በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 25

“ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱንም” አታሰናክሉ

“ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱንም” አታሰናክሉ

“ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ።”—ማቴ. 18:10

መዝሙር 113 ከአምላክ ያገኘነው ሰላም

ማስተዋወቂያ *

1. ይሖዋ ለእያንዳንዳችን ምን አድርጎልናል?

ይሖዋ እያንዳንዳችንን ወደ ራሱ ስቦናል። (ዮሐ. 6:44) ይህ ምን ትርጉም እንዳለው እስቲ ቆም ብለህ አስብ። ይሖዋ በዓለም ላይ ያሉትን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲመረምር በአንተ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር አገኘ፤ ቅን ልብ እንዳለህና ለእሱ ፍቅር ማዳበር እንደምትችል አስተዋለ። (1 ዜና 28:9) ይሖዋ አንተን ያውቅሃል፣ ስሜትህን ይረዳልሃል እንዲሁም ይወድሃል። ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው!

2. ኢየሱስ፣ ይሖዋ ለእያንዳንዱ በግ ምን ያህል እንደሚያስብ ለማሳየት የትኛውን ምሳሌ ተጠቅሟል?

2 ይሖዋ ስለ አንተ በጥልቅ ያስባል፤ በተጨማሪም ለሁሉም ክርስቲያን ወንድሞችህና እህቶችህ ያስባል። ኢየሱስ ይህን ነጥብ በምሳሌ ሲያስረዳ ይሖዋን ከእረኛ ጋር አመሳስሎታል። መቶ በጎች ያሉት እረኛ ከመንጋው መካከል አንዷ በግ ብትጠፋ ምን ያደርጋል? እረኛው “99ኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋችውን ለመፈለግ” ይሄዳል። በጓን ሲያገኛትም ቢሆን ከመንጋው ተለይታ በመጥፋቷ አይበሳጭባትም። ከዚህ ይልቅ ስላገኛት በጣም ይደሰታል። ነጥቡ ምንድን ነው? እያንዳንዱ በግ በይሖዋ ፊት ትልቅ ዋጋ አለው። ኢየሱስ “በሰማይ ያለው አባቴ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱም እንኳ እንዲጠፋ አይፈልግም” ብሏል።—ማቴ. 18:12-14

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን የሚያሰናክል ምንም ነገር ማድረግ እንደማንፈልግ ጥርጥር የለውም። ታዲያ ሌሎችን ላለማሰናከል ምን ማድረግ እንችላለን? ደግሞስ አንድ ሰው ቢያስቀይመን ምን ማድረግ ይኖርብናል? በዚህ ርዕስ ውስጥ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ግን በማቴዎስ ምዕራፍ 18 ላይ ‘እነዚህ ትናንሾቹ’ የተባሉት እነማን እንደሆኑ እንመልከት።

‘እነዚህ ትናንሾቹ’ እነማን ናቸው?

4. ‘እነዚህ ትናንሾቹ’ የተባሉት እነማን ናቸው?

4 ‘እነዚህ ትናንሾቹ’ የተባሉት በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ናቸው። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ዕድሜያቸው ምንም ያህል ቢሆን “እንደ ልጆች” ናቸው፤ ምክንያቱም ከኢየሱስ ለመማር ፈቃደኞች ናቸው። (ማቴ. 18:3) አስተዳደጋቸው፣ ባሕላቸው፣ አመለካከታቸው እንዲሁም ባሕርያቸው የተለያየ ቢሆንም እንኳ ሁሉም በክርስቶስ ያምናሉ። እሱም በጣም ይወዳቸዋል።—ማቴ. 18:6፤ ዮሐ. 1:12

5. ይሖዋ አንድ ሰው ከሕዝቦቹ አንዱን ቢያሰናክለው ወይም ጉዳት ቢያደርስበት ምን ይሰማዋል?

5 ‘እነዚህ ትናንሾቹ’ የተባሉት በሙሉ በይሖዋ ዘንድ ውድ ናቸው። ይሖዋ ለእነሱ ያለውን አመለካከት መረዳት እንድንችል እኛ ለልጆች ያለንን አመለካከት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ልጆችን በጣም እንወዳቸዋለን። የአዋቂዎችን ያህል ጥንካሬ፣ ተሞክሮና ጥበብ ስለሌላቸው እንሳሳላቸዋለን። ማንም ሰው ጉዳት እንዲደርስበት ባንፈልግም በተለይ አንድ ሰው ልጆችን ሲጎዳ ብናይ ግን በጣም እናዝናለን፤ ከዚያም አልፎ እንቆጣለን። በተመሳሳይም ይሖዋ ከጉዳት ሊጠብቀን ይፈልጋል። በመሆኑም አንድ ሰው ከሕዝቦቹ አንዱን ሲያሰናክለው ወይም ጉዳት ሲያደርስበት በጣም ያዝናል፤ ከዚያም አልፎ ይቆጣል።—ኢሳ. 63:9፤ ማር. 9:42

6. አንደኛ ቆሮንቶስ 1:26-29 እንደሚጠቁመው ዓለም ለኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን አመለካከት አለው?

6 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደ ‘ትናንሾች’ የሆኑበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው? እስቲ አስበው፦ ዓለም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለማን ነው? ሀብት፣ ዝና እና ሥልጣን ላላቸው ሰዎች ነው። በአንጻሩ ግን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ትልቅ ቦታ የማይሰጣቸውና ከቁጥር የማይገቡ ስለሆኑ በዓለም ዘንድ እንደ ‘ትናንሾች’ ይቆጠራሉ። (1 ቆሮንቶስ 1:26-29ን አንብብ።) ይሖዋ ለእነሱ ያለው አመለካከት ግን ከዚህ የተለየ ነው።

7. ይሖዋ ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ይፈልጋል?

7 ይሖዋ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉትንም ሆነ በቅርቡ ወደ እውነት የመጡ አገልጋዮቹን በሙሉ ይወዳቸዋል። ይሖዋ ሁሉንም ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል፤ እኛም ከፍ አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል። ለተወሰኑ ወንድሞቻችን ብቻ ሳይሆን “ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር” ሊኖረን ይገባል። (1 ጴጥ. 2:17) አቅማችን በፈቀደ መጠን ልንጠነቀቅላቸው እና አሳቢነት ልናሳያቸው ይገባል። አንድን ሰው ቅር እንዳሰኘነው ወይም ስሜቱን እንደጎዳነው ካወቅን ግለሰቡ ‘አትንኩኝ ባይ’ እንደሆነ በማሰብ ጉዳዩን በቸልታ ልናልፈው አይገባም። ይሁንና አንዳንዶች ቶሎ ቅር የሚሰኙት ለምን ሊሆን ይችላል? አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች በአስተዳደጋቸው የተነሳ ራሳቸውን በጣም ዝቅ አድርገው ይመለከታሉ። አንዳንዶች ደግሞ ወደ እውነት የመጡት በቅርቡ ስለሆነ ሌሎች ሲያስቀይሟቸው ጉዳዩን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው አያውቁም። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ሰላም ለመፍጠር የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን። በሌላ በኩል ደግሞ በሌሎች ቶሎ ቅር የሚሰኝ ሰው፣ ይህ ሊያርመው የሚገባ መጥፎ ባሕርይ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርበታል። ይህን ባሕርይ ማረሙ፣ የአእምሮ ሰላም የሚያስገኝለት ከመሆኑም ሌላ ከወንድሞቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረው ያደርጋል።

ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ አስቡ

8. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በዘመኑ በስፋት ይታይ የነበረው የትኛው አመለካከት ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ነበር?

8 ኢየሱስ ‘እነዚህ ትናንሾች’ በማለት ስለጠራቸው ሰዎች ለመናገር የተነሳሳው ለምንድን ነው? ደቀ መዛሙርቱ “በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጠው ማን ነው?” በማለት ስለጠየቁት ነው። (ማቴ. 18:1) በዘመኑ የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን ለሥልጣን እና ለደረጃ ትልቅ ቦታ ይሰጡ ነበር። አንድ ምሁር እንዳሉት “ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ክብር፣ መልካም ስም፣ ታዋቂነት፣ ውዳሴና አክብሮት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን እንኳ ይሰጡ ነበር።”

9. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን ማድረግ ነበረባቸው?

9 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ በአይሁድ ባሕል ውስጥ በስፋት የሚታየውን የፉክክር መንፈስ ከልባቸው ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚኖርባቸው ያውቅ ነበር። “ከእናንተ መካከል ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ ይሁን፤ አመራር የሚሰጥም እንደ አገልጋይ ይሁን” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 22:26) ‘ሌሎች ከእኛ እንደሚበልጡ’ አድርገን የምናስብ ከሆነ ራሳችንን “እንደ ታናሽ” እንደምንቆጥር በተግባር እናሳያለን። (ፊልጵ. 2:3) ይህን አመለካከት ይበልጥ ባዳበርን መጠን ሌሎችን ላለማሰናከል ይበልጥ ጥንቃቄ እናደርጋለን።

10. የትኛውን የጳውሎስ ምክር ልብ ልንለው ይገባል?

10 ሁሉም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በሆነ መንገድ ከእኛ ይበልጣሉ። ባሏቸው መልካም ባሕርያት ላይ የምናተኩር ከሆነ ይህን ማስተዋል አይከብደንም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሰጣቸውን የሚከተለውን ምክር ልብ ልንለው ይገባል፦ “ለመሆኑ አንተን ከሌላው የተለየህ እንድትሆን ያደረገህ ማን ነው? ደግሞስ ያልተቀበልከው ምን ነገር አለ? ከተቀበልክ ደግሞ እንዳልተቀበልክ ሆነህ የምትኩራራው ለምንድን ነው?” (1 ቆሮ. 4:7) ወደ ራሳችን ትኩረት የመሳብ ወይም ከሌሎች እንደምንበልጥ አድርገን የማሰብ ዝንባሌ እንዳይኖረን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ግሩም ንግግር የማቅረብ ችሎታ ያላቸው ወንድሞች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመር ረገድ የተዋጣላቸው እህቶች ለዚህ ችሎታቸው ምንጊዜም ቢሆን ይሖዋ እንዲወደስ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

“ከልባችሁ” ይቅር በሉ

11. ኢየሱስ ስለ አንድ ንጉሥና ስለ ባሪያው ከተናገረው ምሳሌ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው?

11 ኢየሱስ ሌሎችን እንዳያሰናክሉ ለተከታዮቹ ማሳሰቢያ ከሰጣቸው ብዙም ሳይቆይ ስለ አንድ ንጉሥ እና ስለ ባሪያው የሚገልጽ ምሳሌ ነገራቸው። ባሪያው መቼም ቢሆን ሊከፍለው የማይችል ብዙ ዕዳ ነበረበት፤ ንጉሡም ዕዳውን ሰረዘለት። በኋላ ላይ ግን ይኸው ባሪያ፣ ከእሱ በጣም ያነሰ ዕዳ ለነበረበት ሌላ ባሪያ ምሕረት ለማሳየት ፈቃደኛ አልሆነም። በመጨረሻም ንጉሡ ምሕረት ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆነውን ባሪያ ወደ ወህኒ ጣለው። ነጥቡ ምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተም እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ በሰማይ ያለው አባቴ እንደዚሁ ያደርግባችኋል።”—ማቴ. 18:21-35

12. ይቅር ለማለት ፈቃደኛ አለመሆናችን ሌሎችን የሚጎዳው እንዴት ነው?

12 ባሪያው ምሕረት ባለማድረጉ የጎዳው ራሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ጭምር ነው። በመጀመሪያ፣ ከእሱ የተበደረው ባሪያ “ያለበትን ዕዳ እስኪከፍል ድረስ ወህኒ ቤት” በማሳሰር ደግነት የጎደለው ድርጊት ፈጽሞበታል። ሁለተኛ፣ ሁኔታውን በተመለከቱ ሌሎች ባሪያዎችም ላይ ጉዳት አድርሷል። ኢየሱስ፣ “ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሪያዎች የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ አዘኑ” ብሏል። በተመሳሳይም የእኛ ድርጊት ሌሎችን ሊጎዳ ይችላል። የበደለንን ሰው ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ባንሆን ምን ሊፈጠር ይችላል? በመጀመሪያ ለወንድማችን ይቅርታ፣ ትኩረትና ፍቅር መንፈጋችን እሱን ይጎዳዋል። ሁለተኛ፣ ከወንድማችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የሌለን መሆኑ በጉባኤያችን ያሉ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች እንዲሳቀቁ ያደርጋል።

ቂም ትይዛለህ ወይስ ከልብህ ይቅር ትላለህ? (ከአንቀጽ 13-14⁠ን ተመልከት) *

13. ከአንዲት አቅኚ ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

13 ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይቅር ስንል፣ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን እንጠቅማለን። ክሪስታል * የተባለች አንዲት አቅኚ ይህን በሕይወቷ ተመልክታለች። በጉባኤዋ ያለች አንዲት እህት ስሜቷን ጎድታው ነበር። ክሪስታል እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ የምትናገረኝ ደግነት የጎደለው ነገር እንደ ስለት ይወጋኝ ነበር። ከእሷ ጋር ማገልገል እንኳ አስጠላኝ። ቅንዓቴና ደስታዬ ጠፋ።” ክሪስታል በዚህች እህት ለመበሳጨት የሚያበቃ ምክንያት እንዳላት ተሰምቷት ነበር። ሆኖም ክሪስታል ቂም አልያዘችም፤ ወይም በደረሰባት ጉዳት ላይ ብቻ አላተኮረችም። በጥቅምት 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ላይ በወጣው “ከልባችሁ ይቅር በሉ” በሚለው ርዕስ ላይ የሚገኘውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በትሕትና ተግባራዊ አደረገች። ያስቀየመቻትን እህት ይቅር አለቻት። ክሪስታል እንዲህ ብላለች፦ “ሁላችንም አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ጥረት እያደረግን እንዳለንና ይሖዋ በየዕለቱ በነፃ ይቅር እንደሚለን ተገንዝቤያለሁ። ከላዬ ላይ ትልቅ ሸክም እንደወረደልኝ ሆኖ ተሰምቶኛል። ደስታዬንም መልሼ ማግኘት ችያለሁ።”

14. ከማቴዎስ 18:21, 22 መረዳት እንደሚቻለው ሐዋርያው ጴጥሮስ ምን ተሰምቶት ሊሆን ይችላል? ኢየሱስ ለጴጥሮስ ከሰጠው ምላሽ ምን ትምህርት እናገኛለን?

14 የበደሉንን ይቅር ማለት እንዳለብን እናውቃለን፤ ትክክለኛው እርምጃ ይህ ነው። ይሁንና ይህን ማድረግ ይከብደን ይሆናል። ሐዋርያው ጴጥሮስም እንዲህ የተሰማው ጊዜ ሳይኖር አይቀርም። (ማቴዎስ 18:21, 22ን አንብብ።) ታዲያ ይቅር ለማለት ምን ሊረዳን ይችላል? በመጀመሪያ፣ ይሖዋ ስንት ጊዜ ይቅር እንዳለህ አሰላስል። (ማቴ. 18:32, 33) ይቅርታው የሚገባን ሰዎች ባንሆንም በነፃ ይቅር ይለናል። (መዝ. 103:8-10) “እኛም እርስ በርሳችን የመዋደድ ግዴታ አለብን።” በመሆኑም ይቅር ማለት ለምርጫ የተተወ ነገር አይደለም። ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይቅር ማለት ግዴታ ነው። (1 ዮሐ. 4:11) ሁለተኛ፣ ይቅር ማለት በሚያስገኘው ጥቅም ላይ አሰላስል። ይቅር ማለታችን የበደለንን ሰው ያስደስተዋል፤ የጉባኤውን አንድነት ለመጠበቅ ያስችላል፤ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ይዘን ለመቀጠል ያስችለናል፤ እንዲሁም ከላያችን ላይ ትልቅ ሸክም የወረደልን ያህል ሆኖ እንዲሰማን ያደርጋል። (2 ቆሮ. 2:7፤ ቆላ. 3:14) ሦስተኛ፣ ይቅር እንድንል መመሪያ ወደሰጠን አምላክ ጸልይ። ሰይጣን ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር ያለህን ሰላም እንዲያደፈርሰው አትፍቀድ። (ኤፌ. 4:26, 27) ሰይጣን በዚህ ረገድ እንዳይሳካለት የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል።

አትሰናከሉ

15. አንድ ወንድማችን ወይም እህታችን ያደረጉት ነገር ቅር ቢያሰኘን በቆላስይስ 3:13 መሠረት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

15 አንድ የእምነት ባልንጀራህ ያደረገው ነገር በጣም ቢያስከፋህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ሰላም ለመፍጠር የምትችለውን ሁሉ አድርግ። ለይሖዋ የልብህን አውጥተህ ንገረው። ቅር ያሰኘህን ሰው በተመለከተ ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ እንዲሁም የግለሰቡን መልካም ባሕርያት ይኸውም በይሖዋ ዘንድ ተወዳጅ ያደረጉትን ባሕርያት ለማየት እንዲረዳህ ጸልይ። (ሉቃስ 6:28) ወንድምህ ያደረሰብህን በደል ችለህ ማለፍ ከከበደህ እንዴት ብታነጋግረው የተሻለ እንደሚሆን ቆም ብለህ አስብ። ምንጊዜም ቢሆን፣ ወንድምህ የጎዳህ ሆን ብሎ እንዳልሆነ ማሰቡ የተሻለ ነው። (ማቴ. 5:23, 24፤ 1 ቆሮ. 13:7) ወንድምህን የምታነጋግረው ስለ እሱ መጥፎ አመለካከት ይዘህ መሆን የለበትም። ይሁንና ወንድምህ ሰላም ለመፍጠር ፈቃደኛ ባይሆንስ? ወንድምህን ‘ለመቻል’ ጥረት ማድረግህን ቀጥል። በወንድምህ ተስፋ አትቁረጥበት። (ቆላስይስ 3:13ን አንብብ።) ከሁሉ በላይ ደግሞ ፈጽሞ ቂም አትያዝ፤ ምክንያቱም ቂም መያዝ ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት ያበላሸዋል። ምንም ነገር እንዲያሰናክልህ አትፍቀድ። ይህን ስታደርግ ከማንኛውም ነገር በላይ ይሖዋን እንደምትወደው ታሳያለህ።—መዝ. 119:165

16. እያንዳንዳችን ምን ኃላፊነት አለብን?

16 ‘በአንድ እረኛ’ ሥር ያለ “አንድ መንጋ” ሆነን ይሖዋን በአንድነት የማገልገል መብታችንን ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን! (ዮሐ. 10:16) የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የተባለው መጽሐፍ ገጽ 165 እንዲህ ይላል፦ “በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ካለው አንድነት እየተጠቀምክ በመሆኑ ይህ አንድነት ተጠብቆ እንዲቆይ የበኩልህን አስተዋጽኦ የማድረግ ኃላፊነት አለብህ።” በመሆኑም “ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን . . . ይሖዋ በሚያያቸው መንገድ ለማየት ጥረት” ማድረግ ይኖርብናል። ይሖዋ ሁላችንንም እንደ ‘ትናንሽ’ ልጆች ውድ አድርጎ ይመለከተናል። አንተስ ወንድሞችህን እና እህቶችህን ውድ እንደሆኑ አድርገህ ትመለከታቸዋለህ? ይሖዋ እነሱን ለመርዳትና ለመንከባከብ የምታደርገውን ማንኛውንም ነገር ያስተውላል እንዲሁም ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—ማቴ. 10:42

17. ቁርጥ ውሳኔያችን ምንድን ነው?

17 የእምነት ባልንጀሮቻችንን በጣም እንወዳቸዋለን። በመሆኑም “በአንድ ወንድም ፊት የሚያደናቅፍ ወይም የሚያሰናክል ነገር ላለማስቀመጥ ቁርጥ ውሳኔ” አድርገናል። (ሮም 14:13) ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ከእኛ እንደሚበልጡ አድርገን እናስባለን፤ እንዲሁም ከልባችን ይቅር እንላቸዋለን። በተጨማሪም ማንም ሰው እንዲያሰናክለን አንፍቀድ። ከዚህ በተቃራኒ “ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችን የምንተናነጽበትን ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ።”—ሮም 14:19

መዝሙር 130 ይቅር ባይ ሁኑ

^ አን.5 ፍጹማን ባለመሆናችን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን የሚጎዳ ነገር የምንናገርበት ወይም የምናደርግበት ጊዜ ይኖራል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር ምን ማድረግ ይኖርብናል? ሰላም ለመፍጠር ቶሎ እርምጃ እንወስዳለን? ሳንውል ሳናድር ይቅርታ እንጠይቃለን? ወይስ ‘ቢቀየሙም ይህ የእነሱ ችግር ነው እንጂ የእኔ ችግር አይደለም’ ብለን እናስባለን? በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች በተናገሩት ወይም ባደረጉት ነገር ቶሎ መቀየም የሚቀናን ሰው ብንሆንስ? ‘እንግዲህ ይሄ ተፈጥሮዬ ነው፤ ምንም ማድረግ አልችልም’ የሚል ሰበብ እናቀርባለን? ወይስ ይህ ዓይነቱን ባሕርይ ልናስወግደው የሚገባ ድክመት እንደሆነ አድርገን እንመለከተዋለን?

^ አን.13 ስሟ ተቀይሯል።

^ አን.54 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት በጉባኤዋ ባለች ሌላ እህት ቅር ተሰኝታለች። ሁለቱ እህቶች ጉዳዩን በግል ከተነጋገሩበት በኋላ ችግሩን ፈትተው አብረው በደስታ ሲያገለግሉ።