ሁለተኛ ዜና መዋዕል 24:1-27

  • የኢዮዓስ አገዛዝ (1-3)

  • ኢዮዓስ ቤተ መቅደሱን አደሰ (4-14)

  • ኢዮዓስ ክህደት ፈጸመ (15-22)

  • ኢዮዓስ ተገደለ (23-27)

24  ኢዮዓስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር፤+ በኢየሩሳሌም ሆኖ 40 ዓመት ገዛ። እናቱ ጺብያ የተባለች የቤርሳቤህ+ ተወላጅ ነበረች።  ኢዮዓስ ካህኑ ዮዳሄ በነበረበት ዘመን ሁሉ በይሖዋ ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ።+  ዮዳሄ ሁለት ሚስቶች መረጠለት፤ እሱም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ።  ከጊዜ በኋላ ኢዮዓስ የይሖዋን ቤት ለማደስ ልባዊ ፍላጎት አደረበት።+  በመሆኑም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ሄዳችሁ የአምላካችሁን ቤት በየዓመቱ ለማደስ ከእስራኤል ሁሉ ገንዘብ ሰብስቡ፤+ እናንተም በአስቸኳይ ይህንኑ አድርጉ።” ሌዋውያኑ ግን አፋጣኝ እርምጃ አልወሰዱም።+  ስለዚህ ንጉሡ የካህናቱን አለቃ ዮዳሄን ጠርቶ እንዲህ አለው፦+ “የይሖዋ አገልጋይ የሆነው ሙሴ ያዘዘውንና+ ለምሥክሩ ድንኳን+ የሚውለውን የተቀደሰ ግብር ይኸውም የእስራኤልን ጉባኤ የተቀደሰ ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም እንዲያመጡ ሌዋውያኑን ያላዘዝካቸው ለምንድን ነው?  የዚያች ክፉ ሴት የጎቶልያ+ ወንዶች ልጆች ወደ እውነተኛው አምላክ ቤት ሰብረው በመግባት+ በይሖዋ ቤት የነበሩትን የተቀደሱ ዕቃዎች በሙሉ ለባአል አገልግሎት እንዳዋሉ ታውቃለህ።”  ከዚያም በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ሣጥን+ ተሠርቶ በይሖዋ ቤት በር አጠገብ በውጭ በኩል ተቀመጠ።+  ከዚህ በኋላ የእውነተኛው አምላክ አገልጋይ ሙሴ በምድረ በዳ ሳሉ በእስራኤል ላይ የጣለው የተቀደሰ ግብር+ ለይሖዋ እንዲሰጥ በመላው ይሁዳና ኢየሩሳሌም አዋጅ ተነገረ። 10  መኳንንቱ ሁሉና ሕዝቡ ሁሉ ሐሴት አደረጉ፤+ ሣጥኑ እስኪሞላም* ድረስ መዋጮ እያመጡ ይጨምሩ ነበር። 11  ሌዋውያኑ ሣጥኑን ወደ ንጉሡ በሚያመጡበትና በውስጡ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ የንጉሡ ጸሐፊና የካህናቱ አለቃ ሹም መጥተው ሣጥኑን ካጋቡ+ በኋላ ወደ ቦታው ይመልሱት ነበር። በየዕለቱ እንዲህ ያደርጉ ነበር፤ እጅግ ብዙ ገንዘብም ሰበሰቡ። 12  ከዚያም ንጉሡና ዮዳሄ ገንዘቡን በይሖዋ ቤት አገልግሎት የሚከናወነውን ሥራ ለሚቆጣጠሩት ሰዎች ይሰጧቸው ነበር፤ እነሱ ደግሞ የይሖዋን ቤት ለማደስ+ ድንጋይ ጠራቢዎችንና የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችን እንዲሁም የይሖዋን ቤት ለመጠገን የብረትና የመዳብ ሠራተኞችን ይቀጥሩ ነበር። 13  ሥራውን የሚቆጣጠሩት ሰዎችም ሥራው እንዲጀመር አደረጉ፤ የጥገናውም ሥራ በእነሱ አመራር ሥር ተፋጠነ፤ የእውነተኛውን አምላክ ቤት በማደስ ወደ ቀድሞው ሁኔታ መለሱት፤ ቤቱንም አጠናከሩት። 14  ሥራውን እንደጨረሱም የተረፈውን ገንዘብ ወደ ንጉሡና ወደ ዮዳሄ አመጡ፤ እነሱም ለይሖዋ ቤት የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን፣ ለአገልግሎትና መባ ለማቅረብ የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን፣ ጽዋዎችን እንዲሁም የወርቅና የብር ዕቃዎችን ለመሥራት ተጠቀሙበት።+ ዮዳሄ በነበረበት ዘመን ሁሉ በይሖዋ ቤት የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን+ ዘወትር ያቀርቡ ነበር። 15  ዮዳሄ ሸምግሎና ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ በሞተ ጊዜ ዕድሜው 130 ዓመት ነበር። 16  ከእውነተኛው አምላክና ከአምላክ ቤት ጋር በተያያዘ በእስራኤል መልካም ነገር ስላደረገ+ በዳዊት ከተማ ከነገሥታት ጋር ቀበሩት።+ 17  ከዮዳሄ ሞት በኋላ የይሁዳ መኳንንት መጥተው ንጉሡን እጅ ነሱ፤ ንጉሡም እነሱ ያሉትን ሰማ። 18  እነሱም የአባቶቻቸውን አምላክ የይሖዋን ቤት ትተው የማምለኪያ ግንዶችንና* ጣዖቶችን ማገልገል ጀመሩ፤ ከፈጸሙት በደል የተነሳ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ የአምላክ ቁጣ መጣ።* 19  ይሖዋ ወደ እሱ እንዲመልሷቸው ነቢያትን ይልክላቸው ነበር፤ እነሱም ያስጠነቅቋቸው* ነበር፤ ሕዝቡ ግን ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም።+ 20  የአምላክ መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ+ ልጅ በዘካርያስ ላይ ወረደ፤ እሱም በሕዝቡ ፊት ከፍ ያለ ቦታ ላይ ቆሞ እንዲህ አላቸው፦ “እውነተኛው አምላክ እንዲህ ይላል፦ ‘የይሖዋን ትእዛዛት የምትተላለፉት ለምንድን ነው? አይሳካላችሁም! ይሖዋን ስለተዋችሁ እሱም ይተዋችኋል።’”+ 21  እነሱ ግን በእሱ ላይ አሴሩ፤+ ንጉሡም በሰጠው ትእዛዝ መሠረት በይሖዋ ቤት ግቢ ውስጥ በድንጋይ ወገሩት።+ 22  ንጉሥ ኢዮዓስ፣ አባቱ* ዮዳሄ ያሳየውን ታማኝ ፍቅር አላሰበም፤ ልጁንም ገደለው፤ እሱም ሊሞት ሲል “ይሖዋ ይየው፤ የእጅህንም ይስጥህ” አለ።+ 23  በዓመቱ መጀመሪያ ላይ የሶርያ ሠራዊት በኢዮዓስ ላይ ዘመተ፤ እነሱም ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ወረሩ።+ ከዚያም የሕዝቡን መኳንንት ሁሉ አጠፉ፤+ የማረኩትንም ሁሉ ወደ ደማስቆ ንጉሥ ላኩ። 24  ወራሪው የሶርያ ሠራዊት አነስተኛ ቁጥር የነበረው ቢሆንም ይሖዋ እጅግ ብዙ የሆነውን ሠራዊት በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤+ ይህም የሆነው የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን በመተዋቸው ነው፤ እነሱም* በኢዮዓስ ላይ የተላለፈውን ፍርድ ፈጸሙ። 25  እነሱም ጥለውት በሄዱ ጊዜ (ክፉኛ አቁስለውት* ነበርና) የገዛ አገልጋዮቹ የካህኑን የዮዳሄን ልጆች* ደም በማፍሰሱ አሴሩበት።+ አልጋው ላይ እንዳለ ገደሉት።+ ከሞተም በኋላ በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤+ በነገሥታቱ የመቃብር ስፍራ ግን አልቀበሩትም።+ 26  በእሱ ላይ ያሴሩት+ የአሞናዊቷ የሺምዓት ልጅ ዛባድና የሞዓባዊቷ የሺምሪት ልጅ የሆዛባድ ነበሩ። 27  ስለ ወንዶች ልጆቹ፣ በእሱ ላይ ስለተላለፉት በርካታ የፍርድ መልእክቶችና+ የእውነተኛውን አምላክ ቤት ስለማደሱ*+ የሚገልጸው ታሪክ ሁሉ በነገሥታቱ መጽሐፍ ዘገባዎች* ላይ ሰፍሯል። በእሱም ምትክ ልጁ አሜስያስ ነገሠ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ሁሉም እስኪሰጡ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ቁጣ ሆነ።”
ወይም “ይመሠክሩባቸው።”
የዘካርያስን አባት ያመለክታል።
የሶርያን ሰዎች ያመለክታል።
ወይም “በጠና ታሞ።”
ወይም “ወንድ ልጅ።” በብዙ ቁጥር የተገለጸው ልጁ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ለማሳየት ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ስለመመሥረቱ።”
ወይም “ሐተታ፤ ማብራሪያ።”