በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋን ለማስቀደም ስል የወሰድኳቸው እርምጃዎች

ይሖዋን ለማስቀደም ስል የወሰድኳቸው እርምጃዎች

ወቅቱ 1984 ነው፤ የጠዋቷ ፀሐይ ፍንትው ብላ ወጥታለች። በካራካስ፣ ቬኔዙዌላ በሀብታሞች ሰፈር ከሚገኘው ምቹ ቤታችን ወጥቼ ወደ ሥራ እየሄድኩ ነበር። መንገድ ላይ ሳለሁ በቅርቡ በወጣ አንድ መጠበቂያ ግንብ ላይ ስላነበብኩት ርዕስ ማሰላሰል ጀመርኩ። ርዕሱ፣ ጎረቤቶቻችን ስለ እኛ ያላቸውን አመለካከት እንድናስብበት የሚያበረታታ ነበር። በሰፈራችን ያሉትን ቤቶች እያየሁ ‘ጎረቤቶቼ የሚመለከቱኝ እንደ አንድ ስኬታማ የባንክ ሠራተኛ ብቻ አድርገው ነው? ወይስ ባንክ ውስጥ እየሠራ ቤተሰቡን እንደሚያስተዳድር የአምላክ አገልጋይ አድርገው ይመለከቱኛል?’ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። የዚህ ጥያቄ መልስ ስላላስደሰተኝ ሁኔታዬን ለመቀየር አንዳንድ እርምጃዎችን ለመውሰድ ተነሳሳሁ።

የተወለድኩት ግንቦት 19, 1940 ሊባኖስ ውስጥ በሚገኘው አሚዩን ከተማ ነው። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ቤተሰባችን ወደ ትሪፖሊ ከተማ ተዛወረ፤ ያደግኩት ይሖዋ አምላክን በሚያውቅና በሚወድ ፍቅርና ደስታ የሰፈነበት ቤተሰብ ውስጥ ነው። ከአምስት ልጆች መካከል የመጨረሻው ነኝ፤ ሦስት እህቶችና አንድ ወንድም አለኝ። ወላጆቼ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለገንዘብ አልነበረም፤ በቤተሰባችን ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እና ሰዎች ስለ አምላክ እንዲያውቁ ለመርዳቱ ሥራ ነበር።

በጉባኤያችን ውስጥ በርካታ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነበሩ። ከእነሱ መካከል አንዱ ሚሼል አቡድ ነበር፤ በወቅቱ መጽሐፍ ጥናት ተብሎ የሚጠራውን ስብሰባ የሚመራው እሱ ነበር። ይህ ወንድም እውነትን የሰማው ኒው ዮርክ ውስጥ ሲሆን በ1920ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ እውነትን ወደ ሊባኖስ ያመጣው እሱ ነው። ይህ ወንድም ከጊልያድ ትምህርት ቤት ለተመረቁ ሁለት ወጣቶች ያሳይ የነበረውን አክብሮትና አሳቢነት አልረሳውም፤ እነዚህ እህቶች አን ቢቨር እና ግዌን ቢቨር ይባላሉ። ከእኛ ጋር በጣም እንቀራረብ ነበር። ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በኋላ አንን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሳገኛት በጣም ተደሰትኩ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ግዌንን አገኘኋት፤ እሷም ዊልፍሬድ ጉች የሚባል ወንድም አግብታ ለንደን፣ እንግሊዝ በሚገኘው ቤቴል ውስጥ እያገለገለች ነበር።

ሊባኖስ ውስጥ ማገልገል

ልጅ ሳለሁ በሊባኖስ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ጥቂት ነበሩ። ያም ቢሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘነውን ትምህርት በቅንዓት ለሌሎች እናካፍል ነበር። አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ከባድ ተቃውሞ ቢያደርሱብንም እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ አላልንም። በወቅቱ ካጋጠሙን ከአእምሮዬ የማይጠፉ ክንውኖች አንዳንዶቹን ላጫውታችሁ።

አንድ ቀን እኔ እና ሳና የተባለችው እህቴ በአንድ አፓርታማ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እየሰበክን ነበር። አንድ ቄስ ወደምናገለግልበት ፎቅ መጣ። የመጣው የሆነ ሰው ጠርቶት ይመስለኛል። ቄሱ እህቴን መስደብ ጀመረ። እንዲያውም በኃይል ገፍትሮ ከደረጃው ላይ ቁልቁል ጣላት፤ እሷም ጉዳት ደረሰባት። በዚህ ጊዜ አንድ ሰው ስልክ ደውሎ ፖሊስ ጠራ፤ ፖሊሶቹም መጥተው በደግነት ሳናን ረዷት። ቄሱን ደግሞ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱት፤ እዚያም ሲፈትሹት ሽጉጥ እንደያዘ አወቁ። በዚህ ጊዜ የፖሊስ አዛዡ “ለመሆኑ አንተ ምንድን ነህ? የሃይማኖት መሪ ነህ ወይስ የወንበዴዎች መሪ?” አለው።

የማልረሳው ሌላም አጋጣሚ አለ፤ በጉባኤ ደረጃ አውቶቡስ ተከራይተን ምሥራቹን ለመስበክ ወደ አንድ ራቅ ያለ ከተማ ሄደን ነበር። በጣም ጥሩ ጊዜ እያሳለፍን ነበር፤ በኋላ ግን አንድ ቄስ ምን እያደረግን እንዳለ ሰማና ሕዝብ ሰብስቦ ረብሻ ቀሰቀሰ። ሰዎቹ አንገላቱን፤ እንዲሁም ድንጋይ ወረወሩብን፤ በዚህም ምክንያት አባቴ ጉዳት ደረሰበት። ፊቱ ደም በደም ሆኖ እንደነበር ትዝ ይለኛል። አባቴና እናቴ ወደ አውቶቡሱ ተመለሱ፤ ሌሎቻችንም ተከተልናቸው። በሁኔታው በጣም ተረብሸን ነበር። ሆኖም እናቴ የአባቴን ደም እየጠራረገችለት ሳለ ምን እንዳለች ፈጽሞ አልረሳውም፤ “ይሖዋ ሆይ፣ የሚያደርጉትን ስለማያውቁ እባክህ ይቅር በላቸው” ትል ነበር።

በሌላ ወቅት ደግሞ ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደ ትውልድ አካባቢያችን ሄደን ነበር። እዚያም ታዋቂ የሆነ አንድ ቄስ አያቴ ቤት አገኘን። ቄሱ ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ያውቅ ነበር። በወቅቱ ገና ስድስት ዓመቴ የነበረ ቢሆንም እኔን መርጦ በጥያቄ አፋጠጠኝ። “አንተ፣ ለምንድን ነው ያልተጠመቅከው?” አለኝ። እኔም ገና ልጅ እንደሆንኩና ለመጠመቅ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ እንዲሁም ጠንካራ እምነት ማዳበር እንደሚያስፈልገኝ ነገርኩት። ቄሱ በመልሴ ስላልተደሰተ አክብሮት እንዳላሳየሁት በመግለጽ ለአያቴ ከሰሰኝ።

እርግጥ እንዲህ ዓይነት ተቃውሞ የሚያጋጥመን ከስንት አንዴ ነበር። በጥቅሉ ሲታይ ሊባኖሳውያን ሰው ወዳድ እና እንግዳ ተቀባዮች ናቸው። በመሆኑም ከብዙ ሰዎች ጋር አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቶችን አድርገናል፤ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም ነበሩን።

ቤተሰባችን ወደ ሌላ አገር ለመዛወር ወሰነ

ተማሪ እያለሁ አንድ ወጣት ወንድም ከቬኔዙዌላ ወደ ሊባኖስ መጣ። እኛ ጉባኤ ይሰበሰብ የነበረ ሲሆን ዋፋ ከተባለችው እህቴ ጋር መጠናናት ጀመሩ። ከጊዜ በኋላም ተጋቡና ወደ ቬኔዙዌላ ሄዱ። ዋፋ በምትጽፍልን ደብዳቤዎች ላይ አባቴ መላውን ቤተሰብ ይዞ ወደ ቬኔዙዌላ እንዲዛወር ትወተውተው ነበር። እንዲህ ያደረገችው በጣም ስለናፈቅናት ነው። ውሎ አድሮ ሐሳቧ ተሳካላትና ወደ ቬኔዙዌላ ተዛወርን!

ወደ ቬኔዙዌላ የሄድነው በ1953 ነው፤ በካራካስ በፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ መኖር ጀመርን። በወቅቱ ልጅ ስለነበርኩ ፕሬዚዳንቱ አንዳንድ ጊዜ በውድ መኪናው ሲያልፍ ማየት በጣም ያስደስተኝ ነበር። ወላጆቼ ግን ከአዲስ አገር፣ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ምግብ እና የአየር ሁኔታ ጋር መላመድ ከብዷቸው ነበር። ገና ከሁኔታው ጋር ለመላመድ ጥረት እያደረጉ ሳሉ ቤተሰባችን በጣም አስደንጋጭ ነገር አጋጠመው።

ከግራ ወደ ቀኝ፦ አባቴ፤ እናቴ፤ እኔ በ1953 ቤተሰባችን ወደ ቬኔዙዌላ በተዛወረበት ወቅት

አሳዛኝ ነገር አጋጠመን

በድንገት አባቴ መታመም ጀመረ። አባቴ በጣም ጠንካራና ጤናማ ሰው ስለነበር ይህ እንግዳ ሆነብን። ከዚያ በፊት አባቴ የታመመበትን ጊዜ አላስታውስም። በኋላም ካንሰር እንዳለበት ታወቀና ቀዶ ሕክምና ተደረገለት። የሚያሳዝነው ከአንድ ሳምንት በኋላ ሕይወቱ አለፈ።

በዚያ ወቅት የተሰማንን ሐዘን ለመግለጽ ቃላት ያጥሩኛል። ያኔ ገና 13 ዓመቴ ነበር። በጣም ደነገጥን፤ ሰማይ ምድሩ ዞረብን። እናቴ ባለቤቷ መሞቱን ለመቀበል ረጅም ጊዜ ወስዶባታል። እያደር ግን ሁኔታውን መቀበል እንዳለብን ተገነዘብን፤ ደግሞም በይሖዋ እርዳታ ይህን ማድረግ ችለናል። በ16 ዓመቴ በካራካስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቀቅኩ፤ በወቅቱ ቤተሰቤን በቁሳዊ የመደገፍ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ።

እህቴ ሳና እና ባለቤቷ ሩበን መንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ በእጅጉ ረድተውኛል

በዚህ መሃል እህቴ ሳና፣ ከጊልያድ ተመርቆ ወደ ቬኔዙዌላ የተመለሰውን ሩበን አራውሆን አግብታ ነበር። ሳና እና ባለቤቷ ወደ ኒው ዮርክ ለመዛወር ወሰኑ። ቤተሰቤ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ እንድማር ስለወሰነ ኒው ዮርክ ሄጄ ከእህቴና ከባለቤቷ ጋር እየኖርኩ እዚያው መማር ጀመርኩ። እህቴና ባለቤቷ አብሬያቸው እኖር በነበረበት ጊዜ መንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ በጣም ረድተውኛል። በተጨማሪም በብሩክሊን በሚገኘው የስፓንኛ ጉባኤያችን ውስጥ በርካታ የጎለመሱ ወንድሞች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል ሁለቱ በብሩክሊን ቤቴል ያገለግሉ የነበሩት ሚልተን ሄንሸል እና ፍሬድሪክ ፍራንዝ ናቸው፤ ከእነሱ ጋር በመተዋወቄ በጣም ደስተኛ ነኝ።

በ1957 ስጠመቅ

በኒው ዮርክ የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ለማጠናቀቅ ስቃረብ ሕይወቴን እየመራሁ ስላለሁበት መንገድ ማሰብ ጀመርኩ። ክርስቲያኖች ትርጉም ያለው ግብ እንዲያወጡ የሚያበረታቱ የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶችን አንብቤ እና ስለ ጉዳዩ በጥልቀት አሰላስዬ ነበር። በጉባኤያችን ያሉ አቅኚዎችና ቤቴላውያን ምን ያህል ደስተኛ እንደሆኑም እመለከት ነበር፤ እኔም እንደ እነሱ ለመሆን ተመኘሁ። ሆኖም በወቅቱ ገና አልተጠመቅኩም ነበር። ራሴን ለይሖዋ መወሰን እንዳለብኝ ብዙም ሳይቆይ ተገነዘብኩ። በመሆኑም ራሴን ወስኜ መጋቢት 30, 1957 ተጠመቅኩ።

ትላልቅ ውሳኔዎች

ይህን ወሳኝ እርምጃ ከወሰድኩ በኋላ ስለ ቀጣዩ እርምጃ ማለትም የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስለመጀመር ማሰብ ጀመርኩ። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ያለኝ ፍላጎት እየጨመረ መጥቶ ነበር። ሆኖም እንዲህ ያለውን እርምጃ መውሰድ ቀላል እንደማይሆን ተገንዝቤ ነበር። አቅኚነቴን እና የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን አንድ ላይ ማስኬድ የምችለው እንዴት ነው? ትምህርቴን አቁሜ ወደ ቬኔዙዌላ መመለስና በአቅኚነት ማገልገል እንደምፈልግ ቬኔዙዌላ ላሉት ቤተሰቦቼ ለማስረዳት ብዙ ደብዳቤዎችን መለዋወጥ ነበረብን።

ሰኔ 1957 ወደ ካራካስ ተመለስኩ። ሆኖም ቤተሰቦቼ ያሉበት የኢኮኖሚ ሁኔታ ጥሩ አልነበረም። ተጨማሪ ገቢ የሚያመጣ ሰው ያስፈልግ ነበር። ታዲያ ልረዳቸው የምችለው እንዴት ነው? በአንድ ባንክ ውስጥ ሥራ አገኘሁ፤ ግን አቅኚ መሆን በጣም እፈልግ ነበር። ደግሞም ወደ ቬኔዙዌላ የተመለስኩት ለዚሁ ዓላማ ነው። ስለዚህ ሁለቱንም ለማድረግ ወሰንኩ። ለበርካታ ዓመታት ባንኩ ውስጥ የሙሉ ጊዜ ሥራ እየሠራሁ በአቅኚነት አገለግል ነበር። በሕይወቴ ውስጥ በጣም ሥራ የበዛብኝም፣ በጣም ደስተኛ የነበርኩበትም ጊዜ ያ ነው!

ደስታዬን የጨመረው ሌላው ነገር ደግሞ ሲልቪያ የተባለች ይሖዋን ከልቧ የምትወድ ውብ እህት ማግባቴ ነው። ሲልቪያ ጀርመናዊት ስትሆን ወደ ቬኔዙዌላ የመጣችው ከወላጆቿ ጋር ነው። ከጊዜ በኋላ ሁለት ልጆች ወለድን፤ ወንድ ልጃችን ሚሼል (ማይክ) ይባላል፤ ሴት ልጃችን ደግሞ ሰሚራ ትባላለች። እናቴ አብራን መኖር ስለጀመረች እሷንም መንከባከብ ጀመርኩ። የቤተሰብ ኃላፊነቴን ለመወጣት ስል የአቅኚነት አገልግሎቴን ማቆም ቢያስፈልገኝም የአቅኚነት መንፈስ ይዤ ቀጠልኩ። እኔና ሲልቪያ እረፍት በምናገኝበት ጊዜ በረዳት አቅኚነት እናገለግል ነበር።

ሌላ መሠረታዊ እርምጃ

በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ የጠቀስኩት ሁኔታ የተፈጠረው ልጆቼ ገና ተማሪዎች እያሉ ነው። እውነቱን ለመናገር በወቅቱ ኑሮዬ በጣም የተመቻቸ ነበር፤ አብረውኝ የሚሠሩት ሰዎችም ያከብሩኝ ነበር። ያም ቢሆን በዋነኝነት መታወቅ የምፈልገው በይሖዋ አገልጋይነቴ ነበር። ያን ቀን የመጣብኝ ሐሳብ ከአእምሮዬ ሊወጣ አልቻለም። ስለዚህ እኔና ባለቤቴ ቁጭ ብለን ስለ ገቢና ስለ ወጪያችን ተነጋገርን። የባንክ ሥራዬን ባቆም ዳጎስ ያለ የስንብት ክፍያ ይሰጠኛል። ምንም ዕዳ ስላልነበረብን ኑሯችንን ቀላል ካደረግን ለረጅም ጊዜ የሚያኖረን በቂ ገንዘብ እንደሚኖረን አሰላን።

ይህን እርምጃ መውሰድ ቀላል አልነበረም። ሆኖም ውዷ ባለቤቴ እና እናቴ ውሳኔዬን ሙሉ በሙሉ ደገፉት። በመሆኑም በድጋሚ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የመሆን አጋጣሚ ላገኝ ነው። በጣም ተደስቼ ነበር! ሁሉ ነገር የተስተካከለ ይመስል ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን አንድ ያልተጠበቀ ዜና ደረሰን።

ያልተጠበቀ ደስታ!

ሦስተኛው ልጃችን ጋብርኤል መወለዱ ያልተጠበቀ አስደሳች ክንውን ነበር

ሐኪማችን ሲልቪያ እርጉዝ መሆኗን ነገረን። ይህ ሁለታችንም ያልጠበቅነው ዜና ነበር! በዜናው በጣም ተደሰትን፤ ግን አቅኚ ለመሆን ወስኜ ስለነበር ሁኔታው አሳሰበኝ። በውሳኔዬ መጽናት እችል ይሆን? አዲሱን የቤተሰባችንን አባል ለመቀበል ወዲያውኑ አእምሯዊና ስሜታዊ ዝግጅት አደረግን። ያ ሁሉ ዝርዝር ዕቅድ ግን ምን ሊሆን ነው?

ምን ማድረግ እንዳለብን ከተነጋገርን በኋላ ባወጣነው ዕቅድ ለመጽናት ወሰንን። ሚያዝያ 1985 ልጃችን ጋብርኤል ተወለደ። ያም ቢሆን ሰኔ 1985 የባንክ ሥራዬን አቁሜ እንደገና የዘወትር አቅኚ ሆንኩ። ከጊዜ በኋላ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ የማገልገል መብት አገኘሁ። ሆኖም ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኘው ካራካስ ውስጥ አልነበረም፤ ስለዚህ በሳምንት ሁለት ወይም ሦስት ቀን 80 ኪሎ ሜትር ተጉዤ ወደ ቤቴል መሄድ ነበረብኝ።

እንደገና ወደ ሌላ ቦታ ተዛወርን

ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኘው በላ ቪክቶሪያ ነበር፤ ስለዚህ ወደ ቤቴል ቀረብ ለማለት ስንል በቤተሰብ ደረጃ ወደ ላ ቪክቶሪያ ለመዛወር ወሰንን። ይህ ለሁላችንም ትልቅ ለውጥ ነበር። ቤተሰቤ በጣም ተባባሪ ነበር። ለእነሱ ያለኝን አድናቆትና ምስጋና መግለጽ እፈልጋለሁ። እህቴ ባሃ እናቴን የመንከባከቡን ኃላፊነት ለመረከብ ፈቃደኛ ነበረች። በወቅቱ ማይክ ትዳር መሥርቶ ነበር፤ ሰሚራ እና ጋብርኤል ግን ገና ራሳቸውን አልቻሉም ነበር። ስለዚህ ወደ ላ ቪክቶሪያ ስንዛወር በካራካስ ከነበሩት ጓደኞቻቸው መለየት አስፈልጓቸዋል። ውዷ ባለቤቴ ሲልቪያም ሞቅ ባለ ከተማ ውስጥ የነበረንን ኑሮ ትታ በትንሽ ከተማ መኖርን መልመድ ጠይቆባታል። ደግሞም ሁላችንም አነስ ባለ ቤት መኖር አስፈልጎናል። በእርግጥም ከካራካስ ወደ ላ ቪክቶሪያ ለመዛወር ያደረግነው ውሳኔ ብዙ ለውጥ ጠይቆብናል።

ከዚያ ደግሞ ሁኔታዎች በድጋሚ ተቀየሩ። ጋብርኤል ትዳር መሠረተ፤ ሰሚራም ራሷን ችላ መኖር ጀመረች። ከዚያ እኔና ሲልቪያ በ2007 ቤቴል እንድንገባ ተጋበዝን፤ አሁንም ድረስ እዚያ እያገለገልን ነው። ትልቁ ልጃችን ማይክ የጉባኤ ሽማግሌ ከመሆኑም ሌላ ከባለቤቱ ከሞኒካ ጋር በአቅኚነት እያገለገለ ነው። ጋብርኤልም የጉባኤ ሽማግሌ ነው፤ ከባለቤቱ ከአምብራ ጋር ጣሊያን ውስጥ ያገለግላሉ። ሰሚራም አቅኚ ከመሆኗ በተጨማሪ በቤቴል የርቀት ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆና ታገለግላለች።

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ከባለቤቴ ከሲልቪያ ጋር በቬኔዙዌላ ቅርንጫፍ ቢሮ፤ ትልቁ ልጃችን ማይክ እና ባለቤቱ ሞኒካ፤ ሴት ልጃችን ሰሚራ፤ ልጃችን ጋብርኤል እና ባለቤቱ አምብራ

በወሰድኳቸው እርምጃዎች ቅንጣት ታክል አልቆጭም

በሕይወቴ ውስጥ ብዙ ለውጦችን አስተናግጃለሁ። ሆኖም ባደረግኳቸው ውሳኔዎች ፈጽሞ አልቆጭም። ሌላ ዕድል ቢሰጠኝ እንኳ እነዚህኑ ውሳኔዎች ማድረጌ አይቀርም። በይሖዋ አገልግሎት ያገኘኋቸውን የተለያዩ ኃላፊነቶችና መብቶች በእጅጉ አደንቃለሁ። ከይሖዋ ጋር ምንጊዜም ጠንካራ ወዳጅነት ይዞ መቀጠል ያለውን አስፈላጊነት በሕይወቴ ተመልክቻለሁ። የምንወስዳቸው እርምጃዎች ትናንሽም ይሁኑ ትላልቅ፣ ይሖዋ “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ” የሆነውን ሰላሙን ይሰጠናል። (ፊልጵ. 4:6, 7) እኔ እና ሲልቪያ በቤቴል በምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎት በጣም ደስተኞች ነን፤ እንዲሁም ይሖዋን ለማስቀደም ስንል እርምጃዎች በመውሰዳችን በጣም እንደተባረክን ይሰማናል።