በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍቅር በማሳየት ሌሎችን ማነጻችሁን ቀጥሉ

ፍቅር በማሳየት ሌሎችን ማነጻችሁን ቀጥሉ

“ፍቅር ግን ያንጻል።”—1 ቆሮ. 8:1

መዝሙሮች፦ 109, 121

1. ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ ስለ የትኛው አስፈላጊ ጉዳይ ተናግሯል?

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ ስለ ፍቅር 30 ጊዜ ገደማ ጠቅሷል። ለደቀ መዛሙርቱም “እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” የሚል ቀጥተኛ መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ዮሐ. 15:12, 17) ደቀ መዛሙርቱ አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅር በጉልህ የሚታይ መሆን አለበት፤ እንዲያውም ፍቅራቸው የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች እንደሆኑ በግልጽ የሚያሳይ መለያ ምልክት ይሆናል። (ዮሐ. 13:34, 35) ይሁን እንጂ በመካከላቸው የሚኖረው ፍቅር የስሜት ጉዳይ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ የተናገረው የራስን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ ስለሚያነሳሳ ላቅ ያለ የፍቅር ዓይነት ነው። ኢየሱስ “ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም። የማዛችሁን ነገር የምትፈጽሙ ከሆነ ወዳጆቼ ናችሁ” ብሏል።—ዮሐ. 15:13, 14

2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ተለይተው የሚታወቁት በምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችም እውነተኛና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር በማሳየት እንዲሁም አንድነታቸውን በመጠበቅ ተለይተው ይታወቃሉ። (1 ዮሐ. 3:10, 11) የይሖዋ አገልጋዮች የተለያየ ብሔር፣ ጎሣ፣ ቋንቋ ወይም አስተዳደግና ባሕል ቢኖራቸውም የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር የሚያሳዩ መሆኑ ምንኛ የሚያስደስት ነው! ይሁንና እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ይነሱ ይሆናል፦ ‘ፍቅር በተለይ በአሁኑ ወቅት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋና ኢየሱስ በፍቅር የሚያንጹን እንዴት ነው? እኛስ የክርስቶስን ዓይነት ፍቅር በማሳየት ሌሎችን “ማነጽ” የምንችለው እንዴት ነው?’—1 ቆሮ. 8:1

ፍቅር በተለይ በአሁኑ ወቅት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3. የምንኖርበት “ለመቋቋም የሚያስቸግር” ዘመን በብዙዎች ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?

3 “ለመቋቋም የሚያስቸግር” በተባለው በዚህ ዘመን ሕይወት “በችግርና በሐዘን የተሞላ ነው”፤ በመሆኑም በዘመናችን የሚኖሩ ብዙ ሰዎች በጭንቀት ይዋጣሉ። (መዝ. 90:10፤ 2 ጢሞ. 3:1-5) በርካቶች ሕይወት ተስፋ አስቆራጭ ስለሆነባቸው ቢሞቱ እንደሚሻል ይሰማቸዋል። በየዓመቱ ከ800,000 በላይ ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት እንደሚያጠፉ አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ፤ ይህም በየ40 ሴኮንዱ አንድ ሰው ሕይወቱን ያጠፋል ማለት ነው። የሚያሳዝነው አንዳንድ ክርስቲያኖችም እንኳ የሚሰማቸውን ጭንቀት መቋቋም ስላቃታቸው ሕይወታቸውን አጥፍተዋል።

4. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ የትኞቹ ሰዎች ሞትን ተመኝተው ነበር?

4 በጥንት ዘመን የኖሩ አንዳንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ሁኔታዎች በጣም አስጨናቂ ስለሆኑባቸው ሞትን ተመኝተው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢዮብ ሥቃዩ እጅግ ስለበዛበት “ሕይወቴን ተጸየፍኳት፤ በሕይወት መቀጠል አልፈልግም” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 7:16፤ 14:13) ዮናስም በአገልግሎት ምድቡ ያጋጠመው ነገር በጣም ስላበሳጨው “ይሖዋ ሆይ፣ በሕይወት ከመኖር ይልቅ መሞት ስለሚሻለኝ እባክህ ግደለኝ” ብሎ ነበር። (ዮናስ 4:3) ታማኙ ነቢይ ኤልያስም በአንድ ወቅት በጣም ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ “አሁንስ በቅቶኛል! ይሖዋ ሆይ፣ . . . ሕይወቴን ውሰዳት” ብሏል። (1 ነገ. 19:4) ሆኖም ይሖዋ እነዚህን ታማኝ አገልጋዮቹን ይወዳቸው ስለነበር ሕይወታቸውን እንዲያጡ አልፈለገም። ይሖዋ፣ አገልጋዮቹን እንደዚህ ስለተሰማቸው በመንቀፍ ፋንታ ለእነሱ ያለውን ፍቅር በማሳየት አንጿቸዋል፤ ይህም ሞትን ከመመኘት ይልቅ በሕይወት ኖረው እሱን በታማኝነት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል።

5. ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በተለይ በአሁኑ ወቅት ፍቅራችን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

5 እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተስፋ ቆርጠው ‘ሕይወት በቅቶኛል’ እስከማለት አይደርሱ ይሆናል፤ ይሁንና በርካታ አስጨናቂ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሟቸው ፍቅር በማሳየት ልናንጻቸው ይገባል። አንዳንዶች ስደትና ፌዝ ይደርስባቸዋል። ሌሎች በሥራ ቦታቸው የሚሰነዘርባቸው ነቀፋ እንዲሁም የሥራ ባልደረቦቻቸው ሐሜት ስሜታቸውን ይጎዳዋል። አሊያም ደግሞ ተጨማሪ ሰዓት መሥራታቸው ወይም ከአቅማቸው በላይ እንዲሠሩ የሚጠበቅባቸው መሆኑ ውጥረት ይፈጥርባቸዋል። አንዳንዶች መንፈሳቸውን የሚደቁስ የቤተሰብ ችግር ያጋጥማቸዋል፤ ለምሳሌ የማያምን የትዳር ጓደኛቸው ነጋ ጠባ ይተቻቸው ይሆናል። በጉባኤያችን ያሉ በርካታ ክርስቲያኖች እንደነዚህ ያሉ ችግሮች ስለሚደራረቡባቸው ይዝላሉ። ታዲያ ተስፋ የቆረጡ ክርስቲያኖችን ማን ሊረዳቸው ይችላል?

የይሖዋ ፍቅር ያንጸናል

6. ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ፍቅር በማሳየት የሚያንጻቸው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ፣ አገልጋዮቹን ምንጊዜም እንደሚወዳቸው ማረጋገጫ በመስጠት ያንጻቸዋል። ታማኝ የሆኑት እስራኤላውያን፣ ይሖዋ በተናገረው በሚከተለው ሐሳብ በእጅጉ ተበረታተው መሆን አለበት፤ ይሖዋ ለሕዝቡ “አንተ በዓይኔ ፊት ውድ ሆነሃልና፤ የተከበርክም ነህ፤ እኔም ወድጄሃለሁ። . . . እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ” ብሎ ነበር። (ኢሳ. 43:4, 5) አንተም የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን ይሖዋ አጥብቆ እንደሚወድህ ቅንጣት ታክል አትጠራጠር። * ይሖዋ ንጹሑን አምልኮ የሚከተሉ ሰዎችን ‘እንደ ኃያል ተዋጊ እንደሚያድናቸው እንዲሁም በታላቅ ደስታ በእነሱ ሐሴት እንደሚያደርግ’ ቃል ገብቷል።—ሶፎ. 3:16, 17

7. ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ያለው ፍቅር የምታጠባ እናት ለልጇ ካላት ፍቅር ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

7 ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥማቸው እንደሚንከባከባቸውና እንደሚያጽናናቸው ቃል ገብቷል። አገልጋዮቹን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እናንተም ትጠባላችሁ፤ ጀርባዋም ላይ ታዝላችኋለች፣ ጭኗም ላይ ሆናችሁ ትዘላላችሁ። እናት ልጇን እንደምታጽናና፣ እኔም እናንተን ሁልጊዜ አጽናናችኋለሁ።” (ኢሳ. 66:12, 13) ይህ ምንኛ የሚያበረታታ ሐሳብ ነው! አንዲት አፍቃሪ እናት ልጇን በጀርባዋ ስታዝል ወይም ጭኗ ላይ አድርጋ ስታጫውት በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ጥቅሱ፣ ይሖዋ ለእውነተኛ አገልጋዮቹ ያለውን ጥልቅ ፍቅርና አሳቢነት ግሩም አድርጎ ይገልጻል። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚወድህና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከትህ ጨርሶ ጥርጣሬ አይግባህ።—ኤር. 31:3

8, 9. የኢየሱስ ፍቅር ብርታት የሚሰጠን እንዴት ነው?

8 እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ ይሖዋ እንደሚወዳቸው እርግጠኛ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ሌላም ምክንያት አለ፤ መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል” ይላል። (ዮሐ. 3:16) ኢየሱስም ቢሆን ሕይወቱን ለእኛ በመስጠት ታላቅ ፍቅር አሳይቶናል! ኢየሱስ ያሳየን ፍቅር ኃይል ይሰጠናል። የአምላክ ቃል ‘መከራም ሆነ ጭንቀት ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል’ ይናገራል።—ሮም 8:35, 38, 39

9 አካላችንን የሚያዝሉ፣ ስሜታችንን የሚደቁሱ ወይም መንፈሳዊነታችንን የሚያዳክሙ ችግሮች ሲያጋጥሙን የክርስቶስ ፍቅር ለመጽናት የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15ን አንብብ።) ድንገተኛ አደጋ፣ ስደት አሊያም ተስፋ የሚያስቆርጥ ወይም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመንም እንኳ የክርስቶስ ፍቅር ያበረታናል፤ እንዲሁም በሕይወት ለመቀጠል የሚያነሳሳ ጥንካሬ ይሰጠናል።

ወንድሞቻችን የእኛ ፍቅር ያስፈልጋቸዋል

ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ማጥናታችን ሌሎችን ለማነጽ ያነሳሳናል (አንቀጽ 10, 11⁠ን ተመልከት)

10, 11. ተስፋ የቆረጡ ክርስቲያኖችን የማበረታታት ኃላፊነት ያለባቸው እነማን ናቸው? አብራራ።

10 ይሖዋ ፍቅር በማሳየት እኛን ለማነጽ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ የክርስቲያን ጉባኤ ነው። የእምነት ባልንጀሮቻችንን በመውደድ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊና ስሜታዊ ድጋፍ በማድረግ ይሖዋ ላሳየን ፍቅር ምላሽ መስጠት እንችላለን። (1 ዮሐ. 4:19-21) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “አሁን እያደረጋችሁት እንዳለው እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ” በማለት መክሯቸዋል። (1 ተሰ. 5:11) በእርግጥም ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም የጉባኤው አባላት፣ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን በማጽናናት ብሎም በማነጽ የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ይችላሉ።—ሮም 15:1, 2ን አንብብ።

11 የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች የሕክምና እርዳታ ማግኘት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። (ሉቃስ 5:31) ሽማግሌዎችም ሆኑ ሌሎች የጉባኤው አባላት የሥነ አእምሮ ባለሙያዎች የሚሰጡት ዓይነት የሕክምና እርዳታ መስጠት እንደማይችሉ ያውቃሉ። ያም ቢሆን “የተጨነቁትን አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ጠቃሚ እገዛ ማበርከት ይችላሉ። (1 ተሰ. 5:14) ሁላችንም የተጨነቁ ክርስቲያኖችን ስሜት ለመረዳትና ትዕግሥት ለማሳየት ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል፤ በተጨማሪም ሊያጽናናቸው በሚችል መንገድ ልናነጋግራቸው ይገባል። አንተስ ሌሎችን ለማበረታታትና ለማጽናናት ትጥራለህ? እንዲህ ያለውን እርዳታ ማበርከት የሚቻልበትን መንገድ ማወቅህ ሌሎችን በማበረታታት ረገድ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ይረዳሃል።

12. ጉባኤው ባሳየው ፍቅር የተበረታታ ሰው ምሳሌ ጥቀስ።

12 በመንፈስ ጭንቀት ለሚሠቃዩ ወንድሞቻችን ፍቅር በማሳየት እነሱን ማነጽ የምንችለው እንዴት ነው? በአውሮፓ የምትኖር አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ራሴን የማጥፋት ሐሳብ የሚመጣብኝ ጊዜ አለ። ይሁንና ወንድሞቼና እህቶቼ በጣም ያበረታቱኛል። የጉባኤዬ አባላት ሕይወቴን ታድገዋታል። ሁልጊዜ ፍቅርና አሳቢነት ያሳዩኛል። በመንፈስ ጭንቀት እንደምሠቃይ የሚያውቁት ጥቂቶች ብቻ ቢሆኑም ሁሉም የጉባኤው አባላት ምንጊዜም ከጎኔ ናቸው። በተለይ አንድ ባልና ሚስት፣ መንፈሳዊ አባትና እናት ሆነውልኛል። በጣም የሚንከባከቡኝ ከመሆኑም ሌላ በቀን ውስጥ 24 ሰዓት ሊረዱኝ ዝግጁ ናቸው።” እርግጥ፣ ሁሉም ሰው በእኩል ደረጃ ድጋፍ ማድረግ ይችላል ማለት አይደለም። ሆኖም በመንፈስ ጭንቀት የሚሠቃዩ ክርስቲያኖችን ለመርዳት የምናደርገው ልባዊ ጥረት በሕይወታቸው ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። *

ሌሎችን በፍቅር ማነጽ የምንችለው እንዴት ነው?

13. ሌሎችን ለማነጽ ምን ማድረግ ያስፈልገናል?

13 ጥሩ አዳማጭ ሁኑ። (ያዕ. 1:19) የሌሎችን ስሜት እንደምትረዱ በሚያሳይ መንገድ ማዳመጣችሁ ለእነሱ ፍቅር እንዳላችሁ ያረጋግጣል። በመንፈስ ጭንቀት የሚሠቃየውን ክርስቲያን ስሜት ለመረዳት የሚያስችሉ ጥያቄዎችን በደግነት መጠየቅ ትችላላችሁ። ይህም ያለበትን ሁኔታ ለመገንዘብና እሱን ለማነጽ ያስችላችኋል። ለግለሰቡ ያላችሁ ልባዊ አሳቢነትና ፍቅር በፊታችሁ ላይ ሊነበብ ይገባል። ግለሰቡ ረዘም ላለ ጊዜ ሊያዋራችሁ ከፈለገ ጣልቃ ሳትገቡ በትዕግሥት አዳምጡት። በትዕግሥት ማዳመጣችሁ የግለሰቡን ስሜት በሚገባ ለመረዳት ያስችላችኋል። በተጨማሪም በጭንቀት የተዋጠው ክርስቲያን እምነት እንዲጥልባችሁና እሱን ለማነጽ የምትናገሩትን ነገር ለማዳመጥ ይበልጥ እንዲነሳሳ ሊያደርገው ይችላል። የምታሳዩት ልባዊ አሳቢነት ሌሎችን በእጅጉ ያጽናናቸዋል።

14. ነቃፊ ላለመሆን መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው?

14 ነቃፊ ላለመሆን ተጠንቀቁ። በመንፈስ ጭንቀት የሚሠቃዩ ሰዎችን መንቀፍ ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ እንደሚባለው ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል፤ እነሱን በፍቅር ለማነጽ የምናደርገውን ልባዊ ጥረትም ከንቱ ያደርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጥበበኞች ምላስ ግን ፈውስ ነው” ይላል። (ምሳሌ 12:18) የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸውን ወንድሞቻችንን ሆን ብለን በቃላት ‘እንደማንወጋቸው’ የታወቀ ነው። ይሁንና ሳይታወቀንም እንኳ ‘ብንወጋቸው’ ስሜታቸው ይደቆሳል። ፍቅር በማሳየት ሌሎችን ማበረታታትና ማነጽ ከፈለግን፣ ስሜታቸውን ለመረዳት እንዲሁም በተቻለ መጠን ራሳችንን በእነሱ ቦታ ለማስቀመጥ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።—ማቴ. 7:12

15. ፍቅር በማሳየት ሌሎችን ለማነጽ ምን ይረዳናል?

15 ሌሎችን ለማጽናናት በአምላክ ቃል ተጠቀሙ። (ሮም 15:4, 5ን አንብብ።) ቅዱሳን መጻሕፍት በእጅጉ የሚያጽናኑ ሐሳቦችን ይዘዋል። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው “ጽናትንና መጽናኛን የሚሰጠው አምላክ” ነው። በእርግጥ የሚያጽናኑ ሐሳቦችን የምናገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ አይደለም። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) እንዲሁም የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች በተባሉት ጽሑፎችም መጠቀም እንችላለን። እነዚህ ጽሑፎች የተለያዩ ችግሮችን ለመቋቋም የሚረዱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችን ለማግኘት ያግዙናል። በእነዚህ መሣሪያዎች መጠቀማችን ፍቅር በማሳየት ሌሎችን ለማነጽ በምናደርገው ጥረት ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ያስችለናል።

16. የመንፈስ ጭንቀት ያለበትን ክርስቲያን ስናበረታታ የትኞቹን ባሕርያት ልናንጸባርቅ ይገባል?

16 ርኅራኄና አሳቢነት አሳዩ። እነዚህ ባሕርያት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር በማሳየት ሌሎችን ማበረታታትና ማነጽ እንድንችል ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ይሖዋ “የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ከመሆኑም ሌላ ለአገልጋዮቹ ‘ከአንጀት ይራራል።’ (2 ቆሮንቶስ 1:3-6ን አንብብ፤ ሉቃስ 1:78፤ ሮም 15:13) ጳውሎስም በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል፤ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የምታጠባ እናት ልጆቿን በፍቅር እንደምትንከባከብ እኛም በመካከላችሁ በነበርንበት ጊዜ በገርነት ተንከባከብናችሁ። በመሆኑም ለእናንተ ጥልቅ ፍቅር ስላለን የአምላክን ምሥራች ለማካፈል ብቻ ሳይሆን ራሳችንን ጭምር ለእናንተ ለመስጠት ቆርጠን ነበር፤ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ እጅግ የተወደዳችሁ ነበራችሁ።” (1 ተሰ. 2:7, 8) እኛም እንደ አምላካችን ለሌሎች አሳቢነት የምናሳይ ከሆነ፣ ይሖዋ በጭንቀት የተዋጠ ሰው ለሚያቀርበው ጸሎት መልስ ለመስጠት ሊጠቀምብን ይችላል።

17. ወንድሞቻችንን በፍቅር ለማነጽ ከፈለግን ምን ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

17 ከወንድሞቻችሁ ፍጽምና አትጠብቁ። ስለ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ምንጊዜም ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖራችሁ ይገባል። የእምነት ባልንጀሮቻችን እንከን የለሽ እንዲሆኑ መጠበቅ ምክንያታዊ አይሆንም፤ ደግሞም እንዲህ ያለው አመለካከት ለብስጭት ይዳርጋል። (መክ. 7:21, 22) ይሖዋ ከአገልጋዮቹ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ እንደሆነ እናስታውስ። እኛም የእሱን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ የሌሎችን አለፍጽምና ችለን መኖር አይከብደንም። (ኤፌ. 4:2, 32) ወንድሞቻችሁ የሚያደርጉት ነገር በቂ እንዳልሆነ እንዲሰማቸው ከማድረግ ይልቅ ላከናወኑት ነገር አመስግኗቸው። ይህ በጣም ያበረታታቸዋል። ወንድሞቻችንን ከልብ ማመስገናችን እነሱን በፍቅር ለማነጽ የሚያስችለን ከመሆኑም ሌላ በቅዱስ አገልግሎታቸው ‘እጅግ የሚደሰቱበት ነገር እንዲያገኙ’ ያደርጋል። የእምነት ባልንጀሮቻችንን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ተስፋ ከማስቆረጥ ይልቅ በዚህ መንገድ ማበረታታቱ ምንኛ የተሻለ ነው!—ገላ. 6:4

18. ፍቅር በማሳየት ሌሎችን ለማነጽ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

18 ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ እያንዳንዱን በግ እጅግ ውድ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል፤ ኢየሱስ ሕይወቱን እንኳ ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቶናል። (ገላ. 2:20) እኛም ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ከልባችን እንወዳቸዋለን። ርኅራኄና ፍቅር ልናሳያቸውም እንፈልጋለን። ለወንድሞቻችን የብርታት ምንጭ መሆን እንድንችል “ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችን የምንተናነጽበትን ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ።” (ሮም 14:19) ሁላችንም ወደፊት ምድር ገነት የምትሆንበትንና ተስፋ የሚያስቆርጥ ምንም ነገር የማይኖርበትን ጊዜ እንናፍቃለን! በዚያ ጊዜ ሕመም፣ ጦርነት፣ ከአዳም የወረስነው ሞት፣ ስደት፣ የቤተሰብ ችግር እንዲሁም ሌሎች የሚያሳዝኑን ነገሮች አይኖሩም። ከሺው ዓመት በኋላ ደግሞ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና ይደርሳሉ። የመጨረሻውን ፈተና የሚያልፉ ሰዎችን ይሖዋ አምላክ እንደ ምድራዊ ልጆቹ አድርጎ የሚቀበላቸው ከመሆኑም ሌላ “የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት” ያገኛሉ። (ሮም 8:21) እንግዲያው ፍቅር በማሳየት ሌሎችን ማነጻችንን እንዲሁም ይህን አስደሳች ሽልማት ሁላችንም ማግኘት እንድንችል እርስ በርስ መተጋገዛችንን እንቀጥል።

^ አን.12 ራሳቸውን ለማጥፋት የሚያስቡ ሰዎችን መርዳት የሚቻልባቸውን መንገዶች ለማወቅ ንቁ! መጽሔት ላይ የወጡትን የሚከተሉትን ርዕሶች ተመልከት፦ “መኖር ምን ዋጋ አለው? ዋጋ እንዳለው የሚያሳዩ ሦስት ምክንያቶች” (ሚያዝያ 2014)፣ “በሕይወት መኖር ሲታክትህ” (ጥር 2012)፣ “በሕይወት መኖርን የመሰለ ነገር የለም” (ኅዳር 2001)።