የጥላቻን ሰንሰለት መበጠስ የሚቻለው እንዴት ነው?
4 | በአምላክ እርዳታ ጥላቻን ድል አድርግ
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፦
“የመንፈስ ፍሬ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው።”—ገላትያ 5:22, 23
ምን ማለት ነው?
በአምላክ እርዳታ የጥላቻን ሰንሰለት መበጠስ እንችላለን። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በራሳችን ልናዳብር የማንችላቸውን ግሩም ባሕርያት እንድናፈራ ያስችለናል። ስለዚህ በራሳችን ኃይል ጥላቻን ለማሸነፍ ከመሞከር ይልቅ በአምላክ እርዳታ መታመናችን የተሻለ ነው። እንዲህ ካደረግን የሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ስሜት ይኖረናል፤ ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ” በማለት ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:13) በእርግጥም “እኔን የሚረዳኝ . . . ይሖዋ ነው” ማለት እንችላለን።—መዝሙር 121:2
ምን ማድረግ ትችላለህ?
“ግልፍተኛ የነበርኩት ሰው ተለውጬ ሰላማዊ እንድሆን ይሖዋ ረድቶኛል።”—ዎልዶ
ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጥህ ከልብህ ጸልይ። (ሉቃስ 11:13) ግሩም ባሕርያትን ለማዳበር እንዲረዳህ ጠይቀው። መጽሐፍ ቅዱስ ጥላቻን ለማሸነፍ ስለሚረዱ ባሕርያት ምን እንደሚል አጥና፤ ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ፍቅር፣ ሰላም፣ ትዕግሥትና ራስን መግዛት ይገኙበታል። እነዚህን ባሕርያት ማንጸባረቅ የምትችልባቸውን አጋጣሚዎች ፈልግ። በተጨማሪም እነዚህን ባሕርያት ለማዳበር ጥረት ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ጊዜ አሳልፍ። እንዲህ ያሉ ሰዎች “ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች” እንድትነቃቃ ይረዱሃል።—ዕብራውያን 10:24