4 | መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ምክር ይሰጣል
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ . . . ይጠቅማሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16
ምን ማለት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና መጽሐፍ ባይሆንም ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ጠቃሚ ምክር ይሰጠናል። ምክሩ የአእምሮ ጤንነት ችግር ያለበትን ሰው ሊረዳው ይችላል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።
የሚረዳን እንዴት ነው?
“ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም።”—ማቴዎስ 9:12
መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና እርዳታ ማግኘት የሚያስፈልግበት ጊዜ እንዳለ በግልጽ ይናገራል። ብዙዎች ስለ አእምሮ ሕመማቸው ከአስተማማኝ ምንጮች መረጃ ማግኘታቸው እንዲሁም የባለሙያዎችን እርዳታ መጠየቃቸው እፎይታ ለማግኘት ረድቷቸዋል።
“የአካል ብቃት እንቅስቃሴ . . . ይጠቅማል።”—1 ጢሞቴዎስ 4:8
ጊዜ መድበህ ለአካላዊ ጤንነትህ የሚጠቅሙ ልማዶችን ማዳበርህ የአእምሮ ጤንነትህን ለማሻሻልም ሊረዳህ ይችላል። ከእነዚህ ልማዶች መካከል አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጤናማ የአመጋገብ ልማድ ማዳበር እንዲሁም በቂ እንቅልፍ ማግኘት ይገኙበታል።
“ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኃኒት ነው፤ የተደቆሰ መንፈስ ግን ኃይል ያሟጥጣል።”—ምሳሌ 17:22
የሚያበረታቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማንበብህ እንዲሁም ምክንያታዊ የሆኑና ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦችን ማውጣትህ ደስተኛ ለመሆን ይረዳሃል። አዎንታዊ አመለካከት መያዝህና የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ መጠባበቅህ ከአእምሮ
ሕመምህ ጋር በምትታገልበት ወቅት ስሜታዊ ሚዛንህን ለመጠበቅ ይረዳሃል።“ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች።”—ምሳሌ 11:2
የምትፈልገውን ነገር ሁሉ በራስህ ማድረግ አትችል ይሆናል። ስለዚህ የሌሎችን እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኛ ሁን። ጓደኞችህና ቤተሰቦችህ ሊረዱህ እንደሚፈልጉ ጥያቄ የለውም፤ ሆኖም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ላያውቁ ይችላሉ። ስለዚህ ምን ዓይነት እርዳታ እንደምትፈልግ በግልጽ ንገራቸው። ከሌሎች በምትጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ሁን፤ እንዲሁም ለሚሰጡህ እርዳታ ምንጊዜም አመስጋኝ ሁን።
የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር የረዳቸው እንዴት ነው?
“የሆነ ችግር እንዳለብኝ ስለተሰማኝ ሐኪም አማከርኩ። ሐኪሟ የችግሬን ምንነት ማወቅ ቻለች። ይህም ስላለብኝ ችግር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እንዲሁም ጤንነቴን ለማሻሻል ሊረዱኝ ስለሚችሉ የሕክምና አማራጮች ለማወቅ አስችሎኛል።”—የስሜት መዋዠቅ ችግር ያለባት ኒኮል a
“ከባለቤቴ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሬ ማንበቤ እያንዳንዱን ቀን አዎንታዊ በሆኑና በሚያንጹ ሐሳቦች ለመጀመር እንደሚረዳኝ ተገንዝቤያለሁ። በተለይ በድባቴ በምዋጥባቸው ቀናት ልቤን የሚነካ ጥቅስ ማግኘቴ አይቀርም።”—ከድባቴ ጋር የሚታገለው ፒተር
“ሁኔታው በጣም ስለሚያሳፍረኝ ስላለብኝ ትግል ለሌሎች ሰዎች መናገር ይከብደኝ ነበር። ሆኖም አንዲት የቅርብ ጓደኛዬ በደግነት አዳመጠችኝ፤ እንዲሁም ስሜቴን ተረዳችልኝ። ቀለል እንዲለኝና ብቻዬን እንዳልሆንኩ እንዲሰማኝ ረድታኛለች።”—ከአመጋገብ ችግር ጋር የምትታገለው ጂዩ
“መጽሐፍ ቅዱስ ከሥራና ከእረፍት ጋር በተያያዘ ሚዛናዊና ምክንያታዊ እንድሆን ረድቶኛል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር የሚያሠቃዩኝን የስሜት ችግሮች እንድቋቋም ረድቶኛል።”—ከአእምሮ ሕመም ጋር የሚታገለው ቲሞቲ
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።