ሁለተኛ ነገሥት 7:1-20

  • ኤልሳዕ የረሃቡ ጊዜ እንደሚያበቃ ትንቢት ተናገረ (1, 2)

  • ሶርያውያን ጥለውት በሸሹት ጦር ሰፈር ብዙ ምግብ ተገኘ (3-15)

  • ኤልሳዕ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ (16-20)

7  ኤልሳዕም እንዲህ አለ፦ “የይሖዋን ቃል ስሙ። ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ነገ በዚህ ሰዓት ገደማ በሰማርያ በር* ላይ አንድ የሲህ መስፈሪያ* የላመ ዱቄት በአንድ ሰቅል* እንዲሁም ሁለት የሲህ መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ይሸጣል።’”+  በዚህ ጊዜ ንጉሡ የሚተማመንበት የጦር መኮንን የእውነተኛውን አምላክ ሰው “ይሖዋ የሰማይን የውኃ በሮች ቢከፍት እንኳ እንዲህ ያለ ነገር* ሊፈጸም ይችላል?”+ አለው። ኤልሳዕም “ይህን በገዛ ዓይኖችህ ታያለህ፤+ ሆኖም ከዚያ ምንም አትቀምስም”+ አለው።  በከተማዋ መግቢያ በር ላይ በሥጋ ደዌ የተያዙ አራት ሰዎች ነበሩ፤+ እነሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “እስክንሞት ድረስ እዚህ ቁጭ የምንለው ለምንድን ነው?  ‘ወደ ከተማዋ እንግባ’ ብንል ከተማዋ ውስጥ ረሃብ+ ስላለ እዚያ መሞታችን አይቀርም። እዚህም ብንቀመጥ ያው የሚጠብቀን ሞት ነው። ስለዚህ ዝም ብለን ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሂድ። ካልገደሉን ሕይወታችን ይተርፋል፤ ከገደሉንም ያው ሞቶ መገላገል ነው።”  ከዚያም ጨለምለም ሲል ተነስተው ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄዱ። ወደ ሶርያውያን ሰፈር ዳርቻ በደረሱ ጊዜ በዚያ አንድም ሰው አልነበረም።  ምክንያቱም ይሖዋ የሶርያውያን ሰፈር የጦር ሠረገሎችን ድምፅ፣ የፈረሶችን ድምፅና የታላቅ ሠራዊት ድምፅ እንዲሰማ አድርጎ ነበር።+ በመሆኑም እርስ በርሳቸው “የእስራኤል ንጉሥ እኛን ለመውጋት የሂታውያንንና የግብፅን ነገሥታት ቀጥሮብናል!” ተባባሉ።  እነሱም ወዲያውኑ ተነስተው በምሽት ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውን፣ ፈረሶቻቸውንና አህዮቻቸውን እንዲሁም ሰፈሩን እንዳለ ትተው ሕይወታቸውን* ለማዳን እግሬ አውጪኝ አሉ።  በሥጋ ደዌ የተያዙት እነዚህ ሰዎች ወደ ሰፈሩ ዳርቻ ከደረሱ በኋላ ወደ አንዱ ድንኳን ገብተው መብላትና መጠጣት ጀመሩ። ከዚያም ብር፣ ወርቅና ልብስ ይዘው በመሄድ ደበቁት። ከዚያም ተመልሰው መጥተው ወደ ሌላ ድንኳን በመግባት የተለያዩ ነገሮችን ወሰዱ፤ እነዚህንም ይዘው በመሄድ ደበቁ።  በመጨረሻም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “እያደረግን ያለነው ነገር ትክክል አይደለም። ይህ ቀን እኮ ምሥራች የሚነገርበት ቀን ነው! የምናመነታና እስኪነጋ ድረስ የምንጠብቅ ከሆነ መቀጣታችን አይቀርም። በመሆኑም አሁን ወደ ንጉሡ ቤት ሄደን ይህን ነገር እንናገር።” 10  ስለሆነም ሄደው የከተማዋን በር ጠባቂዎች በመጥራት እንዲህ አሏቸው፦ “ወደ ሶርያውያን ሰፈር ገብተን ነበር፤ ሆኖም በዚያ አንድም ሰው አልነበረም፤ የአንድም ሰው ድምፅ አልሰማንም። እዚያ የነበሩት የታሰሩ ፈረሶችና አህዮች ብቻ ናቸው፤ ድንኳኖቹም እንዳሉ ነበሩ።” 11  የከተማዋ በር ጠባቂዎችም ወዲያውኑ ይህን አስተጋቡ፤ ወሬውም በንጉሡ ቤት ተሰማ። 12  ንጉሡም ወዲያውኑ በሌሊት ተነስቶ አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “ሶርያውያን ምን እንዳደረጉብን ልንገራችሁ። እንደተራብን+ ያውቃሉ፤ በመሆኑም ‘እነሱ ከተማዋን ለቀው ይወጣሉ፤ እኛም በሕይወት እንዳሉ እንይዛቸዋለን፤ ወደ ከተማዋም እንገባለን’ በማለት በዱር ለመደበቅ ከሰፈሩ ወጥተው ሄደዋል።”+ 13  ከዚያም ከአገልጋዮቹ አንዱ እንዲህ አለ፦ “የተወሰኑ ሰዎች በከተማዋ ውስጥ ከቀሩት ፈረሶች አምስቱን ይዘው ይሂዱ። እነዚህ ሰዎች እንደሆነ እዚህ ከሚቀረው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የተለየ ምንም አይደርስባቸውም። የሚጠብቃቸው ነገር ቢኖር በዚህ እንዳለቁት እስራኤላውያን መሆን ነው። ስለሆነም እንላካቸውና የሚሆነውን እንይ።” 14  ስለዚህ ሁለት ሠረገሎችን ከፈረሶች ጋር ወሰዱ፤ ንጉሡም “ሄዳችሁ እዩ” በማለት ወደ ሶርያውያን ሰፈር ላካቸው። 15  እነሱም ዮርዳኖስ ድረስ ተከትለዋቸው ሄዱ፤ ሶርያውያን በድንጋጤ ሲሸሹ ጥለዋቸው የሄዱት ልብሶችና ዕቃዎች መንገዱን ሁሉ ሞልተውት ነበር። መልእክተኞቹም ተመልሰው በመምጣት ሁኔታውን ለንጉሡ ነገሩት። 16  ከዚያም ሕዝቡ ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ በመሆኑም ይሖዋ በተናገረው መሠረት አንድ የሲህ መስፈሪያ የላመ ዱቄት በአንድ ሰቅል እንዲሁም ሁለት የሲህ መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ተሸጠ።+ 17  ንጉሡ፣ የሚተማመንበትን የጦር መኮንን የከተማዋ በር ኃላፊ አድርጎ ሾመው፤ ይሁንና ሕዝቡ በሩ ላይ የጦር መኮንኑን ረጋገጠው፤ የእውነተኛው አምላክ ሰው ንጉሡ ወደ እሱ በወረደ ጊዜ በተናገረው መሠረት ሞተ። 18  የእውነተኛው አምላክ ሰው “ነገ በዚህ ሰዓት በሰማርያ በር ላይ ሁለት የሲህ መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል እንዲሁም አንድ የሲህ መስፈሪያ የላመ ዱቄት በአንድ ሰቅል ይሸጣል”+ በማለት ለንጉሡ የተናገረው ነገር ተፈጸመ። 19  የጦር መኮንኑ ግን የእውነተኛውን አምላክ ሰው “ይሖዋ የሰማይን የውኃ በሮች ቢከፍት እንኳ ይህ የተባለው ነገር* ይፈጸማል?” ብሎት ነበር። በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ “ይህን በገዛ ዓይኖችህ ታያለህ፤ ሆኖም ከዚያ ምንም አትቀምስም” ብሎት ነበር። 20  የጦር መኮንኑ፣ ሕዝቡ በሩ ላይ ረጋግጦት ስለሞተ ልክ እንደተባለው ደረሰበት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ገበያ።”
አንድ ሲህ 7.33 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ይህ ቃል።”
ወይም “ነፍሳቸውን።”
ቃል በቃል “እንዲህ ያለ ቃል።”