ሁለተኛ ዜና መዋዕል 16:1-14
16 አሳ በነገሠ በ36ኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ+ በይሁዳ ላይ ዘመተ፤ እሱም ማንም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ እንዳይገባና እንዳይወጣ*+ ለማድረግ ራማን+ መገንባት* ጀመረ።
2 በዚህ ጊዜ አሳ ከይሖዋ ቤትና ከንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤቶች ብርና ወርቅ አውጥቶ+ በደማስቆ ወደሚገኘው የሶርያ ንጉሥ ወደ ቤንሃዳድ+ እንዲህ ሲል ላከ፦
3 “በእኔና በአንተ እንዲሁም በአባቴና በአባትህ መካከል ውል* አለ። እኔ ብርና ወርቅ ልኬልሃለሁ። ስለዚህ ና፣ የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ከእኔ እንዲርቅ ከእሱ ጋር የገባኸውን ውል* አፍርስ።”
4 ቤንሃዳድ የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ የጦር ሠራዊቱን አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ፤ እነሱም ኢዮንን፣+ ዳንን፣+ አቤልማይምን እና በንፍታሌም+ ከተሞች ውስጥ ያሉትን የማከማቻ ስፍራዎች ሁሉ መቱ።
5 ባኦስም ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ ራማን መገንባቱን* አቆመ፤ ሥራውንም አቋረጠ።
6 ከዚያም ንጉሡ አሳ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ይዞ ሄደ፤ እነሱም ባኦስ እየገነባባቸው የነበሩትን+ የራማን+ ድንጋዮችና ሳንቃዎች አጋዙ፤ እሱም በድንጋዮቹና በሳንቃዎቹ ጌባንና+ ምጽጳን+ ገነባ።*
7 በዚህ ጊዜ ባለ ራእዩ ሃናኒ+ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “በአምላክህ በይሖዋ ከመታመን* ይልቅ በሶርያ ንጉሥ ስለታመንክ* የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት ከእጅህ አምልጧል።+
8 ኢትዮጵያውያንና ሊቢያውያን ብዙ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ያሏቸው ታላቅ ሠራዊት አልነበሩም? ይሁንና በይሖዋ በመታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው።+
9 አዎ፣ በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች*+ ብርታቱን ያሳይ ዘንድ* የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ።+ በዚህ ረገድ የሞኝነት ድርጊት ፈጽመሃል፤ ከእንግዲህ ወዲያ ጦርነት አይለይህም።”+
10 ሆኖም አሳ በባለ ራእዩ ተቆጣ፤ በዚህ ጉዳይ በጣም ስለተናደደበትም እስር ቤት* አስገባው። በዚያ ወቅት አሳ በሌሎች ሰዎችም ላይ በደል መፈጸም ጀመረ።
11 ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለው የአሳ ታሪክ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል።+
12 አሳ በ39ኛው የግዛት ዘመኑ እግሩን ታመመ፤ ሕመሙም ጠናበት፤ ታሞ ሳለም እንኳ የባለ መድኃኒቶችን እንጂ የይሖዋን እርዳታ አልፈለገም።
13 በመጨረሻም አሳ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤+ በ41ኛው የግዛት ዘመኑም ሞተ።
14 እነሱም በዳዊት ከተማ+ ለራሱ ባስቆፈረው ታላቅ የመቃብር ቦታ ቀበሩት፤ የበለሳን ዘይት እንዲሁም ከተለያዩ ቅመሞች የተዘጋጀ ልዩ ቅባት በሞላበት ቃሬዛ ላይ አኖሩት።+ በተጨማሪም ለክብሩ ታላቅ እሳት አነደዱለት።*
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ማጠናከር፤ መልሶ መገንባት።”
^ ወይም “ከይሁዳ ንጉሥ ከአሳ ግዛት ማንም እንዳይወጣ ወይም ማንም ወደዚያ እንዳይገባ።”
^ ወይም “ቤተ መንግሥት።”
^ ወይም “ቃል ኪዳን።”
^ ወይም “ቃል ኪዳን።”
^ ወይም “ማጠናከሩን፤ መልሶ መገንባቱን።”
^ ወይም “አጠናከረ፤ መልሶ ገነባ።”
^ ቃል በቃል “ከመደገፍ።”
^ ቃል በቃል “ስለተደገፍክ።”
^ ወይም “ያዘነበሉትን ሰዎች ይረዳ ዘንድ።”
^ ወይም “ሙሉ በሙሉ ለእሱ ላደሩ ሰዎች።”
^ ቃል በቃል “የእግር ግንድ ቤት ውስጥ።”
^ ያነደዱት የአሳን አስከሬን ሳይሆን የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን እንደሆነ ግልጽ ነው።