የጥላቻን ሰንሰለት መበጠስ የሚቻለው እንዴት ነው?
2 | አትበቀል
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፦
‘ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ። ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። ራሳችሁ አትበቀሉ፤ “‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ይሖዋ” ተብሎ ተጽፏል።’—ሮም 12:17-19
ምን ማለት ነው?
ስንበደል መበሳጨታችን የማይቀር ቢሆንም አምላክ እንድንበቀል አልፈቀደልንም። ከዚህ ይልቅ፣ እሱ በቅርቡ ሁሉንም ነገር ስለሚያስተካክል እስከዚያ ጊዜ ድረስ በትዕግሥት እንድንጠባበቅ አሳስቦናል።—መዝሙር 37:7, 10
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ሲበቀሉ የጥላቻ ሰንሰለት እየረዘመ ይሄዳል። በመሆኑም አንድ ሰው ቅር ካሰኘህ ወይም ከጎዳህ አጸፋውን አትመልስ። ራስህን ለመቆጣጠርና ሰላማዊ ምላሽ ለመስጠት ጥረት አድርግ። አንዳንድ ጊዜ ጉዳዩን ችላ ብሎ ማለፉ የተሻለ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 19:11) እርግጥ ነው፣ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ትመርጥ ይሆናል። ለምሳሌ ወንጀል ተፈጽሞብህ ከሆነ፣ ወንጀሉን ለፖሊስ ወይም ለሌሎች ባለሥልጣናት ሪፖርት ለማድረግ ልትመርጥ ትችላለህ።
የበቀል ሰንሰለት ራስን መልሶ ይጎዳል
ሆኖም ጉዳዩን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት እንደማይቻል ቢሰማህስ? ወይም ደግሞ ጉዳዩን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የምትችለውን ሁሉ አድርገህም ምንም መፍትሔ ባታገኝስ? የበቀል እርምጃ አትውሰድ። በቀል ችግሩን ማባባሱ አይቀርም። ከዚህ ይልቅ የጥላቻን ሰንሰለት በጥስ። አምላክ ችግሮችን የሚፈታበት መንገድ የተሻለ እንደሆነ መተማመን ትችላለህ። “በእሱ ታመን፤ እሱም ለአንተ ሲል እርምጃ ይወስዳል።”—መዝሙር 37:3-5