ሁለተኛ ዜና መዋዕል 12:1-16

  • ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ (1-12)

  • የሮብዓም አገዛዝ አበቃ (13-16)

12  ሮብዓም በበረታና ንግሥናው በጸና ጊዜ+ እሱም ሆነ አብረውት ያሉት እስራኤላውያን ሁሉ የይሖዋን ሕግ ተዉ።+  ለይሖዋ ታማኝ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ንጉሥ ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ+ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ።  እሱም 1,200 ሠረገሎችና 60,000 ፈረሰኞች አስከትሎ ነበር፤ ከእሱም ጋር ከግብፅ የመጡት ሊቢያውያን፣ ሱኪማውያንና ኢትዮጵያውያን+ ወታደሮች ስፍር ቁጥር አልነበራቸውም።  እሱም የይሁዳን የተመሸጉ ከተሞች ያዘ፤ በመጨረሻም ኢየሩሳሌም ደረሰ።  ነቢዩ ሸማያህ+ ወደ ሮብዓምና ሺሻቅን ፈርተው በኢየሩሳሌም ወደተሰበሰቡት የይሁዳ መኳንንት መጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እናንተ ትታችሁኛል፤+ ስለዚህ እኔም በሺሻቅ እጅ ትቻችኋለሁ።’”  በዚህ ጊዜ የእስራኤል መኳንንትና ንጉሡ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ+ “ይሖዋ ጻድቅ ነው” አሉ።  ይሖዋ ራሳቸውን ዝቅ እንዳደረጉ ባየ ጊዜ፣ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሸማያህ መጣ፦ “ራሳቸውን ዝቅ ስላደረጉ አላጠፋቸውም፤+ በቅርቡም እታደጋቸዋለሁ። ቁጣዬንም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አላፈስም።  ይሁን እንጂ እኔን በማገልገልና የሌሎች አገሮች ነገሥታትን* በማገልገል መካከል ያለውን ልዩነት እንዲያውቁ የእሱ አገልጋዮች ይሆናሉ።”  በመሆኑም የግብፁ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን ለመውጋት መጣ። እሱም በይሖዋ ቤት የነበሩትን ውድ ንብረቶችና በንጉሡ ቤት* የነበሩትን ውድ ንብረቶች ወሰደ።+ ሰለሞን የሠራቸውን የወርቅ ጋሻዎች ጨምሮ ሁሉንም ነገር ወሰደ።+ 10  በመሆኑም ንጉሥ ሮብዓም በእነሱ ምትክ የመዳብ ጋሻዎችን ሠርቶ የንጉሡን ቤት በር ለሚጠብቁት የዘብ* አለቆች ሰጣቸው። 11  ዘቦቹም ንጉሡ ወደ ይሖዋ ቤት በመጣ ቁጥር ገብተው ጋሻዎቹን ያነግቡ ነበር፤ ከዚያም ወደ ዘቦቹ ክፍል ይመልሷቸው ነበር። 12  ንጉሡ ራሱን ስላዋረደ የይሖዋ ቁጣ ከእሱ ተመለሰ፤+ ሙሉ በሙሉም አላጠፋቸውም።+ በተጨማሪም በይሁዳ አንዳንድ መልካም ነገሮች ተገኝተው ነበር።+ 13  ንጉሥ ሮብዓም በኢየሩሳሌም ሥልጣኑን አጠናክሮ መግዛቱን ቀጠለ፤ ሮብዓም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 41 ዓመት ነበር፤ እሱም ይሖዋ ስሙ እንዲኖርባት ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም ሆኖ 17 ዓመት ገዛ። የንጉሡም እናት ናዕማ የተባለች አሞናዊት ነበረች።+ 14  ሆኖም ይሖዋን ለመፈለግ ከልቡ ቆርጦ ስላልተነሳ ክፉ ነገር አደረገ።+ 15  ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለው የሮብዓም ታሪክ ነቢዩ ሸማያህና+ ባለ ራእዩ ኢዶ+ በትውልድ ሐረግ መዝገቡ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ውስጥ ይገኝ የለም? በሮብዓምና በኢዮርብዓም+ መካከል ምንጊዜም ጦርነት ይካሄድ ነበር። 16  በመጨረሻም ሮብዓም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም+ ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ አቢያህ+ ነገሠ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “መንግሥታትን።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “የሯጮቹ።”