ሁለተኛ ዜና መዋዕል 9:1-31

  • የሳባ ንግሥት ሰለሞንን ልትጠይቀው መጣች (1-12)

  • የሰለሞን ሀብት (13-28)

  • ሰለሞን ሞተ (29-31)

9  የሳባ ንግሥት+ ስለ ሰለሞን ዝና በሰማች ጊዜ አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች* ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች። እሷም እጅግ ታላቅ አጀብ አስከትላ እንዲሁም የበለሳን ዘይት፣ በጣም ብዙ ወርቅና+ የከበሩ ድንጋዮች በግመል አስጭና ነበር። ወደ ሰለሞንም ገብታ በልቧ ያለውን ሁሉ ነገረችው።+  ሰለሞንም ጥያቄዎቿን ሁሉ መለሰላት። ሰለሞን ሊያብራራላት ያልቻለው* ምንም ነገር አልነበረም።  የሳባ ንግሥት የሰለሞንን ጥበብና+ የሠራውን ቤት+ ስትመለከት፣  በገበታው ላይ የሚቀርበውን ምግብ፣+ የአገልጋዮቹን አቀማመጥ፣ አስተናጋጆቹ በማዕድ ላይ የሚያስተናግዱበትን መንገድና አለባበሳቸውን፣ መጠጥ አሳላፊዎቹንና አለባበሳቸውን እንዲሁም በይሖዋ ቤት ዘወትር የሚያቀርባቸውን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች+ ስታይ በመገረም ፈዛ ቀረች።*  በመሆኑም ንጉሡን እንዲህ አለችው፦ “ስላከናወንካቸው ነገሮችና* ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ነገር እውነት ነው።  ይሁንና እኔ ራሴ መጥቼ በገዛ ዓይኔ እስከማይ ድረስ የተነገረኝን ነገር አላመንኩም ነበር።+ እንደዚያም ሆኖ ታላቅ ከሆነው ጥበብህ ግማሹ እንኳ አልተነገረኝም!+ እኔ ስለ አንተ ከሰማሁት እጅግ የላቅክ ነህ።+  አብረውህ ያሉ ሰዎች ደስተኞች ናቸው፤ ዘወትር በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙት አገልጋዮችህም እጅግ ደስተኞች ናቸው!  ለአምላክህ ለይሖዋ ንጉሥ ሆነህ እንድትገዛ አንተን በዙፋኑ ላይ በማስቀመጥ በአንተ ደስ የተሰኘው አምላክህ ይሖዋ ይወደስ። አምላክህ እስራኤልን ስለወደደውና+ ለዘላለም ያጸናው ዘንድ ስለፈለገ፣ ፍትሕንና ጽድቅን እንድታሰፍን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ ሾሞሃል።”  ከዚያም ለንጉሡ 120 ታላንት* ወርቅ+ እንዲሁም እጅግ ብዙ የበለሳን ዘይትና የከበሩ ድንጋዮችን ሰጠችው። የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰለሞን የሰጠችውን ያህል የበለሳን ዘይት ከዚያ በኋላ መጥቶ አያውቅም።+ 10  ከዚህ በተጨማሪ ከኦፊር ወርቅ+ ጭነው የመጡት የኪራም አገልጋዮችና የሰለሞን አገልጋዮች የሰንደል ዛፍ ሳንቃዎችና የከበሩ ድንጋዮች አመጡ።+ 11  ንጉሡም ከሰንደል ዛፍ ሳንቃዎቹ ለይሖዋ ቤትና ለንጉሡ ቤት*+ ደረጃዎችን+ እንዲሁም ለዘማሪዎቹ የሚሆኑ በገናዎችንና ሌሎች ባለ አውታር መሣሪያዎችን ሠራ።+ ከዚያ በፊት እንዲህ ያለ ነገር በይሁዳ ምድር ታይቶ አያውቅም። 12  ንጉሥ ሰለሞን ደግሞ የሳባ ንግሥት የፈለገችውንና የጠየቀችውን ነገር ሁሉ፣ ካመጣችለት ስጦታ የሚበልጥ ነገር ሰጣት።* ከዚያም ተነስታ አገልጋዮቿን በማስከተል ወደ አገሯ ተመለሰች።+ 13  ሰለሞን በየዓመቱ 666 ታላንት ወርቅ ይመጣለት ነበር፤+ 14  ይህም ነጋዴዎችና ሻጮች የሚያስገቡትን ገቢ እንዲሁም የዓረብ ነገሥታት ሁሉና አገረ ገዢዎች ለሰለሞን የሚያመጡትን ወርቅና ብር ሳይጨምር ነው።+ 15  ንጉሥ ሰለሞን ከቅይጥ ወርቅ 200 ትላልቅ ጋሻዎችን ሠራ፤+ (እያንዳንዱ ጋሻ በ600 ሰቅል* ቅይጥ ወርቅ ተለብጦ ነበር)፤+ 16  እንዲሁም ከቅይጥ ወርቅ 300 ትናንሽ ጋሻዎችን* ሠራ፤ (እያንዳንዱ ትንሽ ጋሻ በሦስት ምናን* ወርቅ ተለብጦ ነበር)። ከዚያም ንጉሡ የሊባኖስ ደን በተባለው ቤት አስቀመጣቸው።+ 17  በተጨማሪም ንጉሡ ከዝሆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን ሠርቶ በንጹሕ ወርቅ ለበጠው።+ 18  ወደ ዙፋኑ የሚያስወጡ ስድስት ደረጃዎች ነበሩ፤ ከዙፋኑም ጋር የተያያዘ ከወርቅ የተሠራ የእግር ማሳረፊያ ነበር፤ መቀመጫውም በጎንና በጎኑ የእጅ መደገፊያዎች ያሉት ሲሆን ከእጅ መደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች+ ቆመው ነበር። 19  በስድስቱ ደረጃዎች ዳርና ዳር አንድ አንድ አንበሳ፣ በአጠቃላይ 12 አንበሶች+ ቆመው ነበር። እንዲህ ያለ ዙፋን የሠራ አንድም ሌላ መንግሥት አልነበረም። 20  የንጉሥ ሰለሞን የመጠጫ ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ የሊባኖስ ደን በተባለው ቤት የነበሩት ዕቃዎችም በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ። ከብር የተሠራ ምንም ነገር አልነበረም፤ በሰለሞን ዘመን ብር እንደ ተራ ነገር ይቆጠር ነበር።+ 21  የኪራም+ አገልጋዮች የሰለሞንን መርከቦች እየነዱ ወደ ተርሴስ+ ይጓዙ ነበር። እነዚህ የተርሴስ መርከቦች በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብር፣ የዝሆን ጥርስ፣+ ጦጣና ጣዎስ* ጭነው ይመጡ ነበር። 22  በመሆኑም ንጉሥ ሰለሞን በብልጽግናና በጥበብ ምድር ላይ ካሉ ሌሎች ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር።+ 23  የምድር ነገሥታትም ሁሉ እውነተኛው አምላክ በሰለሞን ልብ ውስጥ ያኖረውን ጥበብ ይሰሙ ዘንድ ከእሱ ጋር ለመገናኘት ይጓጉ ነበር።*+ 24  ወደ እሱ የሚመጡትም ሰዎች በየዓመቱ የብር ዕቃዎች፣ የወርቅ ዕቃዎች፣ ልብሶች፣+ የጦር ትጥቆች፣ የበለሳን ዘይት፣ ፈረሶችና በቅሎዎች ስጦታ አድርገው ያመጡ ነበር። 25  ሰለሞንም ለፈረሶቹ የሚሆኑ 4,000 ጋጣዎች፣ ሠረገሎችና 12,000 ፈረሶች* ነበሩት፤+ እነሱንም በሠረገላ ከተሞችና በኢየሩሳሌም በንጉሡ አቅራቢያ አኖራቸው።+ 26  እሱም ከወንዙ* አንስቶ እስከ ፍልስጤማውያን ምድርና እስከ ግብፅ ወሰን ድረስ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ላይ ገዛ።+ 27  ንጉሡ በኢየሩሳሌም ያለውን ብር ከብዛቱ የተነሳ በየቦታው እንደሚገኝ ድንጋይ አደረገው፤ የአርዘ ሊባኖሱንም ብዛት በሸፌላ እንደሚገኘው የሾላ ዛፍ አደረገው።+ 28  ደግሞም ለሰለሞን ከግብፅና ከሌሎች አገሮች ሁሉ ፈረሶችን ያመጡለት ነበር።+ 29  ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለው የቀረው የሰለሞን ታሪክ+ ነቢዩ ናታን+ ባዘጋጀው ጽሑፍ፣ የሴሎ ሰው የሆነው አኪያህ+ በተናገረው ትንቢትና ባለ ራእዩ ኢዶ+ ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም+ያየው ራእይ በሰፈረበት ዘገባ ላይ ተጽፎ የለም? 30  ሰለሞን በኢየሩሳሌም ሆኖ በመላው እስራኤል ላይ ለ40 ዓመት ገዛ። 31  በመጨረሻም ሰለሞን ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ። በአባቱም በዳዊት ከተማ+ ቀበሩት፤ በእሱም ምትክ ልጁ ሮብዓም ነገሠ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በእንቆቅልሽ።”
ቃል በቃል “ከሰለሞን የተሰወረ።”
ቃል በቃል “በውስጧ መንፈስ አልቀረም።”
ወይም “ስለ ቃሎችህና።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
“ያመጣችለትን ነገር በዋጋ የሚተካከል ስጦታ የሰጣት ሲሆን ተጨማሪ ገጸ በረከትም አበረከተላት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አብዛኛውን ጊዜ ቀስተኞች የሚይዙት ትንሽ ጋሻ።
በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አንድ ምናን 570 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ዥጉርጉር ቀለም ያለው ትልቅ የወፍ ዝርያ። እንግሊዝኛ፣ ፒኮክ።
ቃል በቃል “የእሱን ፊት ይሹ ነበር።”
ወይም “ፈረሰኞች።”
ኤፍራጥስን ያመለክታል።