ሁለተኛ ዜና መዋዕል 1:1-17

  • ሰለሞን ጥበብ እንዲሰጠው ጠየቀ (1-12)

  • የሰለሞን ሀብት (13-17)

1  የዳዊት ልጅ ሰለሞን ንግሥናውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከረ ሄደ፤ አምላኩ ይሖዋም ከእሱ ጋር ስለነበር እጅግ ገናና አደረገው።+  ሰለሞን ለእስራኤል ሁሉ፣ ለሺህ አለቆች፣ ለመቶ አለቆች፣ ለፈራጆችና የአባቶች ቤቶች መሪዎች ለሆኑት በመላው እስራኤል ለሚገኙት አለቆች ሁሉ መልእክት ላከ።  ከዚያም ሰለሞንና መላው ጉባኤ በገባኦን+ ወደሚገኘው ኮረብታ ሄዱ፤ ምክንያቱም የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእውነተኛው አምላክ የመገናኛ ድንኳን የሚገኘው በዚያ ነበር።  ይሁን እንጂ ዳዊት የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ከቂርያትየአሪም+ እሱ ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ድንኳን ተክሎለት ነበር።+  የሁር ልጅ የዖሪ ልጅ ባስልኤል+ የሠራው የመዳብ መሠዊያ+ በይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ፊት ይገኝ ነበር፤ ሰለሞንና ጉባኤውም በመሠዊያው ፊት ይጸልዩ ነበር።*  ሰለሞንም በዚያ በይሖዋ ፊት መባ አቀረበ፤ በመገናኛው ድንኳን በሚገኘው የመዳብ መሠዊያ ላይ 1,000 የሚቃጠሉ መባዎችን አቀረበ።+  በዚያ ሌሊት አምላክ ለሰለሞን ተገልጦ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ጠይቅ” አለው።+  በዚህ ጊዜ ሰለሞን አምላክን እንዲህ አለው፦ “ለአባቴ ለዳዊት ጥልቅ የሆነ ታማኝ ፍቅር አሳይተኸዋል፤+ በእሱም ምትክ አንግሠኸኛል።+  አሁንም ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸው ቃል ይፈጸም፤+ እንደ ምድር አፈር እጅግ ብዙ በሆነ ሕዝብ+ ላይ አንግሠኸኛልና። 10  ይህን ሕዝብ መምራት* እንድችል ጥበብና እውቀት ስጠኝ፤+ አለዚያማ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊዳኝ ይችላል?”+ 11  ከዚያም አምላክ ሰለሞንን እንዲህ አለው፦ “የልብህ መሻት ይህ ስለሆነ ደግሞም ብልጽግና፣ ሀብትና ክብር ወይም የሚጠሉህን ሰዎች ሞት* አሊያም ረጅም ዕድሜ* ስላልተመኘህ፣ ይልቁንም አንተን ንጉሥ አድርጌ የሾምኩበትን ሕዝቤን ማስተዳደር እንድትችል ጥበብና እውቀት ስለጠየቅክ፣+ 12  ጥበብና እውቀት ይሰጥሃል፤ ከዚህም ሌላ ከአንተ በፊት የነበረ ማንኛውም ንጉሥ ያላገኘውን፣ ከአንተም በኋላ የሚነሳ የትኛውም ንጉሥ የማያገኘውን ብልጽግና፣ ሀብትና ክብር እሰጥሃለሁ።”+ 13  ሰለሞንም በገባኦን+ ኮረብታ ከሚገኘው ከመገናኛው ድንኳን ፊት ወጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ። 14  ሰለሞን ሠረገሎችንና ፈረሶችን* መሰብሰቡን ቀጠለ፤ እሱም 1,400 ሠረገሎችና 12,000 ፈረሶች* ነበሩት፤+ እነሱንም በሠረገላ ከተሞችና+ በኢየሩሳሌም በንጉሡ አቅራቢያ አኖራቸው።+ 15  ንጉሡ ብርና ወርቅ በየቦታው እንደሚገኝ ድንጋይ እስኪሆን ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲበዛ አደረገ፤+ አርዘ ሊባኖሱንም ከብዛቱ የተነሳ በሸፌላ እንደሚገኘው የሾላ ዛፍ አደረገው።+ 16  የሰለሞን ፈረሶች ከግብፅ ያስመጣቸው ነበሩ፤+ የንጉሡ ነጋዴዎችም የፈረሶቹን መንጋ አንዴ በተተመነው ዋጋ ይገዙ ነበር።*+ 17  ከግብፅ የሚመጣው እያንዳንዱ ሠረገላ 600 የብር ሰቅል ያወጣ ነበር፤ አንድ ፈረስ ደግሞ 150 ሰቅል ያወጣል፤ እነሱ ደግሞ በተራቸው ለሂታውያን ነገሥታትና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ይሸጡ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በዚያ አምላክን ይጠይቁ ነበር።”
ቃል በቃል “በዚህ ሕዝብ ፊት መውጣትና መግባት።”
ወይም “ነፍስ።”
ቃል በቃል “ብዙ ቀናት።”
ወይም “ፈረሰኞች።”
ወይም “ፈረሰኞችን።”
“ከግብፅና ከቀዌ ያስመጣቸው ነበሩ፤ የንጉሡ ነጋዴዎች ከቀዌ አንዴ በተተመነው ዋጋ ይገዟቸው ነበር” ማለትም ሊሆን ይችላል። ቀዌ ኪልቅያን ልታመለክት ትችላለች።