“አምላክ የት ነበር?”
“‘አምላክ የት ነበር?’ የሚለውን ጥያቄ በተደጋጋሚ አነሳለሁ።”— ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ፣ በፖላንድ የሚገኘውን የኦሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ በጎበኙበት ጊዜ።
አሳዛኝ ነገር ሲከሰት ተመልክተህ ‘አምላክ የት ነበር?’ ብለህ የጠየቅክበት ጊዜ አለ? ወይም በራስህ ሕይወት ላይ የደረሰብህ አንድ አሰቃቂ ሁኔታ አምላክ በግለሰብ ደረጃ ለአንተ የሚያስብልህ መሆኑን እንድትጠራጠር አድርጎህ ይሆን?
ምናልባት አንተም በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ሺላ የተሰማት ዓይነት ስሜት ይሰማህ ይሆናል። አጥባቂ ሃይማኖተኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ያደገችው ሺላ እንዲህ ብላለች፦ “አምላክ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ወደ እሱ የመቅረብ ፍላጎት ነበረኝ። ሆኖም አምላክ ለእኔ ቅርብ እንደሆነ ተሰምቶኝ አያውቅም። እንደሚያየኝ ባምንም እንዲህ የሚያደርገው ከሩቅ ሆኖ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። አምላክ ይጠላኛል ብዬ አስቤ አላውቅም፤ ግን እንደሚያስብልኝም አይሰማኝም።” ሺላ እንዲህ የተሰማት ለምንድን ነው? እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ቤተሰባችን ተደራራቢ መከራ በደረሰበት ወቅት አምላክ ጨርሶ የተወን ይመስል ነበር።”
እንደ ሺላ ሁሉ አንተም ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ ስለመኖሩ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። ሆኖም በእርግጥ ለአንተ እንደሚያስብ አይሰማህ ይሆናል። በፈጣሪ ኃይልና ጥበብ ላይ እምነት የነበረው ጻድቁ ኢዮብም ተመሳሳይ ጥርጣሬ አድሮበት ነበር። (ኢዮብ 2:3፤ 9:4) ኢዮብ ማባሪያ የሌለው የሚመስል ተደራራቢ መከራ በደረሰበት ጊዜ አምላክን “ፊትህን የምትሰውረውና እንደ ጠላትህ የምትቆጥረኝ ለምንድን ነው?” በማለት ጠይቆታል።—ኢዮብ 13:24
መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል? ለሚደርስብን አሳዛኝ ነገር ተጠያቂው አምላክ ነው? አምላክ በአጠቃላይ ለሰው ልጆችም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ለእያንዳንዳችን እንደሚያስብ የሚያሳይ ማስረጃ አለ? በግለሰብ ደረጃ እያንዳንዳችን አምላክ ትኩረት እንደሚሰጠን፣ ስሜታችንን እንደሚረዳልን፣ ሥቃያችን እንደሚሰማው ወይም በችግራችን እንደሚደርስልን በእርግጥ ማወቅ እንችላለን?
በቀጣዮቹ ርዕሶች ላይ፣ እኛ የሰው ልጆች የተፈጠርንበት መንገድ አምላክ እንደሚያስብልን የሚጠቁመው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። (ሮም 1:20) ከዚያም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አምላክ እንደሚያስብልን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን እንመረምራለን። በፍጥረታቱና በቃሉ አማካኝነት አምላክን ይበልጥ ‘ስታውቀው’ ለአንተ ‘የሚያስብልህ ስለመሆኑ’ ይበልጥ እርግጠኛ እየሆንክ ትሄዳለህ።—1 ዮሐንስ 2:3፤ 1 ጴጥሮስ 5:7