ ንጉሥ ሜሻ በግ አርቢ ነበር፤ እሱም ለእስራኤል ንጉሥ 100,000 የበግ ጠቦቶችንና 100,000 ያልተሸለቱ አውራ በጎችን ይገብር ነበር።
5 አክዓብ እንደሞተ+ የሞዓብ ንጉሥ በእስራኤል ንጉሥ ላይ ዓመፀ።+
6 በዚህ ጊዜ ንጉሥ ኢዮራም ከሰማርያ ወጥቶ በመሄድ እስራኤልን ሁሉ አሰለፈ።
7 በተጨማሪም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ኢዮሳፍጥ “የሞዓብ ንጉሥ ዓምፆብኛል። ሞዓብን ለመውጋት አብረኸኝ ትሄዳለህ?” የሚል መልእክት ላከበት። እሱም “አብሬህ እሄዳለሁ።+ እኔ ማለት እኮ አንተ ማለት ነህ። ሕዝቤ፣ ሕዝብህ ነው። ፈረሶቼም ፈረሶችህ ናቸው” አለው።+
8 ከዚያም “ታዲያ በየትኛው መንገድ ብንወጣ ይሻላል?” ብሎ ጠየቀው። እሱም “ወደ ኤዶም ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ” አለው።
9 በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ ከይሁዳ ንጉሥና ከኤዶም+ ንጉሥ ጋር አብሮ ሄደ። ለሰባት ቀን ያህል በሌላ አቅጣጫ ዞረው ከሄዱ በኋላ ለሠራዊቱም ሆነ እየተከተሏቸው ለነበሩት የቤት እንስሳት የሚሆን ውኃ አጡ።
10 ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ “በጣም አስደንጋጭ ነው! ይሖዋ እነዚህን ሦስት ነገሥታት የጠራው ለሞዓብ አሳልፎ ለመስጠት ነው!” አለ።
11 በዚህ ጊዜ ኢዮሳፍጥ “በእሱ አማካኝነት ይሖዋን ልንጠይቅ የምንችልበት የይሖዋ ነቢይ እዚህ የለም?” አለ።+ ከእስራኤል ንጉሥ አገልጋዮች አንዱ “ኤልያስን+ እጅ ያስታጥብ የነበረው* የሻፋጥ ልጅ ኤልሳዕ+ እዚህ አለ” ሲል መለሰ።
12 ከዚያም ኢዮሳፍጥ “የይሖዋ ቃል እሱ ዘንድ ይገኛል” አለ። በዚህም መሠረት የእስራኤል ንጉሥ፣ ኢዮሳፍጥና የኤዶም ንጉሥ ወደ እሱ ወረዱ።
13 ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ “እኔና አንተን ምን የሚያገናኘን ነገር አለ?+ ወደ አባትህ ነቢያትና ወደ እናትህ ነቢያት ሂድ”+ አለው። የእስራኤል ንጉሥ ግን “ይሄማ አይሆንም፤ ይሖዋ እኮ እነዚህን ሦስት ነገሥታት ጠርቶ በሞዓብ እጅ አሳልፎ ሊሰጣቸው ነው” አለው።
14 በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ እንዲህ አለ፦ “በማገለግለውና* ሕያው በሆነው በሠራዊት ጌታ በይሖዋ እምላለሁ፣ ለማከብረው ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮሳፍጥ+ ብዬ ነው እንጂ ዓይንህን አላይም፣ ጉዳዬም አልልህም ነበር።+
15 በሉ አሁን በገና የሚደረድር ሰው*+ አምጡልኝ።” በገና የሚደረድረውም ሰው መጫወት ሲጀምር የይሖዋ እጅ በኤልሳዕ ላይ መጣ።+
16 እሱም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዚህ ሸለቆ* ውስጥ ብዙ ቦዮች ቆፍሩ፤
17 ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ “ነፋስም ሆነ ዝናብ አታዩም፤ ይሁንና ይህ ሸለቆ* በውኃ ይሞላል፤+ እናንተም ሆናችሁ ከብቶቻችሁ እንዲሁም ሌሎች እንስሶቻችሁ ከዚያ ትጠጣላችሁ።”’
18 ይህ ለይሖዋ በጣም ቀላል ነገር ነው፤+ ሞዓብንም በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋልና።+
19 እናንተም እያንዳንዱን የተመሸገ ከተማና+ እያንዳንዱን የተመረጠ ከተማ ትመታላችሁ፤ ጥሩውንም ዛፍ ሁሉ ትቆርጣላችሁ፤ የውኃ ምንጮችን በሙሉ ትደፍናላችሁ፤ ጥሩውንም መሬት ሁሉ በድንጋይ ታበላሻላችሁ።”+
20 በነጋታውም የጠዋት የእህል መባ+ በሚቀርብበት ጊዜ በድንገት ውኃ ከኤዶም አቅጣጫ መጣ፤ ምድሪቱም በውኃው ተጥለቀለቀች።
21 ሞዓባውያንም ነገሥታቱ ሊወጓቸው እንደመጡ ሲሰሙ የጦር መሣሪያ መታጠቅ የሚችሉ* ሰዎችን ሁሉ ሰብስበው ድንበሩ ላይ ቆሙ።
22 በማለዳ ሲነሱም ፀሐይዋ በውኃው ላይ ታንጸባርቅ ነበር፤ ማዶ ለነበሩት ሞዓባውያንም ውኃው እንደ ደም ቀልቶ ታያቸው።
23 እነሱም “ይሄማ ደም ነው! ነገሥታቱ ያለጥርጥር እርስ በርሳቸው በሰይፍ ተራርደዋል። ስለዚህ ሞዓብ ሆይ፣ ወደ ምርኮህ+ ሂድ!” አሉ።
24 እነሱም ወደ እስራኤል ሰፈር ሲመጡ እስራኤላውያን ተነስተው ሞዓባውያንን መምታት ጀመሩ፤ እነሱም ከፊታቸው ሸሹ።+ እስራኤላውያንም ሞዓባውያንን እየመቱ ወደ ሞዓብ ገሰገሱ።
25 ከተሞቹንም ደመሰሱ፤ እያንዳንዱም ሰው ድንጋይ እየጣለ ጥሩውን መሬት ሁሉ በድንጋይ ሞላው፤ የውኃ ምንጮቹን በሙሉ ደፈኑ፤+ ጥሩውንም ዛፍ ሁሉ ቆረጡ።+ በመጨረሻም የቂርሃረሰት+ የድንጋይ ግንቦች ብቻ ቆመው ቀሩ፤ ወንጭፍ የሚወነጭፉትም ዙሪያዋን ከበው መቷት።
26 የሞዓብ ንጉሥ በውጊያው እንደተሸነፈ ባየ ጊዜ ወደ ኤዶም ንጉሥ+ ጥሶ ለመግባት ሰይፍ የታጠቁ 700 ሰዎችን ወሰደ፤ ሆኖም አልተሳካላቸውም።
27 ስለዚህ በእሱ ምትክ የሚነግሠውን የበኩር ልጁን ወስዶ ቅጥሩ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው።+ በእስራኤልም ላይ ታላቅ ቁጣ ሆነ፤ በመሆኑም አካባቢውን ለቀው ወደ ምድራቸው ተመለሱ።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “የኤልያስ አገልጋይ የነበረው።”
^ ቃል በቃል “ፊቱ በምቆመውና።”
^ ወይም “አንድ ሙዚቀኛ።”
^ ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
^ ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
^ ወይም “መታጠቂያ የታጠቁ።”