በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወደፊት ሕይወትህ የተመካው በምን ላይ ነው?

የወደፊት ሕይወትህ የተመካው በምን ላይ ነው?

ብዙ ሰዎች አንዳንድ በዓይን የማይታዩ ኃይሎች የወደፊት ሕይወታቸውን እንደሚቆጣጠሩት ይሰማቸዋል። በዚህም የተነሳ፣ ጥሩ ዕድል እንዲገጥመን ይረዱናል ብለው የሚያስቧቸውን ነገሮች ያደርጋሉ።

ብዙዎች በምን ያምናሉ?

ኮከብ ቆጠራ፦ አንዳንድ ሰዎች በተወለዱበት ወቅት ከዋክብት የነበራቸው አቀማመጥ የወደፊት ሕይወታቸውን እንደሚወስነው ያምናሉ። በመሆኑም በሆሮስኮፕ ወይም በኮከብ ቆጠራ አማካኝነት ወደፊት ስለሚያጋጥማቸው ነገር ለማወቅ ይሞክራሉ፤ ከዚያም በዚያ ላይ ተመሥርተው ውሳኔ ያደርጋሉ።

ጠንቋይ መጠየቅ፦ ሌሎች ደግሞ ጠንቋዮችን መጠየቅ አንድ ነገር የደረሰባቸው ለምን እንደሆነ ለማወቅና ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመወሰን እንደሚረዳቸው ይሰማቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው ጉዳት ሊያስከትልባቸው የሚችልን ነገር ለመከላከል፣ ለችግሮቻቸው መፍትሔ ለማግኘትና ስኬታማ ለመሆን እንደሚረዳቸው ያምናሉ።

የቀድሞ አባቶች አምልኮ፦ በሕይወታቸው ጥበቃና በረከት ማግኘት ከፈለጉ የሞቱ ዘመዶቻቸውን ወይም የተለያዩ አማልክትን መለማመን እንዳለባቸው የሚያምኑ ሰዎችም አሉ። በቬትናም የሚኖረው ቫን * እንዲህ ብሏል፦ “የሞቱ ዘመዶቼን መንፈስ መለማመኔ እኔም ሆንኩ ልጆቼ አሁን ጥሩ ሕይወት እንድንመራ እንደሚረዳንና የወደፊት ሕይወታችንን አስተማማኝ እንደሚያደርግልን አምን ነበር።”

ሪኢንካርኔሽን፦ ብዙ ሰዎች አንድ ሰው ሲሞት ዳግም እንደሚወለድና ይህ የማያቋርጥ ሂደት እንደሆነ ያምናሉ። በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥማቸው ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር በቀድሞ ሕይወታቸው የፈጸሙት ድርጊት ውጤት እንደሆነ ያስባሉ።

ይሁንና ብዙዎች እንዲህ ያሉት ነገሮች አጉል እምነት እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ያም ሆኖ እንደ መዳፍ ማንበብ፣ አውደ ነገሥት መግለጥ፣ ኮከብ ቆጠራና ሞራ መግለጥ በመሳሰሉ ድርጊቶች ይካፈላሉ። እነዚህ ነገሮች ስለ ወደፊቱ ሕይወታቸው ለማወቅ ሊረዷቸው እንደሚችሉ ይሰማቸዋል።

ውጤቱ ምን ያሳያል?

እንዲህ ባሉት ነገሮች የሚያምኑና እነዚህን ልማዶች የሚከተሉ ሰዎች ጥሩ ሕይወት መምራትና የወደፊት ሕይወታቸውን አስተማማኝ ማድረግ ችለዋል?

በቬትናም የሚኖረው ሃዎ ያጋጠመውን ነገር እንመልከት። ኮከብ ቆጠራንና ፈንግ ሽዌን * በመጠቀም እንዲሁም ለቀድሞ አባቶች አምልኮ በማቅረብ በሕይወቱ ስኬት ለማግኘት ሞክሮ ነበር። ታዲያ ስኬታማ መሆን ችሏል? ሃዎ እንዲህ ብሏል፦ “ንግዴ ከሰረ፤ ዕዳ ውስጥ ገባሁ፤ ቤተሰቤ ተበጠበጠ፤ እንዲሁም ከፍተኛ የስሜት ቀውስ ውስጥ ገባሁ።”

ቺዮሚንግ የተባለ በታይዋን የሚኖር ሰውም በኮከብ ቆጠራ፣ በሪኢንካርኔሽን፣ በዕድል፣ በፈንግ ሽዌ እና ለቀድሞ አባቶች አምልኮ በማቅረብ ያምን ነበር። እነዚህን ነገሮች በጥንቃቄ ከመረመረ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ያሉት ትምህርቶችና ልማዶች እርስ በርስ የሚጋጩና ግራ የሚያጋቡ እንደሆኑ ተገነዘብኩ። የኮከብ ቆጠራ ትንበያዎች በአብዛኛው ትክክል እንዳልሆኑ አስተዋልኩ። ሪኢንካርኔሽንም ቢሆን ትክክል እንዳልሆነ ተረዳሁ፤ ምክንያቱም ስለ ቀድሞ ሕይወታችን ምንም ነገር የማናስታውስ ከሆነ መለወጥና በቀጣዩ ሕይወታችን የተሻለ ነገር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?”

“እንዲህ ያሉት ትምህርቶችና ልማዶች እርስ በርስ የሚጋጩና ግራ የሚያጋቡ እንደሆኑ ተገነዘብኩ።”—ቺዮሚንግ፣ ታይዋን

ሃዎ፣ ቺዮሚንግ እና ሌሎች በርካታ ሰዎች እንደተገነዘቡት የወደፊት ሕይወታችን በዕድል፣ በከዋክብት፣ በሞቱ ዘመዶቻችን ወይም በሪኢንካርኔሽን ላይ የተመካ አይደለም። ይህ ሲባል ታዲያ ከወደፊቱ ሕይወታችን ጋር በተያያዘ ምንም ማድረግ የምንችለው ነገር የለም ማለት ነው?

ብዙ ሰዎች የወደፊት ሕይወታቸውን አስተማማኝ ማድረግ የሚችሉት ከፍተኛ ትምህርት በመከታተልና ሀብት በማካበት እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንዲህ ያለ ምርጫ ያደረጉ ሰዎች ምን ውጤት አግኝተዋል?

^ አን.6 በዚህ ርዕስና በቀጣዮቹ ርዕሶች ላይ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.11 “ፈንግ ሽዌ” በቻይናና በሌሎች የእስያ አገሮች በስፋት የሚታወቅ ልማድ ነው። በፈንግ ሽዌ የሚያምኑ ሰዎች አካባቢያቸውን በተፈጥሮ ውስጥ ካሉ የማይታዩ ኃይሎች ጋር ማቆራኘታቸው ደስታና ስኬት እንደሚያስገኝላቸው ይሰማቸዋል።

^ አን.16 ይህ ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ገላትያ 6:7 ላይ ይገኛል። የሚከተለው ታዋቂ የምሥራቃውያን አባባልም ከዚህ ሐሳብ ጋር ይስማማል፦ ሐብሐብ ከተከልክ ሐብሐብ ታገኛለህ። ባቄላ ከዘራህ ባቄላ ታገኛለህ።