ሁለተኛ ነገሥት 8:1-29

  • ሹነማዊቷ ሴት መሬቷ ተመለሰላት (1-6)

  • ኤልሳዕ፣ ቤንሃዳድና ሃዛኤል (7-15)

  • ኢዮራም በይሁዳ ላይ ነገሠ (16-24)

  • አካዝያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ (25-29)

8  ኤልሳዕ፣ ልጇን ከሞት ያስነሳላትን+ ሴት “ተነስተሽ ከቤተሰብሽ ጋር የባዕድ አገር ሰው ሆነሽ መኖር ወደምትችዪበት ቦታ ሂጂ፤ ይሖዋ ረሃብ እንደሚከሰት ተናግሯልና፤+ ደግሞም ረሃቡ በምድሪቱ ላይ ለሰባት ዓመት ይቆያል” አላት።  በመሆኑም ሴትየዋ ተነስታ የእውነተኛው አምላክ ሰው እንደነገራት አደረገች። እሷም ከመላ ቤተሰቧ ጋር ሄደች፤ በፍልስጤማውያንም+ ምድር ለሰባት ዓመት ተቀመጠች።  በሰባቱ ዓመት ማብቂያ ላይ ሴትየዋ ከፍልስጤማውያን ምድር ተመልሳ መጣች፤ ከዚያም ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ ለንጉሡ አቤቱታ ለማቅረብ ሄደች።  በዚህ ጊዜ ንጉሡ የእውነተኛው አምላክ ሰው አገልጋይ የሆነውን ግያዝን “እስቲ ኤልሳዕ ያደረጋቸውን ታላላቅ ነገሮች በሙሉ ተርክልኝ” እያለው ነበር።+  እሱም ኤልሳዕ የሞተውን ልጅ እንዴት እንዳስነሳው+ ለንጉሡ እየተረከለት ሳለ ኤልሳዕ ልጇን ከሞት ያስነሳላት ሴት ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ ለንጉሡ አቤቱታ ለማቅረብ መጣች።+ ግያዝም ወዲያውኑ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ሴትየዋ ይህች ናት፤ ኤልሳዕ ያስነሳው ልጇም ይሄ ነው” አለው።  በዚህ ጊዜ ንጉሡ ሴትየዋን ጠየቃት፤ እሷም ታሪኩን ነገረችው። ከዚያም ንጉሡ ከቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱ አንዱን “የእሷ የሆነውን በሙሉ እንዲሁም መሬቷን ከለቀቀችበት ቀን አንስቶ እስካሁን ድረስ መሬቱ ያፈራውን ምርት ሁሉ መልስላት” የሚል መመሪያ በመስጠት መደበላት።  የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ+ ታሞ ሳለ ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ+ መጣ። በመሆኑም “የእውነተኛው አምላክ ሰው+ ወደዚህ መጥቷል” ተብሎ ተነገረው።  በዚህ ጊዜ ንጉሡ ሃዛኤልን+ “ስጦታ ይዘህ ወደ እውነተኛው አምላክ ሰው+ ሂድ። በእሱም አማካኝነት ይሖዋን ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁ?’ ብለህ ጠይቀው” አለው።  ሃዛኤልም በደማስቆ ከሚገኘው ምርጥ ነገር ሁሉ 40 የግመል ጭነት ስጦታ ይዞ ሊያገኘው ሄደ። እሱም መጥቶ በፊቱ በመቆም “ልጅህ የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁ?’ በማለት ወደ አንተ ልኮኛል” አለው። 10  ኤልሳዕም “ሂድና ‘በእርግጥ ትድናለህ’ በለው፤ ሆኖም መሞቱ እንደማይቀር ይሖዋ አሳይቶኛል”+ ሲል መለሰለት። 11  ደግሞም እስኪያፍር ድረስ ትኩር ብሎ ተመለከተው። ከዚያም የእውነተኛው አምላክ ሰው አለቀሰ። 12  ሃዛኤልም “ጌታዬ የሚያለቅሰው ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቀው። እሱም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “በእስራኤል ሕዝብ ላይ ምን ዓይነት ጉዳት እንደምታደርስ ስለማውቅ ነው።+ የተመሸጉ ስፍራዎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ምርጥ የሆኑ ሰዎቻቸውን በሰይፍ ትገድላለህ፤ ልጆቻቸውንም ትፈጠፍጣለህ፤ ነፍሰ ጡር የሆኑ ሴቶቻቸውንም ሆድ ትቀድዳለህ።”+ 13  ሃዛኤልም “ለመሆኑ ተራ ውሻ የሆነው አገልጋይህ እንዲህ ያለ ነገር እንዴት ሊያደርግ ይችላል?” አለው። ኤልሳዕ ግን “አንተ በሶርያ ላይ ንጉሥ እንደምትሆን ይሖዋ አሳይቶኛል” አለው።+ 14  ከዚያም ከኤልሳዕ ተለይቶ በመሄድ ወደ ጌታው መጣ፤ ቤንሃዳድም “ለመሆኑ ኤልሳዕ ምን አለህ?” አለው። እሱም “በእርግጥ እንደምትድን ነግሮኛል” ሲል መለሰለት።+ 15  በማግስቱ ግን ሃዛኤል የአልጋ ልብስ ወስዶ ውኃ ውስጥ ከነከረ በኋላ የንጉሡን ፊት ሸፈነው፤ ንጉሡም ሞተ።+ ሃዛኤልም በምትኩ ነገሠ።+ 16  የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም+ በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሳፍጥ ልጅ ኢዮራም ነገሠ፤+ በዚህ ጊዜ ኢዮሳፍጥ በይሁዳ ንጉሥ ሆኖ ይገዛ ነበር። 17  ኢዮራም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 32 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ስምንት ዓመት ገዛ። 18  የአክዓብን ልጅ አግብቶ+ ስለነበር ከአክዓብ ቤት የሆኑት እንዳደረጉት+ ሁሉ እሱም በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤+ በይሖዋም ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 19  ሆኖም ይሖዋ ለአገልጋዩ ለዳዊት ሲል ይሁዳን ማጥፋት አልፈለገም፤+ ምክንያቱም ለእሱና ለልጆቹ ለሁልጊዜ የሚኖር መብራት እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ነበር።+ 20  በእሱ ዘመን ኤዶም በይሁዳ ላይ ዓምፆ+ የራሱን ንጉሥ አነገሠ።+ 21  በመሆኑም ኢዮራም ሠረገሎቹን ሁሉ ይዞ ወደ ጻኢር ተሻገረ፤ በሌሊትም ተነስቶ እሱንና የሠረገሎቹን አዛዦች ከበው የነበሩትን ኤዶማውያን ድል አደረገ፤ ሠራዊቱም ሸሽቶ ወደየድንኳኑ ሄደ። 22  ሆኖም ኤዶም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንዳመፀ ነው። ሊብናም+ በዚሁ ጊዜ ዓመፀ። 23  የቀረው የኢዮራም ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 24  በመጨረሻም ኢዮራም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ከአባቶቹም ጋር በዳዊት ከተማ ተቀበረ።+ በእሱም ምትክ ልጁ አካዝያስ+ ነገሠ። 25  የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በ12ኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ነገሠ።+ 26  አካዝያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 22 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም ጎቶልያ+ የተባለች የእስራኤል ንጉሥ የኦምሪ+ የልጅ ልጅ* ነበረች። 27  እሱም ከአክዓብ ቤተሰብ ጋር በጋብቻ ተሳስሮ ስለነበር የአክዓብን ቤት መንገድ ተከተለ፤ እንዲሁም የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 28  በመሆኑም አካዝያስ ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር ሆኖ ከሶርያ ንጉሥ ከሃዛኤል ጋር ለመዋጋት ወደ ራሞትጊልያድ+ ሄደ፤ ሆኖም ሶርያውያን ኢዮራምን አቆሰሉት።+ 29  ስለዚህ ንጉሥ ኢዮራም ከሶርያ ንጉሥ ከሃዛኤል ጋር በተዋጋበት ጊዜ ሶርያውያን በራማ ካቆሰሉት ቁስል ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል+ ተመለሰ።+ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ፣ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም ቆስሎ* ስለነበር እሱን ለማየት ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ሴት ልጅ።”
ወይም “ታሞ።”