መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
ለራሴም ሆነ ለሴቶች አክብሮት ማሳየትን ተማርኩ
-
የትውልድ ዘመን፦ 1960
-
የትውልድ አገር፦ ፈረንሳይ
-
የኋላ ታሪክ፦ ዓመፀኛ፣ የዕፅ ሱሰኛና ሴቶችን ይንቅ የነበረ
የቀድሞ ሕይወቴ፦
የተወለድኩት በሰሜን ምሥራቅ ፈረንሳይ በምትገኝ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በሚኖሩባት እንዲሁም በብጥብጥ ትታወቅ በነበረች ሚሉዝ የተባለች ከተማ ነው። ልጅ ሳለሁ በአካባቢያችን በቤተሰቦች መካከል ይፈጠር የነበረው ከባድ ግጭት ከአእምሮዬ አይጠፋም። በቤተሰባችን ውስጥ ሴቶች በንቀት የሚታዩ ሲሆን ወንዶቹ ደግሞ ምንም ነገር አያማክሯቸውም ቢባል ይቀልላል። ሴት ልጅ ከጓዳ መውጣት እንደሌለባት፣ ሥራዋም ወንዶችንና ልጆችን መንከባከብ እንደሆነ ይነገረኝ ነበር።
የልጅነት ሕይወቴ በጣም አስቸጋሪ ነበር። የአሥር ዓመት ልጅ ሳለሁ፣ የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ የነበረው አባቴ ሞተ። ከአምስት ዓመት በኋላ ከታላቅ ወንድሞቼ አንዱ ሕይወቱን አጠፋ። በዚያው ዓመት በቤተሰባችን መካከል በነበረ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ጠብ የተነሳ ሰው ሲገደል በገዛ ዓይኔ አየሁ፤ ይህም በጣም አስደነገጠኝ። የቤተሰቤ አባላት ጩቤና ሽጉጥ እንዴት መጠቀም እንደምችል ያሠለጠኑኝ ከመሆኑም ሌላ አስገዳጅ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ሁሉ እርምጃ እንድወስድ ነገሩኝ። በዚያ የወጣትነት ዕድሜዬ ግራ ተጋብቼ ስለነበር ሰውነቴን በንቅሳት መሸፈንና መጠጣት ጀመርኩ።
አሥራ ስድስት ዓመት ሲሆነኝ በየቀኑ ከ10 እስከ 15 ጠርሙስ ቢራ እጠጣ ነበር፤ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ዕፅ መውሰድ ጀመርኩ። ሱሴን የማረካበት ገንዘብ ለማግኘት የተጣሉ ብረቶችን እሸጥ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በስርቆት ሥራ ላይ ተሰማርቼ ነበር። በ17 ዓመቴ የእስር ቤት ሕይወት ምን እንደሚመስል ቀመስኩ። በስርቆትና በዓመፅ የተነሳ በድምሩ 18 ጊዜ ተፈርዶብኛል።
በ20ዎቹ ዕድሜዬ መጀመሪያ ላይ ሕይወቴ ይበልጥ እየተበላሸ ሄደ። በቀን ውስጥ እስከ 20 ጥቅል የማሪዋና ሲጋራዎችን አጨስ እንዲሁም ሄሮይንና ሌሎች በሕግ የታገዱ ዕፆችን እወስድ ነበር። ከመጠን በላይ ዕፅ ወስጄ ሞት አፋፍ የደረስኩባቸው ብዙ ጊዜያት ነበሩ። ከዚያም ዕፅ ማዘዋወር ጀመርኩ፤ በመሆኑም ጩቤና ሽጉጥ ምንጊዜም ከእጄ አይለይም። በሆነ ወቅት አንድ ሰው ላይ ተኮስኩበት፤ ደግነቱ ጥይቷ የቀበቶው ዘለበት ላይ ነጥራ ተፈናጠረች! በኋላም በ24 ዓመቴ እናቴ ስትሞት ይባስ ብስጩ ሆንኩ። መንገደኞች ወደ እነሱ አቅጣጫ ስመጣ ፈርተው ይሻገሩ ነበር። ብዙ ጊዜ ስለምደባደብ ቅዳሜና እሁድን የማሳልፈው በፖሊስ ጣቢያ አሊያም በሆስፒታል ውስጥ ቁስሌን በማሰፋት ነበር።
በ28 ዓመቴ ትዳር መሠረትኩ። መቼም ሚስቱን በአክብሮት ይይዛታል ብላችሁ አትጠብቁም፤ እሰድባትና እደበድባት ነበር። እንደ ባልና ሚስት አብረን የምናደርገው አንድም ነገር አልነበረም። ሰርቄ በማመጣላት ጌጣጌጥ እሷን ማንቆጥቆጥ በቂ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ከዚያ ግን አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ። ባለቤቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ከመጀመሪያ
ጥናቷ በኋላ ሲጋራ ማጨስ አቆመች፣ ሰርቄ የማመጣውን ገንዘብ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች እንዲሁም የሰጠኋትን ጌጣጌጦች መለሰችልኝ። በዚህ ጊዜ ብግን አልኩ። መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናቷ እቃወማት እንዲሁም ፊቷ ላይ የሲጋራ ጭስ አቦንባት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በሰፈራችን ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ፊት አሾፍባት ነበር።አንድ ቀን ማታ በስካር መንፈስ መኖሪያ ቤታችንን በእሳት አያያዝኩት። ባለቤቴ እኔንም ሆነ አምስት ዓመት የሆናት ልጃችንን ከእሳቱ አዳነችን። ስካሩ ከለቀቀኝ በኋላ በጸጸት ስሜት ተዋጥኩ። አምላክ ፈጽሞ ይቅር ሊለኝ እንደማይችል ተሰማኝ። በአንድ ወቅት አንድ ቄስ ክፉዎች ወደ ገሃነመ እሳት ይጣላሉ ብሎ የተናገረውን አስታወስኩ። ይባስ ብሎም የአእምሮ ሐኪሜ “ያንተ ነገር አብቅቶለታል! ፈጽሞ ልትሻሻል አትችልም” አለኝ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?
ቤታችን በእሳት ከተቃጠለ በኋላ ከባለቤቴ ወላጆች ጋር መኖር ጀመርን። የይሖዋ ምሥክሮች ባለቤቴ ጋ ሲመጡ “አምላክ ያን ሁሉ ኃጢአት ይቅር ይለኛል?” ብዬ ጠየቅኳቸው። እነሱም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ 1 ቆሮንቶስ 6:9-11ን አሳዩኝ። ዘገባው አምላክ የሚያወግዛቸውን ድርጊቶች ከዘረዘረ በኋላ “አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ” ይላል። እዚህ ጥቅስ ላይ ያለው ሐሳብ፣ ለውጥ ማድረግ እንደምችል አሳመነኝ። ከዚያም እነዚያ የይሖዋ ምሥክሮች 1 ዮሐንስ 4:8ን አሳይተው አምላክ እንደሚወደኝ በመግለጽ አረጋጉኝ። የነገሩኝ ነገር ስላበረታታኝ በሳምንት ሁለቴ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠኑኝ ጠየቅኳቸው፤ በጉባኤ ስብሰባዎችም ላይ መገኘት ጀመርኩ። ደግሞም ወደ ይሖዋ ደጋግሜ እጸልይ ነበር።
ከአንድ ወር በኋላ ዕፅ መውሰድና አልኮል መጠጣት ለማቆም ወሰንኩ። ብዙም ሳይቆይ ግን ሰውነቴ ተተራመሰብኝ! የሚያስጨንቅ ቅዠት፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻ መሸማቀቅና ሱስ ከማቆም ጋር የተያያዙ ሌሎች ችግሮች ያጋጥሙኝ ጀመር። በሌላ በኩል ግን በወቅቱ ይሖዋ እጄን እንደያዘኝ እንዲሁም እያበረታኝ እንደሆነ ተሰማኝ። ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰማው ዓይነት ስሜት አደረብኝ። አምላክ ያደረገለትን እርዳታ በተመለከተ ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:13) በጊዜ ሂደት ትንባሆ ማጨስም አቆምኩ።—2 ቆሮንቶስ 7:1
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን እንዳስተካክል የረዳኝ ከመሆኑም ሌላ የቤተሰቤ ሕይወት እንዲሻሻልም አድርጓል። ለባለቤቴ የነበረኝ አመለካከት ተለወጠ። እሷን በአክብሮት መያዝ ብሎም “እባክሽ” እና “አመሰግናለሁ” የሚሉትን ቃላት መጠቀም ጀመርኩ። በተጨማሪም የአባትነት ኃላፊነቴን በሚገባ መወጣት ጀመርኩ። ለአንድ ዓመት ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ካጠናሁ በኋላ የባለቤቴን አርዓያ በመከተል ሕይወቴን ለይሖዋ ወስኜ ተጠመቅኩ።
ያገኘሁት ጥቅም፦
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ሕይወቴን እንዳተረፈልኝ ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም። የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑት የቤተሰቤ አባላት ሳይቀር፣ በምወስደው ዕፅ የተነሳ ልሞት ወይም በድብድብ መሃል ልገደል እችል እንደነበር ይሰማቸዋል።
ባልና አባት እንደመሆኔ መጠን ምን ኃላፊነቶች እንዳሉብኝ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ የቤተሰቤ ሕይወት ሙሉ በሙሉ እንዲቀየር አስችሏል። (ኤፌሶን 5:25፤ 6:4) የተለያዩ ነገሮችን በቤተሰብ ደረጃ አብረን ማከናወን ጀመርን። ባለቤቴ ከኩሽና እንዳትወጣ ከማድረግ ይልቅ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆና ስታገለግል በደስታ እደግፋታለሁ። እሷ ደግሞ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ ኃላፊነቴን ስወጣ በደስታ ትደግፈኛለች።
ይሖዋ አምላክ ያሳየኝ ፍቅርና ምሕረት በሕይወቴ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ተስፋ የላቸውም ተብለው ለሚታዩ ሰዎች ስለ ይሖዋ ባሕርያት ለመናገር በጣም እጓጓለሁ፤ ምክንያቱም ብዙዎች ለእኔ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ነበራቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውም ሰው ንጹሕና ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት እንዲችል የመርዳት ኃይል እንዳለው አውቃለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወንድ ሴት ሳልል ለሰው ሁሉ ፍቅርና አክብሮት እንዳሳይ ያስተማረኝ ከመሆኑም ሌላ ለራሴም አክብሮት እንዲኖረኝ አስችሎኛል።