ሁለተኛ ዜና መዋዕል 13:1-22

  • አቢያህ በይሁዳ ላይ ነገሠ (1-22)

    • አቢያህ ኢዮርብዓምን ድል አደረገ (3-20)

13  ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በ18ኛው ዓመት አቢያህ በይሁዳ ላይ ነገሠ።+  እሱም በኢየሩሳሌም ለሦስት ዓመት ገዛ። የእናቱ ስም ሚካያህ*+ ነበር፤ እሷም የጊብዓዊው+ የዑሪኤል ልጅ ነበረች። በአቢያህና በኢዮርብዓም መካከልም ጦርነት ነበር።+  በመሆኑም አቢያህ 400,000 የሠለጠኑ* ኃያላን ተዋጊዎችን ያቀፈ ሠራዊት ይዞ ዘመተ።+ ኢዮርብዓምም 800,000 የሠለጠኑ* ኃያላን ተዋጊዎችን አስከትሎ እሱን ለመግጠም ተሰለፈ።  አቢያህ በኤፍሬም ተራራማ ክልል በሚገኘው በጸማራይም ተራራ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ፦ “ኢዮርብዓምና እስራኤላውያን ሁሉ፣ ስሙኝ።  የእስራኤል አምላክ ይሖዋ፣ ዳዊትና ልጆቹ+ በእስራኤል ላይ ለዘላለም እንዲነግሡ በጨው ቃል ኪዳን*+ መንግሥት እንደሰጣቸው አታውቁም?+  የዳዊት ልጅ የሰለሞን አገልጋይ የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም+ ግን ተነስቶ በጌታው ላይ ዓመፀ።+  ሥራ ፈት የሆኑ የማይረቡ ሰዎችም ወደ እሱ ተሰበሰቡ። የሰለሞን ልጅ ሮብዓም ለጋ ወጣት በነበረበትና ልቡ በቀላሉ ይሸበር በነበረበት ጊዜም በእሱ ላይ በረቱበት፤ ሊቋቋማቸውም አልቻለም።  “አሁንም እናንተ እጅግ ብዙ ስለሆናችሁና ኢዮርብዓም አማልክት አድርጎ የሠራላችሁን የወርቅ ጥጃዎች+ ስለያዛችሁ በዳዊት ልጆች እጅ ያለውን የይሖዋን መንግሥት መቋቋም እንደምትችሉ ተሰምቷችኋል።  የአሮን ዘሮች የሆኑትን የይሖዋን ካህናትና ሌዋውያንን አላባረራችሁም?+ ደግሞስ እንደ ሌሎቹ አገሮች ሕዝቦች የራሳችሁን ካህናት አልሾማችሁም?+ አንድ ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ይዞ የሚመጣ ማንኛውም ሰው አማልክት ላልሆኑት ጣዖቶች ካህን መሆን ይችላል። 10  እኛ ግን አምላካችን ይሖዋ ነው፤+ እሱንም አልተውነውም፤ የአሮን ዘሮች የሆኑት ካህናት ይሖዋን እያገለገሉ ሲሆን ሌዋውያንም በሥራው ይረዷቸዋል። 11  በየጠዋቱና በየማታው+ ለይሖዋ የሚቃጠል መባ እንዲሁም ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን+ ያቀርባሉ፤ የሚነባበረውም ዳቦ*+ ከንጹሕ ወርቅ በተሠራው ጠረጴዛ ላይ ይቀመጣል፤ የወርቁን መቅረዝና+ መብራቶቹን በየማታው ያበራሉ፤+ ምክንያቱም እኛ በአምላካችን በይሖዋ ፊት ያለብንን ኃላፊነት እየተወጣን ነው፤ እናንተ ግን እሱን ትታችሁታል። 12  እነሆ፣ እውነተኛው አምላክ ከእኛ ጋር ነው፤ እሱም በእናንተ ላይ ጦርነት መታወጁን የሚያመለክት ድምፅ ለማሰማት መለከት ከያዙ ካህናቱ ጋር ሆኖ እየመራን ነው። የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ስለማይሳካላችሁ ከአባቶቻችሁ አምላክ ከይሖዋ ጋር አትዋጉ።”+ 13  ኢዮርብዓም ግን ከበስተ ጀርባቸው አድፍጠው ጥቃት የሚሰነዝሩ ተዋጊዎችን ላከ፤ ዋናው ሠራዊት ከፊት፣ ያደፈጡትም ተዋጊዎች ከበስተ ጀርባ ይሁዳን እንዲገጥሙ አደረገ። 14  የይሁዳ ሰዎች ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከፊትና ከኋላ መከበባቸውን አዩ። በዚህ ጊዜ ወደ ይሖዋ ጮኹ፤+ ካህናቱም መለከቶቹን በኃይል ነፉ። 15  የይሁዳ ሰዎች ቀረርቶ አሰሙ፤ የይሁዳ ሰዎች ቀረርቶ ባሰሙ ጊዜም እውነተኛው አምላክ ኢዮርብዓምንና እስራኤላውያንን ሁሉ በአቢያህና በይሁዳ ፊት ድል አደረጋቸው። 16  እስራኤላውያን ከይሁዳ ፊት ሸሹ፤ አምላክም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። 17  አቢያህና ሕዝቡም ፈጇቸው፤ ከእስራኤላውያንም መካከል 500,000 የሠለጠኑ ተዋጊዎች* ተገደሉ። 18  በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሰዎች ተዋረዱ፤ የይሁዳ ሰዎች ግን በአባቶቻቸው አምላክ በይሖዋ በመታመናቸው* ድል ነሱ።+ 19  አቢያህ ኢዮርብዓምን አሳደደው፤ ከተሞቹን ይኸውም ቤቴልንና+ በሥሯ* ያሉትን ከተሞች፣ የሻናንና በሥሯ ያሉትን ከተሞች እንዲሁም ኤፍራይንንና+ በሥሯ ያሉትን ከተሞች ወሰደበት። 20  ኢዮርብዓምም በአቢያህ ዘመን እንደገና ሊያንሰራራ አልቻለም፤ ከዚያም ይሖዋ ስለቀሰፈው ሞተ።+ 21  አቢያህ ግን እየበረታ ሄደ። ከጊዜ በኋላም 14 ሚስቶችን+ አግብቶ 22 ወንዶች ልጆችና 16 ሴቶች ልጆች ወለደ። 22  የቀረው የአቢያህ ታሪክ፣ የሠራውና የተናገረው ነገር ሁሉ በነቢዩ ኢዶ ጽሑፎች* ላይ ሰፍሯል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

1ነገ 15:2 እና 2ዜና 11:20-22 ላይ ማአካ ተብላም ተጠርታለች።
ቃል በቃል “የተመረጡ።”
ቃል በቃል “የተመረጡ።”
ዘላቂና የማይለወጥ ቃል ኪዳንን ያመለክታል።
ገጸ ኅብስቱን ያመለክታል።
ቃል በቃል “የተመረጡ ተዋጊዎች።”
ቃል በቃል “በመደገፋቸው።”
ወይም “በዙሪያዋ።”
ወይም “ዘገባ፤ ሐተታ።”