በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዓት ስንት ነው?

ሰዓት ስንት ነው?

ሰዓት ስንት እንደሆነ ማወቅ ስትፈልግ ምን ታደርጋለህ? የእጅ ሰዓትህን ትመለከት ይሆናል። አንድ ጓደኛህ “ሰዓት ስንት ነው?” ቢልህ ምን ብለህ ትመልስለታለህ? ሰዓቱ ስንት እንደሆነ መናገር የሚቻልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። እንዴት?

እኩለ ቀን ከሆነ አንድ ሰዓት ከሠላሳ ደቂቃ አልፏል እንበል። ስለዚህ ለጓደኛህ ሰዓቱ 7:30 እንደሆነ ልትነግረው ትችላለህ። አሊያም ደግሞ በምትኖርበት አካባቢ የ24 ሰዓት አቆጣጠር ዘዴ የተለመደ ከሆነ ደግሞ ሰዓቱ 13:30 መሆኑን ትናገር ይሆናል። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ይኸው ሰዓት “ለሁለት ተኩል ጉዳይ” ተብሎ ይገለጻል።

መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ፣ በጥንት ዘመን የኖሩ ሰዎች ሰዓቱ ስንት እንደሆነ የሚገልጹት እንዴት እንደነበር ጥያቄ ይፈጠርብህ ይሆናል። ሰዎቹ የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀሙ ነበር። በዕብራይስጥ የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል “ማለዳ፣” “ጠዋት፣” “እኩለ ቀን” እንዲሁም “አመሻሹ ላይ” የሚሉ የጊዜ መግለጫዎችን ይጠቀማል። (ዘፍ. 8:11፤ 19:27፤ ዘዳ. 28:29፤ 1 ነገ. 18:26) አንዳንድ ጊዜ ግን ሰዓቱን ለይቶ የሚጠቅስ አገላለጽ እናገኛለን።

ኢየሱስ ከመወለዱ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት እስራኤላውያን ሌሊቱን በሦስት ክፍለ ሌሊቶች የመከፋፈል ልማድ ነበራቸው። (መዝ. 63:6 ግርጌ) መሳፍንት 7:19 ላይ “በመካከለኛው ክፍለ ሌሊት” የሚል አገላለጽ እናገኛለን። በኢየሱስ ዘመን ግን አይሁዳውያኑ፣ የግሪካውያንንና የሮማውያንን ልማድ በመከተል ሌሊቱን በአራት ክፍለ ሌሊቶች መከፋፈል ጀምረው ነበር።

ወንጌሎች እነዚህን ክፍለ ሌሊቶች የተለያዩ ቦታዎች ላይ ጠቅሰዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በጀልባ ላይ ወደነበሩት ደቀ መዛሙርቱ በውኃ ላይ እየተራመደ የመጣው “በአራተኛው ክፍለ ሌሊት” ነው። (ማቴ. 14:25) ኢየሱስ በተናገረው አንድ ምሳሌ ላይ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰው ሌባ በየትኛው ክፍለ ሌሊት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ ነቅቶ በጠበቀና ቤቱ እንዳይደፈር በተከላከለ ነበር።”—ማቴ. 24:43

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸውም ነበር፦ “ስለዚህ የቤቱ ጌታ፣ በምሽት ይሁን በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ይሁን ከመንጋቱ በፊት፣ መቼ እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ”፤ እዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ አራቱንም ክፍለ ሌሊቶች ጠቅሷል። (ማር. 13:35 ግርጌ) ከእነዚህ ክፍለ ሌሊቶች የመጀመሪያው ማለትም “ምሽት” የተባለው፣ ጀምበር ከጠለቀችበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሦስት ሰዓት ገደማ ያለውን ጊዜ ያመለክታል። “እኩለ ሌሊት” ተብሎ የተጠራው ሁለተኛው ክፍለ ሌሊት ደግሞ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ገደማ ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ያለው ጊዜ ነው። “ዶሮ ሲጮህ” ተብሎ የተገለጸው ሦስተኛው ክፍለ ሌሊት፣ ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ድረስ ያለው ጊዜ ነው። ኢየሱስ በተያዘበት ሌሊት ዶሮ የጮኸው በዚህ ክፍለ ሌሊት ላይ ሳይሆን አይቀርም። (ማር. 14:72) “ከመንጋቱ በፊት” ወይም “ንጋት” የተባለው አራተኛው ክፍለ ሌሊት ደግሞ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ጀምሮ ፀሐይ እስከምትወጣበት ድረስ ያለውን ጊዜ ያመለክታል።

ከዚህ ማየት እንደሚቻለው በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ዛሬ ያሉን የሰዓት መቁጠሪያ መሣሪያዎች ባይኖሯቸውም ከሌሊቱም ሆነ ከቀኑ ስንት ሰዓት እንደሆነ መግለጽ የሚችሉበት የሰዓት አቆጣጠር ዘዴ ነበራቸው።