በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወደፊቱ ሕይወትህና የምታደርገው ምርጫ!

የወደፊቱ ሕይወትህና የምታደርገው ምርጫ!

የወደፊቱ ሕይወትህ በምታደርገው ምርጫ ላይ የተመካ ነው? አንዳንድ ሰዎች ዕድላቸው ወይም ዕጣ ፈንታቸው አስቀድሞ እንደተወሰነ ያምናሉ። በመሆኑም የወደፊት ሕይወታቸውና የሚያደርጉት ምርጫ ግንኙነት እንዳለው አይሰማቸውም። ያወጧቸው ግቦች ላይ መድረስ ሲያቅታቸው “አስቀድሞ የተወሰነ ነገር ነው” ወይም “ድሮም ለእኔ አላለውም” ብለው ይተዉታል።

ሌሎች ደግሞ ጭቆናና የፍትሕ መጓደል በሰፈነበት በዚህ ዓለም ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ማሸነፍ ሲያቅታቸው ግራ ይጋባሉ። ሕይወታቸውን ለማሻሻል ቢጥሩም እንደ ጦርነት፣ ወንጀል፣ የተፈጥሮ አደጋና ሕመም የመሳሰሉ ነገሮች ያሰቡትን እንዳያሳኩ እንቅፋት ይሆኑባቸዋል። በዚህ ጊዜ ‘ታዲያ ምን አደከመኝ?’ ብለው ያስባሉ።

በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ የተለያዩ ሁኔታዎች ያሰብከውን ከመፈጸም ሊያግዱህ እንደሚችሉ አይካድም። (መክብብ 9:11) ከወደፊት ሕይወትህ ጋር በተያያዘ ግን የራስህን ምርጫ ማድረግ ትችላለህ። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱ ሕይወትህ በምታደርገው ምርጫ ላይ የተመካ እንደሆነ ይገልጻል። እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንመልከት።

የጥንቱ የእስራኤል ብሔር መሪ የነበረው ሙሴ ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገባ በተቃረበበት ወቅት እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር፦ “ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና እርግማንን በፊታችሁ [አስቀምጫለሁ]፤ . . . እንግዲህ አንተም ሆንክ ዘሮችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤ ይህን የምታደርገው አምላክህን ይሖዋን በመውደድ፣ ቃሉን በመስማትና ከእሱ ጋር በመጣበቅ ነው።”ዘዳግም 30:15, 19, 20

‘ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና እርግማንን በፊትህ አስቀምጫለሁ፤ አንተም ሕይወትን ምረጥ።’—ዘዳግም 30:19

አምላክ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ በማውጣት በተስፋይቱ ምድር ላይ ነፃ ሕዝብ ሆነው በደስታ እንዲኖሩ አጋጣሚ ሰጥቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ ከእነሱም የሚጠበቅ ነገር አለ። እነዚያን በረከቶች ለማግኘት ‘ሕይወትን መምረጥ’ ነበረባቸው። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? ‘አምላክን በመውደድ፣ ቃሉን በመስማትና ከእሱ ጋር በመጣበቅ’ ነው።

በዛሬው ጊዜም ተመሳሳይ ምርጫ ማድረግ ያለብህ ሲሆን የምታደርገው ምርጫ በወደፊት ሕይወትህ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። አምላክን የምትወድ፣ ቃሉን የምትሰማና ከእሱ ጋር የምትጣበቅ ከሆነ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር የሚያስችልህን ሕይወት መረጥክ ማለት ነው። ሆኖም እነዚህን ሦስት ነገሮች ማድረግ ሲባል ምን ማለት ነው?

አምላክን መውደድ

ፍቅር የአምላክ ዋነኛ ባሕርይ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት “አምላክ ፍቅር ነው” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 4:8) ኢየሱስ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው እንደሆነ ሲጠየቅ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ” በማለት የተናገረው በዚህ ምክንያት ነው። (ማቴዎስ 22:37) ከይሖዋ ጋር ዝምድና መመሥረት ያለብን ለእሱ ባለን ፍቅር ተነሳስተን እንጂ ስለምንፈራው ወይም እሱን በጭፍን መታዘዝ ስለምንፈልግ መሆን የለበትም። ይሁንና አምላክን እንድንወደው የሚያደርገን ምንድን ነው?

ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር፣ አፍቃሪ ወላጆች ለልጆቻቸው ካላቸው ፍቅር ጋር ይመሳሰላል። አፍቃሪ ወላጆች ልጆቻቸው ፍጹም ባይሆኑም እንኳ ደስተኛ እንዲሆኑና እንዲሳካላቸው ስለሚፈልጉ ያስተምሯቸዋል፣ ያበረታቷቸዋል፣ ይደግፏቸዋል እንዲሁም እርማት ይሰጧቸዋል። ታዲያ እነዚህ ወላጆች በምላሹ ከልጆቻቸው ምን ይጠብቃሉ? ልጆቻቸው እንዲወዷቸው እንዲሁም እነሱን ለመጥቀም ብለው የሚሰጧቸውን ትምህርት በቁም ነገር እንዲመለከቱት ይፈልጋሉ። ታዲያ ፍጹም የሆነው የሰማዩ አባታችን ብዙ ነገር ስላደረገልን በፍቅር ተነሳስተን እንድንታዘዘው መጠበቁ ምክንያታዊ አይደለም?

ቃሉን መስማት

መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “መስማት” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ “መታዘዝ” የሚለውን ሐሳብ ያስተላልፋል። እኛስ አንድን ልጅ “ወላጆችህን ስማ” ስንለው “ወላጆችህን ታዘዝ” ማለታችን አይደለም? በመሆኑም የአምላክን ቃል መስማት ሲባል የእሱን ቃል ማወቅና መታዘዝ ማለት ነው። የአምላክን ድምፅ ቃል በቃል መስማት ስለማንችል እሱን የምንሰማው ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና ከቃሉ የተማርነውን በሥራ ላይ በማዋል ነው።—1 ዮሐንስ 5:3

በአንድ ወቅት ኢየሱስ የአምላክን ቃል መስማት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማሳየት “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 4:4) ሥጋዊ ምግብ መመገብ የግድ አስፈላጊ ነው፤ የአምላክን እውቀት መቅሰም ደግሞ ከዚያም የበለጠ አስፈላጊ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “ገንዘብ ጥበቃ እንደሚያስገኝ ሁሉ ጥበብም ጥበቃ ታስገኛለችና፤ የእውቀት ብልጫ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት ጠብቃ ማቆየት መቻሏ ነው” በማለት ተናግሯል። (መክብብ 7:12) ከአምላክ የምናገኘው እውቀትና ጥበብ ዛሬ ጥበቃ የሚያስገኝልን ሲሆን ወደፊት የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ የሚያስችል ትክክለኛ ምርጫ እንድናደርግም ይረዳናል።

ከእሱ ጋር መጣበቅ

ኢየሱስ “ወደ ሕይወት የሚወስደው በር . . . ጠባብ፣ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” በማለት የተናገረውን ምሳሌ ባለፈው ርዕስ ላይ ተመልክተን ነበር። (ማቴዎስ 7:13, 14) እንዲህ ባለው መንገድ ላይ ስንጓዝ መንገዱን በደንብ የሚያውቅን ሰው ተከትለን መሄዳችን ያሰብንበት ቦታ ለመድረስ ማለትም የዘላለም ሕይወት ለማግኘት እንደሚረዳን የታወቀ ነው። ስለዚህ ከአምላክ ሳንርቅ መኖራችን አስፈላጊ ነው። (መዝሙር 16:8) ይሁንና ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ማድረግ የምንፈልጋቸውና የግድ ልናደርጋቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮች አሉ። እነዚህ ነገሮች ጊዜያችንን ሊሻሙብን ወይም ትኩረታችንን ሊሰርቁ ስለሚችሉ አምላክ ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግ ለማሰብ እንኳ ጊዜ እናጣለን። መጽሐፍ ቅዱስ “የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ስለሆኑ ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት” በማለት የሚያሳስበን ለዚህ ነው። (ኤፌሶን 5:15, 16) ከአምላክ ጋር ላለን ዝምድና በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ በመስጠት ከእሱ ጋር ተቀራርበን መኖር እንችላለን።—ማቴዎስ 6:33

ምርጫው የአንተ ነው

ያለፈውን ጊዜ ለመለወጥ ማድረግ የምትችለው ነገር ባይኖርም የአንተንም ሆነ የቤተሰብህን የወደፊት ሕይወት አስተማማኝ ለማድረግ ልትወስድ የምትችላቸው እርምጃዎች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ ያለው አባታችን ይሖዋ በጣም እንደሚወደን እንዲሁም ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግ ይናገራል። እስቲ ነቢዩ ሚክያስ ምን እንዳለ እንመልከት፦

“ሰው ሆይ፣ መልካም የሆነውን ነግሮሃል። ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን እንድታደርግ፣ ታማኝነትን እንድትወድና ልክህን አውቀህ ከአምላክህ ጋር እንድትሄድ ብቻ ነው!”ሚክያስ 6:8

አንተስ ይሖዋ ከእሱ ጋር እንድትሄድ ያቀረበልህን ግብዣ ትቀበላለህ? ይህን ግብዣ ለሚቀበሉ ሰዎች ያዘጋጃቸውን ዘላለማዊ በረከቶች ታገኝ ይሆን? ምርጫው የአንተ ነው!