ሁለተኛ ዜና መዋዕል 17:1-19

  • ኢዮሳፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ (1-6)

  • የማስተማር ዘመቻ (7-9)

  • የኢዮሳፍጥ የጦር ኃይል (10-19)

17  ልጁ ኢዮሳፍጥም+ በምትኩ ነገሠ፤ በእስራኤልም ላይ ሥልጣኑን አጠናከረ።  በይሁዳ ባሉት የተመሸጉ ከተሞች ሁሉ የጦር ሠራዊት አሰፈረ፤ በይሁዳ ምድርና አባቱ አሳ በያዛቸው በኤፍሬም ከተሞችም የጦር ሰፈሮች አቋቋመ።+  ኢዮሳፍጥ፣ በቀድሞዎቹ ዘመናት አባቱ ዳዊት የሄደበትን መንገድ በመከተሉና+ ባአልን ባለመፈለጉ ይሖዋ ከእሱ ጋር ነበር።  የእስራኤልን ልማድ ከመከተል ይልቅ+ የአባቱን አምላክ ፈልጓል፤+ ትእዛዙንም ተከትሏል።*  ይሖዋ መንግሥቱን በእጁ አጸናለት፤+ የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ለኢዮሳፍጥ ስጦታ ያመጡለት ነበር፤ እሱም ብዙ ሀብትና ታላቅ ክብር አገኘ።+  ልቡም የይሖዋን መንገዶች በድፍረት ተከተለ፤ ደግሞም ከፍ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎችና የማምለኪያ ግንዶቹን* ከይሁዳ አስወገደ።+  በነገሠ በሦስተኛው ዓመት በይሁዳ ከተሞች እንዲያስተምሩ መኳንንቱን ይኸውም ቤንሃይልን፣ አብድዩን፣ ዘካርያስን፣ ናትናኤልንና ሚካያህን አስጠራቸው።  ከእነሱ ጋር ሌዋውያኑ ሸማያህ፣ ነታንያህ፣ ዘባድያህ፣ አሳሄል፣ ሸሚራሞት፣ የሆናታን፣ አዶንያስ፣ ጦቢያህ እና ቶብአዶኒያህ ይገኙ ነበር፤ ካህናቱ ኤሊሻማ እና ኢዮራምም አብረዋቸው ነበሩ።+  እነሱም በይሁዳ ማስተማር ጀመሩ፤ የይሖዋን ሕግ መጽሐፍም ይዘው ነበር፤+ በይሁዳ ከተሞች ሁሉ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር። 10  ይሖዋም በይሁዳ ዙሪያ በሚገኙ አገሮች ባሉት መንግሥታት ሁሉ ላይ ፍርሃት ለቆባቸው ስለነበር ከኢዮሳፍጥ ጋር አልተዋጉም። 11  ፍልስጤማውያንም ለኢዮሳፍጥ ስጦታ አመጡለት፤ ገንዘብም ገበሩለት። ዓረቦች ከመንጎቻቸው መካከል 7,700 አውራ በጎችንና 7,700 አውራ ፍየሎችን አመጡለት። 12  ኢዮሳፍጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ ሄደ፤+ በይሁዳም ምሽጎችንና+ የማከማቻ ከተሞችን+ መገንባቱን ተያያዘው። 13  በይሁዳ ከተሞች መጠነ ሰፊ የሆነ ሥራ አከናወነ፤ በኢየሩሳሌምም ኃያላን ተዋጊዎች የሆኑ ወታደሮች ነበሩት። 14  እነዚህ ሰዎች በየአባቶቻቸው ቤት ተመድበው ነበር፦ ከይሁዳ የሺህ አለቆች መካከል አለቃው አድናህ የነበረ ሲሆን ከእሱ ጋር 300,000 ኃያላን ተዋጊዎች ነበሩ።+ 15  ከእሱ ሥር ደግሞ የሆሃናን የተባለ አለቃ የነበረ ሲሆን ከእሱም ጋር 280,000 ሰዎች ነበሩ። 16  ደግሞም ከእሱ ሥር ለይሖዋ አገልግሎት ራሱን በፈቃደኝነት ያቀረበው የዚክሪ ልጅ አማስያህ የነበረ ሲሆን ከእሱም ጋር 200,000 ኃያላን ተዋጊዎች ነበሩ። 17  ከቢንያምም+ ወገን ኃያል ተዋጊ የሆነው ኤሊያዳ የነበረ ሲሆን ከእሱም ጋር ቀስትና ጋሻ የታጠቁ 200,000 ሰዎች ነበሩ።+ 18  ከእሱም ሥር የሆዛባድ የነበረ ሲሆን ከእሱም ጋር ለውጊያ የታጠቁ 180,000 ሰዎች ነበሩ። 19  እነዚህ ንጉሡ በመላው ይሁዳ በተመሸጉ ከተሞች+ ውስጥ ካስቀመጣቸው ሌላ ንጉሡን ያገለግሉ የነበሩ ሰዎች ናቸው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “በትእዛዙም ተመላልሷል።”