በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጂኖች ላይ ለውጥ በማድረግ የሰዎችን ዕድሜ ማስረዘም ተችሏል?

ረጅም ዕድሜ ለመኖር የሚደረግ ጥረት

ረጅም ዕድሜ ለመኖር የሚደረግ ጥረት

“አምላክ የሰው ልጆች እንዲጠመዱበት የሰጣቸውን ሥራ ተመለከትኩ። አምላክ ሁሉንም ነገር በወቅቱ ውብ አድርጎ ሠርቶታል። ደግሞም ዘላለማዊነትን በልባቸው ውስጥ አኑሯል።”​መክብብ 3:10, 11

ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን ከበርካታ ዘመናት በፊት የተናገረው ይህ ሐሳብ የሰው ልጆችን ስሜት በትክክል የሚገልጽ ነው። ሕይወት አጭር፣ ሞትም አይቀሬ በመሆኑ ረጅም ዕድሜ የመኖር ጉጉት በሰው ልጆች ልብ ውስጥ እንደተቀረጸ ኖሯል። ከጥንት ጀምሮ፣ ረጅም ዕድሜ ለመኖር የሚያስችለውን ሚስጥር ለማግኘት ስለታገሉ ሰዎች የሚናገሩ በርካታ ታሪኮችና ገድሎች አሉ።

ለምሳሌ የሱሜሪያውያን ንጉሥ የሆነውን ጊልጋሜሽን በተመለከተ የሚነገሩ ብዙ አፈ ታሪኮች አሉ። “የጊልጋሜሽ ትውፊት” እንደሚናገረው ጊልጋሜሽ ከሞት ማምለጥ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ አደገኛ ጉዞ አድርጎ ነበር። ሆኖም ጥረቱ አልተሳካም።

በመካከለኛው ዘመን አንድ አልኬሚስት ቤተ ሙከራው ውስጥ ሆኖ

በአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በቻይና የሚገኙ አልኬሚስቶች ለዘላለም መኖር የሚያስችል አስማታዊ ኃይል ያለው መድኃኒት ለመሥራት ሞክረው ነበር። በውጤቱም ሜርኩሪና አርሴኒክ የተቀላቀለበት መድኃኒት ቀመሙ። ይህ መድኃኒት ለበርካታ የቻይና ነገሥታት ሞት ምክንያት እንደሆነ ይገመታል። በመካከለኛው ዘመን ደግሞ በአውሮፓ የሚገኙ አልኬሚስቶች ከወርቅ ምግብ ለማዘጋጀት ሞከሩ፤ ወርቅ ያለው በቀላሉ ያለመበላሸት ባሕርይ የሰዎችን ዕድሜ እንደሚያስረዝም አስበው ነበር።

በዛሬው ጊዜም አንዳንድ የባዮሎጂና የጄኔቲክስ ተመራማሪዎች የእርጅናን መንስኤ ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ። ይህም በጥንት ጊዜ ሰዎች “ለዘላለም መኖር የሚያስችል መድኃኒት” ይፈልጉ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም እርጅናንና ሞትን ለማስቀረት መሞከራቸውን እንዳላቆሙ ያሳያል። ታዲያ እንዲህ ያለው ምርምር ምን ውጤት አስገኘ?

አምላክ “ዘላለማዊነትን በልባቸው ውስጥ አኑሯል።”​—መክብብ 3:10, 11

በዘመናችን የእርጅናን መንስኤ ለማወቅ የሚደረግ ጥረት

ስለ ሰዎች ሴል የሚያጠኑ ሳይንቲስቶች የምናረጀውና የምንሞተው ለምን እንደሆነ የሚገልጹ ከ300 የሚበልጡ ንድፈ ሐሳቦችን አቅርበዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሞለኪውላር ባዮሎጂ ተመራማሪዎች ጂኖችና ፕሮቲኖች ላይ ለውጥ በማድረግ የቤተ ሙከራ እንስሳትና ከሰው የተወሰዱ ሴሎች ቶሎ እንዳያረጁ ማድረግ ችለዋል። እንዲህ ያሉ ግኝቶች መኖራቸው አንዳንድ ባለጸጋ ሰዎች የሞትን ምክንያት ለማወቅ በሚደረገው ምርምር ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ አነሳስቷቸዋል። ታዲያ እስካሁን የተደረገው ምርምር ምን ይመስላል?

ዕድሜን ማራዘም። አንዳንድ የባዮሎጂ ተመራማሪዎች የእርጅና መንስኤ ቴሎሜር በመባል ከሚታወቀው የክሮሞዞሞች ጫፍ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይናገራሉ። ሴሎቻችን በሚባዙበት ጊዜ ቴሎሜሮች በሴሎች ውስጥ ያለው ጄኔቲካዊ መረጃ እንዳይጠፋ ይከላከላሉ። ሆኖም ሴሎቹ በተባዙ ቁጥር ቴሎሜሮቹ እያጠሩ ይሄዳሉ። ከጊዜ በኋላ ሴሎቹ መባዛት ስለሚያቆሙ እርጅና ይመጣል።

በ2009 የኖቤል ሎሬት የሆኑት ፕሮፌሰር ኤሊዛቤት ብላክበርን እና የቡድናቸው አባላት ቴሎሜሮች ቶሎ እንዳያጥሩ በማድረግ ሴሎች ቶሎ እንዳያረጁ የሚያደርግ ኢንዛይም አግኝተዋል። ሆኖም በጻፉት ሪፖርት ላይ እንደገለጹት ቴሎሜሮች “በራሳቸው ዕድሜያችንን አያረዝሙልንም፤ ከተለመደው የዕድሜ ጣሪያ በላይ እንድንኖር አያስችሉንም።”

በሴሎች ላይ ለውጥ ማድረግ። በሴሎች ላይ ለውጥ በማድረግም እርጅናን ለማስቀረት ተሞክሮ ነበር። ሴሎቻችን አርጅተው መባዛት ሲያቆሙ በአቅራቢያቸው ላሉ በሽታ ተከላካይ ሴሎች የተሳሳተ መልእክት ሊልኩ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ ሰውነታችን እንዲቆጣ፣ ከባድ ሕመም እንዲሰማን ብሎም በበሽታ እንድንያዝ ሊያደርግ ይችላል። በቅርቡ በፈረንሳይ የሚገኙ ሳይንቲስቶች ከአረጋውያን በተወሰዱ ሴሎች ላይ ለውጥ አድርገው ነበር፤ አንዳንዶቹ ሴሎች የተወሰዱት 100 ዓመት ካለፋቸው አረጋውያን ነው። የተመራማሪዎቹ ቡድን መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ዣን ማርክ ለሜትረ እንደተናገሩት ጥናቱ በሴሎች ላይ “እርጅናን መቀልበስ እንደሚቻል” ያሳያል።

ሳይንስ ዕድሜያችንን ሊያረዝምልን ይችላል?

ብዙ ሳይንቲስቶች፣ እርጅናን ለማስቀረት የሚደረጉት ሕክምናዎች የሰውን ዕድሜ አሁን ካለው ይበልጥ ሊያስረዝሙ እንደሚችሉ አይሰማቸውም። እርግጥ ነው፣ ከ19ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ የሰዎች የዕድሜ ጣሪያ እየጨመረ መጥቷል። ሆኖም ይህ በዋነኝነት የሆነው ከንጽሕና አጠባበቅና ተላላፊ በሽታዎችን ከመከላከል ጋር በተያያዘ መሻሻል ስለታየ እንዲሁም አንቲባዮቲኮችና ክትባቶች ስለተስፋፉ ነው። አንዳንድ የጄኔቲክስ ተመራማሪዎች የሰውን ልጅ ዕድሜ አሁን ከደረሰበት እምብዛም ማስረዘም እንደማይቻል ይናገራሉ።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ የሆነው ሙሴ ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የዕድሜያችን ርዝማኔ 70 ዓመት ነው፤ ለየት ያለ ጥንካሬ ካለን ደግሞ 80 ዓመት ቢሆን ነው። ይህም በችግርና በሐዘን የተሞላ ነው፤ ፈጥኖ ይነጉዳል፤ እኛም እናልፋለን።” (መዝሙር 90:10) የሰው ልጆች ዕድሜያቸውን ለማርዘም ብዙ ጥረት ቢያደርጉም የሰዎች ዕድሜ አሁንም ጥቅሱ ከሚገልጸው የዘለለ አይደለም።

በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የኤሊ ዝርያዎች ከ150 ዓመት በላይ መኖር ይችላሉ፤ እንደ አርዘ ሊባኖስ ያሉ ዛፎች ደግሞ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ይኖራሉ። የእኛን ዕድሜ እንዲህ ካሉ ፍጥረታት ጋር ስናወዳድር “ሕይወት በቃ 70 ወይም 80 ዓመት ብቻ ነው?” ብለን መጠየቃችን አይቀርም።