ድምፅ አልባው ምሥክር
ጣሊያን ውስጥ በሮም ከተማ እምብርት ላይ ከመላው ዓለም የሚመጡ ጎብኚዎችን ትኩረት የሚስብ አንድ የድል ሐውልት አለ። የቲቶ ቅስት በመባል የሚታወቀው ይህ ሐውልት የቆመው በሮማውያን ዘንድ ተወዳጅ ከነበሩት ንጉሠ ነገሥታት አንዱ ለሆነው ለቲቶ ክብር ነው።
ሐውልቱ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅን ታሪካዊ ክንውን የሚያሳዩ ሁለት ትላልቅ ምስሎች አሉት። ይሁንና በሐውልቱና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል ያለው አስገራሚ ተያያዥነት ያን ያህል አይታወቅም፤ የቲቶ ቅስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ትክክል እንደሆነ የሚያረጋግጥ ድምፅ አልባ ምሥክር ነው።
ጥፋት የተፈረደባት ከተማ
በመጀመሪያው መቶ ዘመን መባቻ ላይ የሮም ግዛት ብሪታንያን ጨምሮ ከጋውል (ከአሁኗ ፈረንሳይ) እስከ ግብፅ ድረስ ተስፋፍቶ ነበር፤ በግዛቱ ውስጥ ከዚያ በፊት ታይቶ የማያውቅ ሰላምና ብልጽግና ሰፍኖ ነበር። ይሁንና አለመረጋጋት የሰፈነበት የይሁዳ አውራጃ የሮም መንግሥትን እረፍት ነስቶት ነበር።
ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ኤንሸንት ሮም እንዲህ ይላል፦ “በሮም ቁጥጥር ሥር ካሉት ክልሎች ውስጥ የይሁዳን ያህል ሁለቱም ወገኖች በከፍተኛ ጥላቻ የሚተያዩበት ክልል የለም ማለት ይቻላል። አይሁዳውያን ለእነሱ ወግና ባሕል ምንም ደንታ ላልነበራቸው ለሮማውያን ጌቶቻቸው ጥላቻ ያዳበሩ ሲሆን ሮማውያኑም የአይሁዳውያንን ግትርነት ለመታገሥ ፈቃደኛ አልነበሩም።” አብዛኞቹ አይሁዳውያን አንድ የፖለቲካ መሪ ማለትም መሲሕ ተነስቶ የሚጠሏቸውን ሮማውያንን በማባረር ለእስራኤል ወርቃማ ዘመን ያመጣል የሚል ተስፋ ነበራቸው። ይሁን እንጂ በ33 ዓ.ም. ኢየሱስ ክርስቶስ ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ ተናገረ።
ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ጠላቶችሽ በሾለ እንጨት በዙሪያሽ ቅጥር ቀጥረው አንቺን የሚከቡበትና ከሁሉም አቅጣጫ የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣል። አንቺንና በውስጥሽ የሚኖሩትን ልጆችሽን ፈጥፍጠው ከአፈር ይደባልቃሉ፤ በአንቺ ውስጥም ሳያፈርሱ እንደተነባበረ የሚተዉት ድንጋይ አይኖርም።”—ሉቃስ 19:43, 44
ኢየሱስ የተናገረው ነገር ለደቀ መዛሙርቱ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ግልጽ ነው። ኢየሱስ ይህን ትንቢት ከተናገረ ከሁለት ቀናት በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በኢየሩሳሌም ያለውን ቤተ መቅደስ እየተመለከተ “መምህር፣ እንዴት ያሉ ግሩም ድንጋዮችና ሕንጻዎች እንደሆኑ ተመልከት!” በማለት በአድናቆት ተናገረ። ቤተ መቅደሱ የተሠራባቸው አንዳንዶቹ ድንጋዮች ርዝመታቸው ከ11 ሜትር በላይ፣ ወርዳቸው 5 ሜትር ከፍታቸው ደግሞ 3 ሜትር እንደነበር ይነገራል! ሆኖም ኢየሱስ “ይህ የምታዩት ነገር ሁሉ የሚፈርስበት ጊዜ ይመጣል፤ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ አይኖርም” አላቸው።—ማርቆስ 13:1፤ ሉቃስ 21:6
በተጨማሪም ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት ተከባ ስታዩ መጥፊያዋ እንደቀረበ እወቁ። በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በከተማዋ ውስጥ ያሉም ከዚያ ይውጡ፤ በገጠር ያሉም ወደ እሷ አይግቡ።” (ሉቃስ 21:20, 21) ታዲያ ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ተፈጽሟል?
የአንዲት ከተማ መጥፋት
ኢየሱስ ከላይ ያለውን ትንቢት ከተናገረ ከሠላሳ ሦስት ዓመታት በኋላም እንኳ ይሁዳ ከሮማውያን የባርነት ቀንበር አልተላቀቀችም ነበር። ይሁንና በ66 ዓ.ም. በይሁዳ የነበረው ሮማዊው አገረ ገዢ ጀሲየስ ፍሎረስ፣ ቅዱስ ከሆነው የቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት ገንዘብ ወሰደ፤ ይህም አይሁዳውያኑን እጅግ አስቆጣቸው። በመሆኑም አይሁዳውያን ተዋጊዎች ወዲያውኑ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ከዚያም በአካባቢው የነበረውን የሮም ሠራዊት በመፍጀት ነፃ መውጣታቸውን አወጁ።
ከሦስት ወራት ገደማ በኋላ ሴስቲየስ ጋለስ 30,000 ሮማውያን ወታደሮችን እየመራ ማቴዎስ 24:15, 16
የአይሁዳውያንን ዓመፅ ለማስቆም ወደ ኢየሩሳሌም ዘመተ። ሮማውያን በፍጥነት ወደ ከተማዋ በመግባት በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ያለውን ውጨኛ ግንብ ለመናድ ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ከዚያም ባልታወቀ ምክንያት ወደኋላ አፈገፈጉ። አይሁዳውያን ዓማፂዎች በዚህ በመደሰት የሮማውያኑን ሠራዊት ማሳደድ ጀመሩ። በዚህ መንገድ ሁለቱም ተዋጊ ኃይሎች ከከተማዋ ወጡ፤ በዚህ ጊዜ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ በመታዘዝ ከኢየሩሳሌም ወጥተው ከዮርዳኖስ ማዶ ወደሚገኙ ተራሮች ሸሹ።—በቀጣዩ ዓመት ሮም በይሁዳ ላይ የጀመረችውን ዘመቻ አጠናክራ ለመቀጠል በጄኔራል ቨስፔዥያንና በልጁ በቲቶ የሚመራ ሠራዊት ላከች። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ በ68 ዓ.ም. ንጉሠ ነገሥት ኔሮ ሞተ፤ በመሆኑም ቨስፔዥያን ልጁንና 60,000 ወታደሮቹን በይሁዳ በመተው ዙፋኑን ለመረከብ ወደ ሮም ተመለሰ።
በ70 ዓ.ም. ሰኔ ወር ላይ ቲቶ ወታደሮቹ የይሁዳን ገጠራማ አካባቢዎች ደን መንጥረው የሾሉ እንጨቶች በማዘጋጀት በኢየሩሳሌም ግንብ ዙሪያ 7 ኪሎ ሜትር የሚያህል ርዝመት ያለው ቅጥር እንዲሠሩ ትእዛዝ አስተላለፈ። መስከረም ላይ ሮማውያኑ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን ከመዘበሩና ካቃጠሉ በኋላ ልክ ኢየሱስ በትንቢት እንደተናገረው የተነባበሩትን ድንጋዮች አፈራረሷቸው። (ሉቃስ 19:43, 44) አንድ ምንጭ እንደገመተው ከሆነ በዚያ ወቅት “በኢየሩሳሌምና በቀሪው የአገሪቱ ክፍል ወደ 500,000 የሚጠጋ ሕዝብ አልቋል።”
ታላቅ ንጉሣዊ ድል
ቲቶ በ71 ዓ.ም. ወደ ጣሊያን ሲመለስ የሮም ዜጎች ደማቅ አቀባበል አደረጉለት። መላው የከተማዋ ነዋሪ ከዚያ በፊት በዋና ከተማዋ ከተደረጉት ሁሉ የሚበልጠውን ታላቅ የድል ሰልፍ ለማጀብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ነበር።
በምርኮ የተገኘው ከፍተኛ ሀብት በሮም ጎዳናዎች ላይ በሰልፍ ሲያልፍ ሕዝቡ በአድናቆት ይመለከት ነበር። በተጨማሪም የከተማዋ ነዋሪዎች በምርኮ የተገኙትን ጀልባዎች፣ በጦርነቱ ወቅት የነበረው ሁኔታ የተሳለባቸው ትላልቅ የትርኢት ማሳያ ጋሪዎችንና ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የመጡ ዕቃዎችን ማየታቸው አስደስቷቸዋል።
ቲቶ በ79 ዓ.ም. በአባቱ በቨስፔዥያን ምትክ የሮም ንጉሠ ነገሥት ሆነ። ይሁንና ከሁለት ዓመት በኋላ በድንገት ሞተ። ወንድሙ ደሚሸን ዙፋኑን የተረከበ ሲሆን ወዲያውኑ ለቲቶ ክብር የድል ሐውልት አቆመለት።
የቲቶ ቅስት በዛሬው ጊዜ
በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሮምን ይጎበኛሉ፤ እነዚህ ሰዎች የቲቶን ቅስት ሲያዩ በጣም ይደነቃሉ። አንዳንዶች ይህን ሐውልት የሚመለከቱት እንደ ድንቅ የሥነ ጥበብ ሥራ አድርገው ነው፤ ሌሎች ደግሞ ታላቁን የሮማውያን ግዛት ኃያልነት ለመዘከር እንደቆመ ሐውልት አድርገው ይመለከቱታል። በሌላ በኩል ደግሞ በኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሷ ላይ የደረሰውን ጥፋት ለማስታወስ እንደሚያገለግል ሐውልት አድርገው የሚመለከቱትም አሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች በጥንቃቄ የሚመረምሩ አንባቢዎች ግን የቲቶን ቅስት ከዚህ የበለጠ ትርጉም እንዳለው አድርገው ይመለከቱታል። ይህ ሐውልት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እምነት የሚጣልባቸውና ትክክለኛ እንደሆኑ እንድንገነዘብ የሚያደርግ እንዲሁም ትንቢቶቹ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፉ የሚያረጋግጥ ድምፅ አልባ ምሥክር ነው።—2 ጴጥሮስ 1:19-21