በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አሳቢነትና ደግነት በማሳየት ይሖዋን ምሰሉ

አሳቢነትና ደግነት በማሳየት ይሖዋን ምሰሉ

“ለተቸገረ ሰው የሚያስብ ደስተኛ ነው።”—መዝ. 41:1

መዝሙሮች፦ 130, 107

1. የአምላክ አገልጋዮች አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር የሚያሳዩት እንዴት ነው?

በመላው ዓለም ያሉት የአምላክ አገልጋዮች እንደ አንድ ቤተሰብ ናቸው፤ ተለይተው የሚታወቁትም በመካከላቸው ባለው ፍቅር ነው። (1 ዮሐ. 4:16, 21) ክርስቲያኖች ለወንድሞቻቸው ሲሉ ከፍተኛ መሥዋዕት የሚከፍሉባቸው ጊዜያት አሉ፤ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ ፍቅራቸውን የሚገልጹት፣ ለወንድሞቻቸው በሚያከናውኗቸው ትናንሽ የደግነት ድርጊቶች እንዲሁም በሚናገሯቸው አሳቢነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት ነው። ለሌሎች ደግነትና አሳቢነት ስናሳይ ‘የተወደድን ልጆቹ በመሆን አምላክን መምሰል’ እንችላለን።—ኤፌ. 5:1

2. ኢየሱስ ፍቅር በማሳየት አምላክን የመሰለው እንዴት ነው?

2 ኢየሱስ አባቱን ፍጹም በሆነ መንገድ መስሏል። “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። . . . እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 11:28, 29) ‘ለተቸገረ ሰው አሳቢነት በማሳየት’ የክርስቶስን ምሳሌ ስንከተል በሰማይ ያለውን አባታችንን ሞገስ እንዲሁም ታላቅ ደስታ እናገኛለን። (መዝ. 41:1) በቤተሰባችንና በጉባኤ ውስጥ እንዲሁም በአገልግሎት ላይ ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት የምንችልባቸውን መንገዶች እስቲ እንመልከት።

ለቤተሰባችሁ አባላት አሳቢነት አሳዩ

3. ባሎች የሚስቶቻቸውን ሁኔታ መረዳታቸው አሳቢነት ለማሳየት የሚያስችላቸው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

3 ባሎች ለቤተሰባቸው አባላት አሳቢነት በማሳየት ረገድ ቀዳሚ መሆን አለባቸው። (ኤፌ. 5:25፤ 6:4) ባሎች ከሚስቶቻቸው ጋር “በእውቀት” እንዲኖሩ ተመክረዋል፤ ይህ አገላለጽ “ለእነሱ አሳቢነት በማሳየት፤ ሁኔታቸውን በመረዳት” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። (1 ጴጥ. 3:7 ግርጌ) የሌሎችን ሁኔታ መረዳት፣ አሳቢነት ለማሳየት ቁልፍ ነው። ለምሳሌ የሚስቱን ሁኔታ የሚረዳ ባል፣ ማሟያ የሆነችው ሚስቱ በብዙ መንገዶች ከእሱ የተለየች ብትሆንም ከእሱ እንደማታንስ ይገነዘባል። (ዘፍ. 2:18) በመሆኑም ስሜቷን ከግምት ያስገባል እንዲሁም በአክብሮት ይይዛታል። በካናዳ የምትኖር አንዲት ሚስት ስለ ባሏ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ በፍጹም ስሜቴን አቅልሎ አይመለከትም፤ ወይም ደግሞ ‘እንዴት እንደዚህ ይሰማሻል?’ አይለኝም። ጥሩ አዳማጭ ነው። ስለ አንድ ጉዳይ ያለኝን አመለካከት ማስተካከል ቢፈልግ እንኳ ይህን የሚያደርገው በደግነት ነው።”

4. አንድ ባል ከሌሎች ሴቶች ጋር ባለው ግንኙነት ለሚስቱ አሳቢነት የሚያሳየው እንዴት ነው?

4 አሳቢ የሆነ ባል ከሌሎች ሴቶች ጋር ባለው ግንኙነትም የሚስቱን ስሜት ከግምት ያስገባል። ሌሎች ሴቶችን አያሽኮረምምም ወይም ለእነሱ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት አይሰጥም። ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ሲጠቀምም ሆነ ሌሎች ድረ ገጾችን ሲቃኝም ቢሆን እንዲህ ከማድረግ ይቆጠባል። (ኢዮብ 31:1) በእርግጥም ለሚስቱ ታማኝ ለመሆን ጥረት ያደርጋል፤ ይህን የሚያደርገውም ሚስቱን ስለሚወዳት ብቻ ሳይሆን አምላክን ስለሚወድና ክፉ የሆነውን ነገር ስለሚጠላ ጭምር ነው።መዝሙር 19:14⁠ን እና 97:10ን አንብብ።

5. አንዲት ሚስት ለባሏ አሳቢነት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

5 አንድ ባል፣ ራሱ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያ የሚከተል ከሆነ ሚስቱ እሱን ‘በጥልቅ ማክበር’ አይከብዳትም። (ኤፌ. 5:22-25, 33) ሚስትም ብትሆን ለባሏ ያላት አክብሮት ለእሱ አሳቢነት ለማሳየት ያነሳሳታል፤ በተለይም ባሏ ለቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶች ሰፋ ያለ ጊዜ መስጠት ሲያስፈልገው ወይም የሚያስጨንቀው ነገር ሲኖር አሳቢነት ለማሳየት ጥረት ታደርጋለች። በብሪታንያ የሚኖር አንድ ባል እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ ባለቤቴ ሁኔታዬን በማየት የሆነ ነገር እንዳስጨነቀኝ ታስተውላለች። በዚህ ጊዜ በምሳሌ 20:5 ላይ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት በተግባር ለማዋል ትሞክራለች፤ ያሳሰበኝ ጉዳይ ሚስጥር ካልሆነ ሐሳቤን ‘ቀድታ ለማውጣት’ ጥረት ታደርጋለች፤ ይህን የምታደርገው ግን ተስማሚ ጊዜ መርጣ ነው።”

6. ልጆች ለሌሎች አሳቢነት እንዲያሳዩ ሁላችንም ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ ለልጆቹ ምን ጥቅም ያስገኛል?

6 አንዳቸው ለሌላው አሳቢነት የሚያሳዩ ወላጆች ለልጆቻቸው ግሩም ምሳሌ መሆን ይችላሉ። ልጆች ለሌሎች አሳቢነት እንዲያሳዩ የማሠልጠኑ ኃላፊነት በዋነኝነት የሚወድቀው በወላጆች ላይ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እንዳይሯሯጡ ማስተማራቸው አስፈላጊ ነው። ወይም ደግሞ በግብዣዎች ላይ ምግብ ሲወስዱ ትላልቅ ሰዎችን እንዲያስቀድሙ ሊነግሯቸው ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ ሁሉም የጉባኤው አባላት እንዲህ ያለ ሥልጠና በመስጠት ረገድ ወላጆችን ሊያግዟቸው ይችላሉ። አንድ ልጅ አሳቢነት የሚንጸባረቅበት ነገር ቢያደርግ ለምሳሌ በር ቢከፍትልን ልናመሰግነው ይገባል። እንዲህ ማድረጋችን ልጁ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ [እንደሚያስገኝ]” እንዲገነዘብ ስለሚረዳው አሳቢነት ማሳየቱን ለመቀጠል ይነሳሳል።—ሥራ 20:35

በጉባኤ ውስጥ “አንዳችን ለሌላው እናስብ”

7. ኢየሱስ መስማት ለተሳነው ሰው አሳቢነት ያሳየው እንዴት ነው? ከኢየሱስ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

7 በአንድ ወቅት ኢየሱስ ዲካፖሊስ በተባለው ክልል እያለ ሰዎች “መስማት የተሳነውና የመናገር እክል ያለበት አንድ ሰው ወደ እሱ [አመጡ]።” (ማር. 7:31-35) ኢየሱስ ግለሰቡን የፈወሰው ሰዎቹ መሃል እያለ ሳይሆን ‘ከሕዝቡ ለይቶ ለብቻው ከወሰደው’ በኋላ ነው። እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? ግለሰቡ መስማት የተሳነው በመሆኑ ብዙ ሰዎች መሃል ሲሆን ሊጨንቀው ይችላል። ኢየሱስ ሰውየውን ለብቻው ወስዶ የፈወሰው ይህን ስላስተዋለ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ እኛ እንደ ኢየሱስ ሰዎችን በተአምር መፈወስ አንችልም። ይሁን እንጂ የእምነት አጋሮቻችን ለሚያስፈልጓቸው ነገሮችና ለስሜታቸው ትኩረት መስጠት እንችላለን፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው እናስብ” በማለት ጽፏል። (ዕብ. 10:24 ግርጌ) ኢየሱስ፣ መስማት የተሳነው ሰው ምን ሊሰማው እንደሚችል ስለተረዳ አሳቢነት አሳይቶታል። ኢየሱስ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!

8, 9. በዕድሜ ለገፉና አቅመ ደካማ ለሆኑ ክርስቲያኖች አሳቢነት ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? ምሳሌ ስጥ።

8 ለአረጋውያንና አቅመ ደካማ ለሆኑት አሳቢነት አሳዩ። የክርስቲያን ጉባኤ መለያ፣ አባላቱ ውጤታማ በሆነ መንገድ ነገሮችን ማከናወን መቻላቸው ሳይሆን በመካከላቸው ያለው ፍቅር ነው። (ዮሐ. 13:34, 35) እንዲህ ያለው ፍቅር አረጋውያንንም ሆነ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ወንድሞቻችንን በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙና በስብከቱ ሥራ እንዲካፈሉ ለመርዳት የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት እንድናደርግ ያነሳሳናል። እነዚህ ወንድሞቻችን ማከናወን የሚችሉት ነገር ውስን መሆኑ እንዲህ ከማድረግ አያግደንም። (ማቴ. 13:23) ሚካኤል ያለተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ አይችልም፤ ይህ ወንድም የቤተሰቡ አባላትና በአገልግሎት ቡድኑ ውስጥ ያሉ ወንድሞች የሚያደርጉለትን ድጋፍ ከልቡ ያደንቃል። እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉም ድጋፍ ስለሚያደርጉልኝ በአብዛኞቹ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና አገልግሎት አዘውትሬ መውጣት ችያለሁ። በተለይም በአደባባይ ምሥክርነት መካፈል በጣም ያስደስተኛል።”

9 በብዙ ቤቴሎች ውስጥ በዕድሜ የገፉና አቅመ ደካማ የሆኑ ቤቴላውያን አሉ። አሳቢ የሆኑ የበላይ ተመልካቾች፣ እነዚህ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በደብዳቤና በስልክ አማካኝነት እንዲመሠክሩ ዝግጅት ያደርጋሉ። የ86 ዓመት አረጋዊ የሆኑት ቢል የተባሉ ወንድም ራቅ ባሉ አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች ደብዳቤ በመጻፍ ይመሠክራሉ፤ ወንድም ቢል “በደብዳቤ የመመሥከር አጋጣሚ በማግኘታችን በጣም ደስተኞች ነን” ብለዋል። ዕድሜያቸው ወደ 90 ዓመት የተጠጋው እህት ናንሲ ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦ “በደብዳቤ መመሥከር፣ ፖስታ እያሸጉ የመላክ ጉዳይ እንደሆነ አይሰማኝም። ይህ አገልግሎት ነው። ሰዎች እውነትን መስማት ያስፈልጋቸዋል!” በ1921 የተወለዱት እህት ኤተል እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “የማልታመምበት ቀን የለም ማለት እችላለሁ። አንዳንድ ጊዜ ልብሴን መልበስ እንኳ ትልቅ ሥራ ይሆንብኛል።” ያም ቢሆን እህት ኤተል በስልክ አማካኝነት የሚመሠክሩ ሲሆን ተመላልሶ መጠየቅ የሚያደርጉላቸው ሰዎችም አግኝተዋል። የ85 ዓመት አረጋዊት የሆኑት እህት ባርባራ ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦ “የጤና እክል ስላለብኝ አዘውትሬ አገልግሎት መውጣት በጣም ይከብደኛል። ሆኖም በስልክ አማካኝነት ለሌሎች እመሠክራለሁ። ለዚህም ይሖዋን አመሰግነዋለሁ!” በአንድ አገር በሚገኝ ቤቴል ውስጥ የሚኖሩ ውድ አረጋውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በአገልግሎት 1,228 ሰዓታት አሳልፈዋል፤ እነዚህ ክርስቲያኖች 6,265 ደብዳቤዎችን የጻፉና 6,315 ጽሑፎችን ያበረከቱ ሲሆን ከ2,000 በላይ የስልክ ጥሪዎችን አድርገዋል! የእነዚህ አረጋውያን ጥረት የይሖዋን ልብ ደስ እንዳሰኘው ምንም ጥርጥር የለውም!—ምሳሌ 27:11

10. ወንድሞቻችን ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ሙሉ ጥቅም እንዲያገኙ አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

10 በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አሳቢነት አሳዩ። ወንድሞቻችን ከስብሰባዎች ሙሉ ጥቅም እንዲያገኙ እንፈልጋለን። አሳቢነት ማሳየታችን ይህን ለማድረግ ያስችላቸዋል። ይሁንና አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ፣ ስብሰባዎች ላይ በሰዓቱ መድረስ ነው፤ ይህም ወንድሞቻችንን ሳያስፈልግ እንዳንረብሻቸው ያደርጋል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች እንድናረፍድ ሊያደርጉን ይችላሉ። ማርፈድ ልማድ ከሆነብን ግን ለሌሎች አሳቢነት ስለማሳየት በቁም ነገር ልናስብበት ይገባል። ከዚህም ሌላ በስብሰባው ላይ እንድንገኝ የጋበዙን ይሖዋና ኢየሱስ መሆናቸውን ማስታወስ ይኖርብናል። (ማቴ. 18:20) ይሖዋንና ኢየሱስን በጥልቅ ልናከብራቸው እንደሚገባ ጥያቄ የለውም!

11. በስብሰባዎች ላይ ክፍል የሚያቀርቡ ወንድሞች በ1 ቆሮንቶስ 14:40 ላይ የሚገኘውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ያለባቸው ለምንድን ነው?

11 ለወንድሞቻችን አሳቢነት ማሳየት “ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት ይሁን” የሚለውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግንም ይጨምራል። (1 ቆሮ. 14:40) በስብሰባዎች ላይ ክፍል የሚያቀርቡ ወንድሞች ክፍላቸውን በተመደበላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ ይህን መመሪያ እንደሚታዘዙ ያሳያሉ። እንዲህ ማድረጋቸው ደግሞ ቀጣዩን ክፍል ለሚያቀርበው ወንድምም ሆነ ለመላው ጉባኤ አሳቢነት እንዳላቸው ያረጋግጣል። አንዳንድ ወንድሞች ቤታቸው ሩቅ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ ወደ ቤታቸው የሚሄዱት በሕዝብ መጓጓዣ ነው፤ ወይም ደግሞ ቤታቸው ለመድረስ ረጅም መንገድ በእግራቸው መጓዝ ይኖርባቸዋል። የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸው ክርስቲያኖችም አሉ፤ እነዚህ ክርስቲያኖች በተወሰነ ሰዓት ቤት እንዲደርሱ ይጠበቅባቸው ይሆናል።

12. ተግተው ለሚሠሩት የጉባኤ ሽማግሌዎች “በፍቅር ለየት ያለ አሳቢነት” ልናሳያቸው የሚገባው ለምንድን ነው? (“ አመራር ለሚሰጡን ወንድሞች አሳቢነት ማሳየት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

12 በጉባኤ ውስጥ ተግተው ለሚሠሩና ግንባር ቀደም ሆነው በአገልግሎት በቅንዓት ለሚካፈሉ እረኞች ለየት ያለ አሳቢነት ልናሳያቸው ይገባል። (1 ተሰሎንቄ 5:12, 13ን አንብብ።) ሽማግሌዎች አንተን ለመርዳት የሚያደርጉትን ጥረት እንደምታደንቅ አያጠራጥርም። እንግዲያው ከእነሱ ጋር በመተባበርና እነሱን በመደገፍ አድናቆትህን አሳይ። ደግሞም እነዚህ ወንድሞች ‘ተግተው የሚጠብቁን ከመሆኑም ሌላ ይህን በተመለከተ ስሌት ያቀርባሉ።’—ዕብ. 13:7, 17

በአገልግሎት ላይ ለሰዎች አሳቢነት ማሳየት

13. ኢየሱስ ሰዎችን የያዘበት መንገድ ምን ያስተምረናል?

13 ኢሳይያስ፣ ኢየሱስን በተመለከተ “የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጨስንም የጧፍ ክር አያጠፋም” የሚል ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳ. 42:3) ኢየሱስ ለሰዎች ያለው ፍቅር እንዲያዝንላቸው አድርጎታል። እንደተቀጠቀጠ ሸምበቆ ወይም ሊጠፋ እንደተቃረበ የጧፍ ክር የሆኑትን ሰዎች ስሜት ይረዳ ነበር። በመሆኑም አሳቢነት፣ ደግነትና ትዕግሥት አሳይቷቸዋል። ልጆችም እንኳ ይወዱት ነበር። (ማር. 10:14) እኛ የኢየሱስ ዓይነት ማስተዋልና የማስተማር ችሎታ እንደሌለን የታወቀ ነው። ያም ሆኖ በክልላችን ውስጥ ላሉት ሰዎች አሳቢነት ማሳየት እንችላለን፤ ደግሞም ይህን ልናደርግ ይገባል። ይህም ‘ሰዎችን የምናነጋግረው እንዴት ነው? የምናነጋግራቸው መቼ ነው? እንዲሁም ለምን ያህል ደቂቃዎች ነው?’ በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰብን ይጨምራል።

14. ሰዎችን ለምናነጋግርበት መንገድ ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው?

14 ሰዎችን ማነጋገር ያለብን እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ምግባረ ብልሹና ጨካኝ በሆኑት የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም የንግዱን ሥርዓት በሚቆጣጠሩት ሰዎች በደል ይደርስባቸዋል፤ እነዚህ ሰዎች ‘እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈዋል እንዲሁም ተጥለዋል።’ (ማቴ. 9:36) በዚህም ምክንያት ብዙዎች ተጠራጣሪ ከመሆናቸውም ሌላ ተስፋ ቆርጠዋል። እንግዲያው የምንናገረው ነገርም ሆነ የድምፃችን ቃና ደግነትና አሳቢነት የሚንጸባረቅበት መሆኑ እጅግ አስፈላጊ ነው! ደግሞም ብዙ ሰዎች መልእክታችንን ለመቀበል የሚያነሳሳቸው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታችን ወይም የማስረዳት ችሎታችን ብቻ ሳይሆን ለእነሱ ልባዊ አሳቢነትና አክብሮት ማሳየታችንም ጭምር ነው።

15. ምሥራቹን ለምንሰብክላቸው ሰዎች አሳቢነት ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

15 ምሥራቹን ለምንሰብክላቸው ሰዎች አሳቢነት ማሳየት የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ጥያቄዎችን የምናቀርብበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ጥያቄዎችን መጠቀም ግሩም የማስተማሪያ ዘዴ ቢሆንም ይህን የምናደርገው በደግነትና በአክብሮት ሊሆን ይገባል። አንድ አቅኚ በክልሉ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች ቁጥብና ዓይናፋር በመሆናቸው፣ አድማጮቹን ሊያሸማቅቁ የሚችሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንደሌለበት ተገንዝቧል። ሰዎቹ ሊጠይቃቸው ያሰበውን ጥያቄ መልስ እንደማያውቁት ወይም የተሳሳተ መልስ ሊሰጡ እንደሚችሉ ከተጠራጠረ ጥያቄውን አይጠይቅም። ለምሳሌ፣ ‘የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ታውቃለህ?’ ወይም ‘የአምላክ መንግሥት ምን እንደሆነ ታውቃለህ?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ ይቆጠባል። ከዚህ ይልቅ “አምላክ የግል ስም እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንብቤያለሁ። የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላሳይህ?” በማለት ይጠይቃቸዋል። እርግጥ ነው፣ የሰዎች ባሕልና አመለካከት ይለያያል፤ በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ሕግ ማውጣት አያስፈልግም። ይሁን እንጂ ምንጊዜም ለሰዎች አሳቢነትና አክብሮት ማሳየት አለብን፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ በክልላችን ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሁኔታ በደንብ ማወቅ ይኖርብናል።

16, 17. (ሀ) ወደ ሰዎች ቤት የምንሄድበትን ጊዜ ስንመርጥ አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ሰዎቹ ጋ ከምንቆይበት ጊዜ ጋር በተያያዘ አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 ሰዎችን ማነጋገር ያለብን መቼ ነው? ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ሰዎቹ ቤት የምንሄደው ተጋብዘን እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። በመሆኑም ለመወያየት ይበልጥ በሚያመቻቸው ጊዜ መሄዳችን በጣም አስፈላጊ ነው! (ማቴ. 7:12) ለምሳሌ፣ በክልላችሁ ውስጥ ያሉ ሰዎች ቅዳሜና እሁድ አረፋፍደው የመነሳት ልማድ አላቸው? ከሆነ ቀኑ ረፈድ እስኪል ድረስ በአደባባይ ምሥክርነት ልትካፈሉ ወይም መንገድ ላይ ልታገለግሉ አሊያም ደግሞ በጠዋት እንደሚነሱ ለምታውቋቸው ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ ልታደርጉ ትችሉ ይሆናል።

17 ሰዎቹ ጋ ምን ያህል ጊዜ መቆየት ይኖርብናል? ብዙ ሰዎች ፕሮግራማቸው የተጣበበ ነው፤ በመሆኑም ቢያንስ መጀመሪያ አካባቢ ውይይታችንን አጠር ማድረጉ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ውይይታችን በጣም ከሚረዝም ይልቅ ቢያጥር የተሻለ ነው። (1 ቆሮ. 9:20-23) ሰዎች ሁኔታቸውን እንደተረዳን ወይም ሥራ የሚበዛባቸው መሆኑን እንዳስተዋልን ሲመለከቱ በሌላ ጊዜም ውይይቱን ለመቀጠል ፈቃደኞች ሊሆኑ ይችላሉ። በአገልግሎታችን ላይ የአምላክን መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች ማንጸባረቅ ይኖርብናል። ይህን ስናደርግ “ከአምላክ ጋር አብረን [መሥራት]” እንችላለን፤ ይሖዋም አንድን ሰው ወደ እውነት ለመሳብ በእኛ ሊጠቀም ይችላል።—1 ቆሮ. 3:6, 7, 9

18. ለሌሎች አሳቢነት ካሳየን ምን በረከት እናገኛለን?

18 እንግዲያው በቤተሰባችንና በጉባኤ ውስጥ እንዲሁም በአገልግሎት ላይ ለሌሎች አሳቢነት ለማሳየት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ። ይህን ካደረግን በአሁኑ ጊዜም ሆነ ወደፊት የተትረፈረፈ በረከት እናጭዳለን። መዝሙር 41:1, 2 እንዲህ ይላል፦ “ለተቸገረ ሰው የሚያስብ ደስተኛ ነው፤ በመከራ ቀን ይሖዋ ይታደገዋል። . . . በምድር ላይ ደስተኛ ይባላል።”