በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ”

“እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ”

“የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና እንዳከናውነው የሰጠኝን ሥራ መፈጸም ነው።”​—ዮሐ. 4:34

መዝሙሮች፦ 80, 35

1. በዓለም ላይ የሚታየው የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል?

ከአምላክ ቃል የምንማረውን ነገር በተግባር ማዋል ተፈታታኝ የሆነው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት፣ ትክክል የሆነውን ማድረግ ትሕትና የሚጠይቅ መሆኑ ነው። ትሑት መሆን ደግሞ ቀላል አይደለም፤ ምክንያቱም የምንኖረው “ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች” እንዲሁም “ራሳቸውን የማይገዙ” ሰዎች በሞሉባቸው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ነው። (2 ጢሞ. 3:1-3) የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ከላይ የተጠቀሱት ባሕርያት መጥፎ መሆናቸውን እናውቃለን፤ ሆኖም እነዚህን ባሕርያት የሚያንጸባርቁ ሰዎች በሕይወታቸው ሲሳካላቸው ስናይ ቅናት ሊያድርብን ይችላል። (መዝ. 37:1፤ 73:3) እንዲያውም ‘ከራሴ ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት ማስቀደሜ ምን ፋይዳ አለው? “ራሴን ከሁሉ እንደማንስ” አድርጌ መቁጠሬ ሌሎች ለእኔ አክብሮት እንዲያጡ ያደርጋቸው ይሆን?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች ይፈጠሩብን ይሆናል። (ሉቃስ 9:48) በዓለም ላይ ያለው የራስ ወዳድነት ዝንባሌ እንዲጋባብን ከፈቀድን ከወንድሞቻችን ጋር ያለን መልካም ግንኙነት ሊበላሽ አልፎ ተርፎም ክርስቲያናዊ ማንነታችንን ልናጣ እንችላለን። በሌላ በኩል ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ትሑት ሰዎች ምሳሌ መመርመራችንና አርዓያቸውን መከተላችን ይጠቅመናል።

2. በጥንት ዘመን ከነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ምን ትምህርት እናገኛለን?

2 ታማኝ የሆኑ የአምላክ አገልጋዮችን አርዓያ መከተል ከፈለግን የእነሱን ምሳሌ መመርመር አለብን። እነዚህ ሰዎች የአምላክ ወዳጅ መሆንና የእሱን ሞገስ ማግኘት የቻሉት እንዴት ነው? የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚረዳ ኃይል ያገኙትስ ከየት ነው? እንዲህ ያለ ጥናት ማድረጋችን መንፈሳዊነታችንን በእጅጉ ያጠናክረዋል።

መንፈሳዊ ምግብ እውቀት ብቻ ነው?

3, 4. (ሀ) መንፈሳዊ ትምህርት የምናገኘው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) መንፈሳዊ ምግብ መመገብ ሲባል እውቀት ከመሰብሰብ ያለፈ ነገርን ይጨምራል የምንለው ለምንድን ነው?

3 ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን፣ ከድረ ገጾቻችን፣ ከJW ብሮድካስቲንግ እንዲሁም ከጉባኤና ከትላልቅ ስብሰባዎቻችን ብዙ ትምህርትና ሥልጠና እናገኛለን። ይሁንና ኢየሱስ በዮሐንስ 4:34 ላይ ከተናገረው ሐሳብ መረዳት እንደምንችለው መንፈሳዊ ምግብ መመገብ ሲባል እውቀት ከመሰብሰብ ያለፈ ነገርን ይጨምራል። ኢየሱስ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና እንዳከናውነው የሰጠኝን ሥራ መፈጸም ነው” ብሏል።

4 ኢየሱስ፣ የአምላክን ፈቃድ ማድረግን እንደ መንፈሳዊ ምግብ ተመልክቶታል። ሆኖም የአምላክን ፈቃድ ማድረግ እንደ ምግብ የተቆጠረው እንዴት ነው? ጥሩ ምግብ ስንመገብ እንደምንረካና ሰውነታችን እንደሚጠናከር ሁሉ የአምላክን ፈቃድ ስንፈጽምም ደስታ እናገኛለን፤ እምነታችንም ይጠናከራል። ወደ መስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ስንሄድ ደክሞን የነበረ ቢሆንም ስናገለግል ከዋልን በኋላ መንፈሳችን ታድሶና ኃይላችን ተጠናክሮ የተመለስንበት ጊዜ የለም?

5. ጥበበኛ መሆን ምን ጥቅም አለው?

5 ጥበበኛ መሆን ሲባል ከአምላክ ያገኘነውን ትምህርት በተግባር ማዋልን ያመለክታል። (ያዕ. 3:13) ጥበብ ለማግኘት ስንል የምናደርገው ጥረት መልሶ የሚክስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “አንተ የምትመኘው ማንኛውም ነገር ሊተካከላት አይችልም። . . . ለሚይዟት የሕይወት ዛፍ ናት፤ አጥብቀው የሚይዟትም ደስተኞች ይባላሉ።” (ምሳሌ 3:13-18) ኢየሱስም “እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 13:17) ደቀ መዛሙርቱ ደስተኛ ሆነው መኖር የሚችሉት ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች መፈጸማቸውን ከቀጠሉ ነው። የኢየሱስን ትምህርትና ምሳሌ መከተል በሕይወታቸው ሙሉ ሊያደርጉት የሚገባ ነገር ነው።

6. የተማርነውን ነገር በተግባር ማዋላችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?

6 በዛሬው ጊዜ ያለን ክርስቲያኖችም ብንሆን የተማርናቸውን ነገሮች ምንጊዜም ተግባራዊ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ አንድ መካኒክ ለሥራው የሚያስፈልገው እውቀት እንዲሁም የጥገና መሣሪያዎችና አስፈላጊ ቁሳቁሶች ይኖሩት ይሆናል። ሆኖም እነዚህን ነገሮች ካልተጠቀመባቸው ምንም የሚፈይዱለት ነገር የለም። በዚህ ሥራ ተሰማርቶ ብዙ ተሞክሮ አካብቶ ሊሆን ይችላል፤ ያም ቢሆን በሥራው ምንጊዜም ውጤታማ መሆን ከፈለገ፣ ያገኘውን ተሞክሮ ተጠቅሞ ሥራውን ማከናወኑን መቀጠል አለበት። እኛም በተመሳሳይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘነውን እውቀት ተግባራዊ ማድረግ ስንጀምር ጥሩ ውጤት አግኝተን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ዘላቂ ደስታ ማጣጣም የምንችለው ይሖዋ የሚሰጠንን መመሪያ በትሕትና ተግባራዊ ማድረጋችንን ከቀጠልን ነው።

7. ጥበብ ማዳበር እንድንችል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙ ምሳሌዎች ስንማር ምን ማድረግ ይኖርብናል?

7 ትሕትናችን ሊፈተን የሚችልባቸውን አንዳንድ ሁኔታዎች እንዲሁም በጥንት ዘመን የነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች እንደ እነዚህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ትሕትና ያሳዩት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ይሁንና መንፈሳዊነታችን እንዲጠናከር ከፈለግን ስለ እነሱ መረጃ ከማግኘት ያለፈ ነገር ማድረግ እንዳለብን አንዘንጋ። በመሆኑም ከእነዚህ ዘገባዎች የምታገኘውን ትምህርት እንዴት በተግባር ማዋል እንደምትችል ቆም ብለህ አስብ፤ እንዲሁም ዛሬ ነገ ሳትል ትምህርቱን በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ አድርግ።

ራሳችሁን ከሌሎች ከፍ አድርጋችሁ አትመልከቱ

8, 9. በሐዋርያት ሥራ 14:8-15 ላይ ያለው ዘገባ ጳውሎስ ስላሳየው ትሕትና ምን ያስተምረናል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

8 የአምላክ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።” (1 ጢሞ. 2:4) አንተስ እውነትን ገና ላልሰሙት የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ምን አመለካከት አለህ? ሐዋርያው ጳውሎስ ምን እንዳደረገ እስቲ እንመልከት፤ ጳውሎስ ስለ አምላክ መጠነኛ እውቀት ላላቸው ሰዎች ለመስበክ ወደ ምኩራቦች የሄደ ቢሆንም ምሥራቹን የተናገረው ለአይሁዳውያን ብቻ አልነበረም። የሐሰት አማልክትን ለሚያመልኩ ሰዎችም ሰብኳል፤ ይሁንና ይህን ሲያደርግ ትሕትናውን የሚፈትን ሁኔታ አጋጥሞታል።

9 ለምሳሌ በመጀመሪያው የሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ሊቃኦናውያን እሱና በርናባስ ያከናወኑትን ነገር ሲያዩ፣ ሄርሜስና ዙስ የተባሉት የሐሰት አምላኮቻቸው በሰው አምሳል ሆነው እንደወረዱ ተሰምቷቸው ነበር። ታዲያ ጳውሎስና በርናባስ እንዲህ ያለ ክብር ሲሰጣቸው ምን አደረጉ? ከዚያ በፊት በሰበኩባቸው ሁለት ከተሞች ካጋጠማቸው ስደት ትንሽ እፎይ የሚሉበት አጋጣሚ እንዳገኙ ተሰምቷቸው ይሆን? እንዲህ ያለ ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑ ምሥራቹን ይበልጥ ለማስፋፋት እንደሚረዳቸው አስበው ይሆን? በጭራሽ! ልብሳቸውን ቀደው እየሮጡ ወደ ሕዝቡ መሃል በመግባት “እንዲህ የምታደርጉት ለምንድን ነው? እኛም እንደ እናንተው ድክመት ያለብን ሰዎች ነን” በማለት ተቃውሟቸውን አሰሙ።—ሥራ 14:8-15

10. ጳውሎስና በርናባስ ከሊቃኦናውያን ጋር እኩል እንደሆኑ የተሰማቸው ከምን አንጻር ነው?

10 ጳውሎስና በርናባስ፣ “እኛም እንደ እናንተው ድክመት ያለብን ሰዎች ነን” ሲሉ እነሱም እንደነዚያ ሰዎች ጣዖት አምላኪ እንደሆኑ መናገራቸው አልነበረም። ጳውሎስና በርናባስ ልዩ ተልእኮ የተሰጣቸው ሚስዮናውያን ናቸው። (ሥራ 13:2) በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ከመሆኑም ሌላ ክብራማ ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል። ይህ መሆኑ ግን ራሳቸውን ከሌሎች ከፍ አድርገው ለመመልከት ምክንያት አይሆናቸውም። ጳውሎስና በርናባስ፣ ሊቃኦናውያንም ቢሆን ምሥራቹን ከተቀበሉ እነሱ ያገኟቸውን መብቶች ማግኘት እንደሚችሉ ተገንዝበው ነበር።

11. ምሥራቹን ስንሰብክ ጳውሎስ በትሕትና ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

11 እኛስ ትሕትና በማሳየት ረገድ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? በአንደኛ ደረጃ፣ በይሖዋ ኃይል ላከናወንነው ነገር ሌሎች ለየት ያለ አድናቆት እንዲሰጡን መጠበቅ የለብንም፤ እንዲህ ያለ አድናቆት ቢሰጠንም ልንቀበል አይገባም። ሁላችንም እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ለምሰብክላቸው ሰዎች ምን አመለካከት አለኝ? አንዳንድ የማኅበረሰቡ ክፍሎችን በተመለከተ በአካባቢዬ ያሉ ብዙ ሰዎች ያላቸው ዓይነት የተዛባ አመለካከት ሳይታወቀኝ አዳብሬ ይሆን?’ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በክልላቸው ውስጥ ምሥራቹን የሚቀበሉ ተጨማሪ ሰዎችን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ መሆኑ የሚያስመሰግን ነው። እንዲያውም አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ ማኅበረሰቡ ዝቅ አድርጎ የሚመለከታቸውን ሰዎች ቋንቋና ባሕል ተምረዋል። ይሁንና እንዲህ የሚያደርጉ ክርስቲያኖች፣ ከሚሰብኩላቸው ሰዎች እንደሚበልጡ አድርገው ራሳቸውን በፍጹም ሊመለከቱ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ለእያንዳንዱ ሰው ትኩረት በመስጠት ምሥራቹን የግለሰቡን ልብ በሚነካ መንገድ ለማቅረብ መጣር ይኖርባቸዋል።

የሌሎችን ስም ጠቅሳችሁ ጸልዩ

12. ኤጳፍራ ለሌሎች ከልቡ እንደሚያስብ ያሳየው እንዴት ነው?

12 መለኮታዊ መመሪያን በትሕትና እንደምንከተል የምናሳይበት ሌላው መንገድ “እኛ ያገኘነውን ዓይነት ክቡር እምነት ለተቀበሉ” ወንድሞቻችን መጸለይ ነው። (2 ጴጥ. 1:1) ኤጳፍራ እንዲህ አድርጓል። ኤጳፍራ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ሦስት ጊዜ ብቻ ሲሆን ሦስቱም ጥቅሶች የሚገኙት ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት በጻፋቸው ደብዳቤዎች ውስጥ ነው። ጳውሎስ በሮም የቁም እስረኛ በነበረበት ወቅት በቆላስይስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ደብዳቤ ጽፎ ነበር፤ በደብዳቤው ላይ ስለ ኤጳፍራ ሲናገር “ዘወትር በጸሎቱ ስለ እናንተ እየተጋደለ ነው” ብሏቸዋል። (ቆላ. 4:12) ኤጳፍራ ወንድሞቹን በሚገባ ያውቃቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ከልቡ ያስብላቸው ነበር። እሱም እንደ ጳውሎስ “እስረኛ” የነበረ ቢሆንም ይህ የሌሎችን መንፈሳዊ ፍላጎት እንዳያስተውል አላደረገውም። (ፊልሞና 23) ደግሞም እነሱን ለመርዳት ስለፈለገ እነሱን በተመለከተ ጸልዮአል። በእርግጥም ኤጳፍራ ለሌሎች ከልቡ ያስብ ነበር። እኛም አብረውን ይሖዋን የሚያገለግሉ ክርስቲያኖችን በተመለከተ የምናቀርበው ጸሎት ታላቅ ኃይል አለው፤ በተለይ ደግሞ ስማቸውን ጠቅሰን መጸለያችን በጣም ጠቃሚ ነው።—2 ቆሮ. 1:11፤ ያዕ. 5:16

13. በጸሎት ረገድ የኤጳፍራን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

13 አንተም ኤጳፍራ እንዳደረገው ስማቸውን ጠቅሰህ ልትጸልይላቸው ስለምትችል ሰዎች ለማሰብ ሞክር። በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በጉባኤያቸው ውስጥ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ልክ እንደ ኤጳፍራ ጸሎት ያቀርባሉ፤ ለምሳሌ፣ ብዙ ኃላፊነት ያለባቸው ወይም ከባድ ውሳኔ ማድረግ የሚያስፈልጋቸው አሊያም ፈተና የሚያጋጥማቸው የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በተመለከተ ይጸልያሉ። ሌሎች ደግሞ jw.org ላይ ስማቸው ለተዘረዘሩት በእስር ላይ ያሉ ወንድሞቻቸው ጸሎት ያቀርባሉ። (ኒውስሩም > ሊጋል ዲቨሎፕመንትስ በሚለው ሥር ጀሆቫስ ዊትነስስ ኢምፕሪዝንድ ፎር ዜይር ፌይዝየሚለውን ርዕስ ተመልከት።) ከዚህም በተጨማሪ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ፣ በአደጋ ወይም በጦርነት የተነሳ ችግር ያጋጠማቸው እንዲሁም ከኢኮኖሚ ችግር ጋር የሚታገሉ ወንድሞቻችንን በጸሎት ማሰባችን አስፈላጊ ነው። በእርግጥም ጸሎታችን የሚያስፈልጋቸው በርካታ ወንድሞችና እህቶች አሉ። እነዚህን ክርስቲያኖች በተመለከተ ስንጸልይ፣ ስለ ራሳችን ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት እንደምንሰጥ እናሳያለን። (ፊልጵ. 2:4) ይሖዋም እንዲህ ዓይነት ጸሎቶችን ይሰማል።

‘ለመስማት የፈጠናችሁ ሁኑ’

14. ሌሎችን ከማዳመጥ ጋር በተያያዘ ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ የተወልን እንዴት ነው?

14 ትሕትናችን የሚፈተንበት ሌላው አቅጣጫ ደግሞ ‘ሌሎች ሲናገሩ በትዕግሥት ለማዳመጥ ፈቃደኛ ነን?’ የሚለው ነው። ያዕቆብ 1:19 ‘ለመስማት የፈጠንን’ መሆን እንዳለብን ይናገራል። በዚህ ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ይሖዋ ነው። (ዘፍ. 18:32፤ ኢያሱ 10:14) በዘፀአት 32:11-14 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ዘገባ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚያስተምረን እስቲ እንመልከት። (ጥቅሱን አንብብ።) ይሖዋ ከሙሴ ጋር መመካከር ባያስፈልገውም ሙሴ ሐሳቡን እንዲገልጽ አጋጣሚ ሰጥቶታል። አንተ ብትሆን ሲሳሳት ያየኸውን ሰው ሐሳብ በትዕግሥት አዳምጠህ የእሱን ሐሳብ ተግባራዊ ታደርጋለህ? ይሖዋ ግን በእምነት ወደ እሱ የሚጸልዩ ሰዎችን ሁሉ በትዕግሥት ያዳምጣል።

15. ሌሎችን በማክበር ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

15 ሁላችንም ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘ይሖዋ ራሱን ዝቅ በማድረግ አብርሃምን፣ ራሔልን፣ ሙሴን፣ ኢያሱን፣ ማኑሄን፣ ኤልያስን እና ሕዝቅያስን በትዕግሥት ካዳመጠ እኔስ ከወንድሞቼ ጋር በተያያዘ እንዲህ ማድረግ የለብኝም? ወንድሞቼ ሐሳብ ሲሰጡ በማዳመጥ ብሎም የሰጡኝን ጥሩ ሐሳብ በተግባር በማዋል አክብሮት ላሳያቸውስ አይገባም? በጉባኤያችን ውስጥ ካሉ ወንድሞች አሊያም ከቤተሰቤ አባላት መካከል በአሁኑ ወቅት የእኔ ትኩረት የሚያስፈልገው ሰው አለ? ግለሰቡን ለመርዳት ምን ማድረግ እችላለሁ?’—ዘፍ. 30:6፤ መሳ. 13:9፤ 1 ነገ. 17:22፤ 2 ዜና 30:20

“ምናልባትም ይሖዋ መከራዬን ያይልኝ . . . ይሆናል”

ዳዊት “ተዉት ይርገመኝ” ብሏል፤ አንተ ብትሆን ምን ታደርግ ነበር? (አንቀጽ 16, 17⁠ን ተመልከት)

16. ንጉሥ ዳዊት፣ ሺምአይ ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርግበት ምን ምላሽ ሰጥቷል?

16 ትሕትና፣ ሌሎች ተገቢ ያልሆነ ነገር በሚያደርጉብን ጊዜ ራሳችንን ለመግዛትም ይረዳናል። (ኤፌ. 4:2) በ2 ሳሙኤል 16:5-13 ላይ የሚገኘው ዘገባ በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። (ጥቅሱን አንብብ።) የንጉሥ ሳኦል ዘመድ የሆነው ሺምአይ በዳዊትና በአገልጋዮቹ ላይ ስድብና አካላዊ ጥቃት ሰንዝሮባቸው ነበር። ዳዊት ይህን ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ማስቆም ቢችልም ሁኔታውን በትዕግሥት አለፈው። ዳዊት እንዲህ ያለ ራስን የመግዛት ባሕርይ ለማሳየት የረዳው ምንድን ነው? መዝሙር 3⁠ን መመርመራችን ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ያስችለናል።

17. ዳዊት ራስን የመግዛትን ባሕርይ እንዲያሳይ የረዳው ምንድን ነው? እኛስ የዳዊትን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

17 በመዝሙር 3 አናት ላይ ያለው መግለጫ እንደሚጠቁመው ዳዊት ይህን መዝሙር ያቀናበረው “ከልጁ ከአቢሴሎም በሸሸ ጊዜ” ነው። በቁጥር 1 እና 2 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በሁለተኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 16 ላይ ስለተገለጹት ክንውኖች የሚያወሳ ነው። መዝሙር 3:4 ደግሞ ዳዊት በይሖዋ ምን ያህል እንደሚታመን ያሳያል፤ ጥቅሱ “ድምፄን ከፍ አድርጌ ይሖዋን እጣራለሁ፤ እሱም ከተቀደሰ ተራራው ይመልስልኛል” ይላል። እኛም ጥቃት በሚሰነዘርብን ጊዜ መጸለይ እንችላለን። ይሖዋ ለመጽናት የሚረዳንን ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ጸሎታችንን ይመልስልናል። አንተስ ትዕግሥትህን የሚፈታተን ሁኔታ ሲያጋጥምህ ራስህን በመግዛት አሊያም ሌሎች ያለምክንያት ሲጠሉህ በነፃ ይቅር በማለት ረገድ ማሻሻያ ማድረግ ትችላለህ? ይሖዋ መከራህን ተመልክቶ እንደሚባርክህስ ትተማመናለህ?

“ጥበብ በጣም አስፈላጊ ነገር ናት”

18. የአምላክን መመሪያዎች ምንጊዜም በተግባር ማዋላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

18 ትክክል እንደሆነ የምናውቀውን ነገር ማድረግ የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል። በእርግጥም ምሳሌ 4:7 “ጥበብ በጣም አስፈላጊ ነገር ናት” ማለቱ አያስገርምም! ጥበብ የሚመሠረተው በእውቀት ላይ ነው፤ ያም ቢሆን አንድን እውነታ ከመረዳት ያለፈ ነገርን ይጨምራል፤ ጥበብ የሚገለጸው በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ነው። ጉንዳኖች እንኳ ጥበብ እንዳላቸው ያሳያሉ። ጉንዳኖች ምግባቸውን በበጋ ወቅት ማዘጋጀታቸው በደመ ነፍስ ጥበበኞች እንደሆኑ ይጠቁማል። (ምሳሌ 30:24, 25) “የአምላክ ጥበብ” የተባለው ክርስቶስም ምንጊዜም የሚያደርገው አባቱን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ነው። (1 ቆሮ. 1:24፤ ዮሐ. 8:29) አምላክ ትክክለኛውን ውሳኔ በማድረግና ውሳኔያችንን በተግባር በማዋል መካከል ልዩነት እንዳለ ያውቃል። እንዲሁም ምንጊዜም ትሕትና የሚያሳዩና ትክክል እንደሆነ የሚያውቁትን ነገር በተግባር የሚያውሉ ሰዎችን ይባርካል። (ማቴዎስ 7:21-23ን አንብብ።) እንግዲያው ትሕትና ለማሳየት ጥረት እናድርግ፤ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ሌሎች የክርስቲያን ጉባኤ አባላትም ይሖዋን በትሕትና እንዲያገለግሉ እናበረታታለን። ትክክል እንደሆነ የምናውቀውን ነገር ማድረግ ጊዜና ትዕግሥት ይጠይቃል፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረጋችን ትሕትና እንዳለን ያሳያል። ትሕትና ደግሞ አሁንም ሆነ ለዘላለም ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል።