ሁለተኛ ዜና መዋዕል 5:1-14

  • ለቤተ መቅደሱ ምረቃ የተደረገው ዝግጅት (1-14)

    • ታቦቱ ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ (2-10)

5  በዚህ ሁኔታ ሰለሞን ከይሖዋ ቤት ጋር በተያያዘ መሥራት የሚገባውን ሥራ በሙሉ ሠርቶ አጠናቀቀ።+ ከዚያም ሰለሞን አባቱ ዳዊት የቀደሳቸውን ነገሮች ወደዚያ አስገባ፤+ ብሩን፣ ወርቁንና ዕቃዎቹን በሙሉ በእውነተኛው አምላክ ቤት ግምጃ ቤቶች ውስጥ አስቀመጠ።+  በዚህ ጊዜ ሰለሞን የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የነገዶቹን መሪዎች ሁሉና የእስራኤልን የአባቶች ቤት አለቆች ሰበሰበ። እነሱም የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ማለትም ከጽዮን+ ለማምጣት ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።+  የእስራኤል ሰዎች በሙሉ በሰባተኛው ወር በሚከበረው በዓል* ላይ በንጉሡ ፊት ተሰበሰቡ።+  የእስራኤል ሽማግሌዎችም በሙሉ መጡ፤ ሌዋውያኑም ታቦቱን አነሱ።+  ታቦቱን፣ የመገናኛ ድንኳኑንና+ በድንኳኑ ውስጥ የነበሩትን ቅዱስ ዕቃዎች በሙሉ አመጡ። እነዚህንም ያመጡት ካህናቱና ሌዋውያኑ* ናቸው።  ንጉሥ ሰለሞንና ወደ እሱ እንዲመጣ የተጠራው መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ታቦቱ ፊት ነበሩ። ከብዛታቸው የተነሳ ሊቆጠሩ የማይችሉ ብዙ በጎችና ከብቶች መሥዋዕት ሆነው ቀረቡ።+  ከዚያም ካህናቱ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት አምጥተው ቦታው ላይ ማለትም በቤቱ ውስጠኛ ክፍል ይኸውም በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ከኪሩቦቹ ክንፎች በታች አስቀመጡት።+  የኪሩቦቹ ክንፎች ታቦቱ ባለበት ቦታ ላይ ተዘርግተው ስለነበር ኪሩቦቹ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን+ ከላይ ሸፍነዋቸው ነበር።  መሎጊያዎቹ ረጅም ስለነበሩ የመሎጊያዎቹን ጫፎች ከውስጠኛው ክፍል ፊት ለፊት ባለው በቅድስቱ ውስጥ ሆኖ ማየት ይቻል ነበር፤ ከውጭ ግን አይታዩም ነበር። እስከ ዛሬም ድረስ እዚያው ይገኛሉ። 10  የእስራኤል ሰዎች ከግብፅ ምድር ሲወጡ+ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን+ በገባበት ጊዜ ሙሴ በኮሬብ ታቦቱ ውስጥ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች+ በስተቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም። 11  ካህናቱ ከቅዱሱ ስፍራ በወጡ ጊዜ (በዚያ የተገኙት ካህናት ሁሉ ከየትኛውም ምድብ+ ይሁኑ ራሳቸውን ቀድሰው ነበር)፣+ 12  ከአሳፍ፣+ ከሄማን፣+ ከየዱቱን+ እንዲሁም ከወንዶች ልጆቻቸውና ከወንድሞቻቸው ወገን የሆኑት ሌዋውያን ዘማሪዎች+ ሁሉ ጥራት ያለው ልብስ ለብሰውና ሲምባል፣* ባለ አውታር መሣሪያዎችና በገና ይዘው ነበር፤ ከመሠዊያው በስተ ምሥራቅ ቆመው የነበረ ሲሆን ከእነሱም ጋር መለከት የሚነፉ 120 ካህናት ነበሩ።+ 13  መለከት ነፊዎቹና ዘማሪዎቹ በኅብረት ይሖዋን ባወደሱና ባመሰገኑ ጊዜ እንዲሁም “እሱ ጥሩ ነውና፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል”+ እያሉ ይሖዋን በማወደስ የመለከቱን፣ የሲምባሉንና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ድምፅ ባሰሙ ጊዜ ቤቱ ይኸውም የይሖዋ ቤት በደመና ተሞልቶ ነበር።+ 14  የይሖዋ ክብር የእውነተኛውን አምላክ ቤት ሞልቶት ስለነበር ካህናቱ ከደመናው የተነሳ በዚያ ቆመው ማገልገል አልቻሉም።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

የዳስ በዓልን ያመለክታል።
ወይም “ሌዋውያኑ ካህናት።”
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል፣ እርስ በርሱ ሲጋጭ ኃይለኛ ድምፅ የሚያወጣን ክብ ቅርጽ ያለው ከብረት የተሠራ የሙዚቃ መሣሪያ ያመለክታል።