የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውናል?
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “መንግሥትህ ይምጣ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። ምክንያቱም በምድር ላይ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ የአምላክ ፈቃድ እንዳልሆነና ይህን ሁኔታ ሊያስተካክል የሚችለው ብቸኛው አገዛዝ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ያውቅ ነበር። የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውን ይሆን?
የአምላክ መንግሥት እስካሁን ምን ነገሮችን አከናውኗል?
ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ፣ ኢየሱስ የሰጠውን ምልክት መርምረናል። ይህ ምልክት የአምላክ መንግሥት በሰማይ እንደተቋቋመና ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ንጉሥ ሆኖ እንደተሾመ የሚያረጋግጥ ግልጽ ማስረጃ ነው።
ኢየሱስ ንጉሣዊ ሥልጣኑን እንደያዘ ወዲያውኑ ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ እንደሚያባርራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በአሁኑ ጊዜ የሰይጣንና የአጋንንቱ እንቅስቃሴ በምድር ላይ ብቻ የተገደበ እንዲሆን ተደርጓል፤ ከ1914 ወዲህ የሰው ዘር ያለበት ሁኔታ እጅግ አስከፊ የሆነበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።—ራእይ 12:7, 9
የዓለም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ቢሄድም የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ በሁሉም የምድር ክፍሎች የሚኖሩ ሰዎችን ለመርዳት የተለያዩ ነገሮችን አድርጓል። ኢየሱስ በትንቢት የተናገረለት ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማሩ ሥራ፣ ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተምረው በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ተግባራዊ እንዲያደርጉ እየረዳ ነው። (ኢሳይያስ 2:2-4) በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በመማራቸው ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት መምራት እንዲሁም ለሰብዓዊ ሥራቸውም ሆነ ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ችለዋል። እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ሕይወት መምራት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ተምረዋል፤ እንዲሁም በአምላክ መንግሥት ሥር ለሚኖረው ሕይወት ከወዲሁ መዘጋጀት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ተገንዝበዋል።
የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ምን ነገሮችን ያከናውናል?
ኢየሱስ በሰማይ መግዛት የጀመረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ምድርን እየገዙ ያሉት ሰብዓዊ መንግሥታት ናቸው። ሆኖም አምላክ ኢየሱስን “በጠላቶችህ መካከል በድል አድራጊነት ግዛ” ብሎታል። (መዝሙር 110:2) ስለዚህ ኢየሱስ በቅርቡ ተቃዋሚዎቹን ሁሉ በማጥፋት በፈቃደኝነት አምላክን ለሚታዘዙ ሰዎች እፎይታ ያስገኛል።
የአምላክ መንግሥት በቅርቡ የሚከተሉትን እርምጃዎች ይወስዳል፦
-
የሐሰት ሃይማኖትን ያጠፋል። አምላክን በተመለከተ ውሸት የሚያስተምሩና ሰዎች ሕይወት ከባድ እንዲሆንባቸው የሚያደርጉ ሃይማኖቶች ይጠፋሉ። የሐሰት ሃይማኖት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአንዲት አመንዝራ ተመስሏል። በሐሰት ሃይማኖት ላይ የሚመጣው ጥፋት ለብዙዎች አስደንጋጭ ይሆንባቸዋል።—ራእይ 17:15, 16
-
የሰዎችን አገዛዝ ያስወግዳል። የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ አገዛዝን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል።—ራእይ 19:15, 17, 18
-
ክፉዎችን ያጠፋል። መጥፎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ቆርጠው የተነሱና አምላክን ለመታዘዝ አሻፈረኝ ያሉ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉዎች . . . ከምድር ገጽ ይጠፋሉ” ይላል።—ምሳሌ 2:22
-
ሰይጣንንና አጋንንቱን ያጠፋል። ሰይጣንና አጋንንቱ ‘ሕዝቦችን ማሳሳት’ እንዳይችሉ ይደረጋሉ።—ራእይ 20:3, 10
እነዚህ ሁሉ ክንውኖች የአምላክን መንግሥት ለሚደግፉ ሰዎች ምን ትርጉም ይኖራቸዋል?
የአምላክ መንግሥት ለሰው ዘር የሚያመጣው በረከት
በሰማይ ንጉሥ ሆኖ የሚያስተዳድረው ኢየሱስ ማንኛውም ሰብዓዊ ገዢ ሊያከናውን ከሚችለው ነገር ሁሉ እጅግ የላቀ ነገር ያከናውናል። ከሰዎች መካከል የተመረጡ 144,000 ገዢዎች አብረውት ይገዛሉ። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 3) ኢየሱስ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ያደርጋል። የአምላክ መንግሥት፣ ለምድር ነዋሪዎችስ ምን ያደርግላቸው ይሆን?
-
ሕመምንና ሞትን ያስወግዳል። “በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም” እንዲሁም “ሞት አይኖርም።”—ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 21:4
-
እውነተኛ ሰላምና ደህንነት ያሰፍናል። “የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል”፤ “እያንዳንዱም ከወይኑና ከበለስ ዛፉ ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም።”—ኢሳይያስ 54:13፤ ሚክያስ 4:4
-
ሁሉም ሰው አስደሳች ሥራ እንዲኖረው ያደርጋል። “የመረጥኳቸው አገልጋዮቼም በእጃቸው ሥራ የተሟላ እርካታ ያገኛሉ። በከንቱ አይለፉም።”—ኢሳይያስ 65:22, 23
-
በፕላኔቷ ምድራችን ላይ የደረሰውን ጉዳት ያስተካክላል። “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ሐሴት ያደርጋል፤ በረሃማው ቦታም ደስ ይለዋል፤ እንደ ሳሮን አበባም ያብባል።”—ኢሳይያስ 35:1
-
ሰዎች ለዘላለም ለመኖር ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያስተምራል። “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ነው።”—ዮሐንስ 17:3
አምላክ እነዚህን በረከቶች እንድታገኝ ይፈልጋል። (ኢሳይያስ 48:18) ቀጣዩ ርዕስ ይህን አስደሳች ተስፋ ለማግኘት ከወዲሁ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ያብራራል።