በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጠላታችን ሞት የሚጠፋው እንዴት ነው?

ጠላታችን ሞት የሚጠፋው እንዴት ነው?

የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን አለመታዘዛቸው በመላው የሰው ዘር ላይ ኃጢአትንና ሞትን ቢያመጣም አምላክ ለሰዎች የነበረው ዓላማ አልተለወጠም። አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይህ ዓላማው እንዳልተለወጠ በተደጋጋሚ ገልጿል።

  • “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።”​መዝሙር 37:29

  • “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፤ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።”​ኢሳይያስ 25:8

  • “የመጨረሻው ጠላት፣ ሞት ይደመሰሳል።”​1 ቆሮንቶስ 15:26

  • “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።”​ራእይ 21:4

አምላክ ሞትን ‘የሚውጠው’ ወይም የሚደመስሰው እንዴት ነው? ከላይ እንደተጠቀሰው፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን . . . ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት በግልጽ ይናገራል። ሆኖም “ሁልጊዜ ጥሩ ነገር የሚያደርግ . . . ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም” በማለትም ይገልጻል። (መክብብ 7:20) ታዲያ አምላክ ሞትን ለማጥፋት ሲል የራሱን መሥፈርት ይሽራል? ይህ የማይሆን ነገር ነው! ‘አምላክ ሊዋሽ ስለማይችል’ በፍጹም እንዲህ አያደርግም። (ቲቶ 1:2) ታዲያ አምላክ ሰዎችን ሲፈጥር የነበረውን ፍቅራዊ ዓላማ የሚፈጽመው እንዴት ነው?

አምላክ “ሞትን ለዘላለም ይውጣል።”​—ኢሳይያስ 25:8

ሞትን ለማጥፋት የተከፈለ ቤዛ

ይሖዋ አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ ቤዛ በመክፈል ከሞት ነፃ የምንወጣበትን ዝግጅት አደረገ። ቤዛ የሚባለው፣ ጉዳት የደረሰበትን አካል ለመካስ ወይም ፍትሕ ለማስገኘት የሚከፈል ተመጣጣኝ ዋጋ ነው። የሰው ልጆች በሙሉ ኃጢአተኞች ስለሆኑ ሞት ይገባቸዋል፤ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት በግልጽ ይናገራል፦ “አንዳቸውም ቢሆኑ ሌላውን ሰው መዋጀት፣ ወይም ለእሱ ቤዛ የሚሆን ነገር ለአምላክ መክፈል ጨርሶ አይችሉም፤ (ለሕይወታቸው የሚከፈለው የቤዛ ዋጋ እጅግ ውድ ስለሆነ መቼም ቢሆን ከአቅማቸው በላይ ነው)።”—መዝሙር 49:7, 8

ፍጹም ያልሆነ ሰው ሲሞት የሚከፍለው ለራሱ ኃጢአት የሚገባውን ቅጣት ብቻ ነው፤ ራሱን መዋጀት ወይም ለሌሎች ኃጢአት ቤዛ መክፈል አይችልም። (ሮም 6:7) ከሞት ነፃ መውጣት የምንችለው፣ ለራሱ ኃጢአት ቅጣት መክፈል የማያስፈልገው ፍጹም ሰው ለእኛ ኃጢአት ሲል ከሞተልን ብቻ ነው።—ዕብራውያን 10:1-4

አምላክ እንዲህ ያለ ዝግጅት አድርጎልናል። ልጁ ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት ፍጹም ሰው ሆኖ እንዲወለድ ከሰማይ ወደ ምድር ላከው። (1 ጴጥሮስ 2:22) ኢየሱስ፣ ወደ ምድር የመጣው “በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት” እንደሆነ ተናግሯል። (ማርቆስ 10:45) ኢየሱስ የሞተው ጠላት የሆነውን ሞትን በማጥፋት ሕይወት ሊያስገኝልን ነው።—ዮሐንስ 3:16

ሞት የሚጠፋው መቼ ነው?

አሁን የምንኖረው “ለመቋቋም [በሚያስቸግር] በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ ነው፤ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት በዚህ ክፉ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀናት’ ውስጥ እንደምንኖር ያሳያል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) የመጨረሻዎቹ ቀናት የሚያበቁት ‘ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች የሚጠፉበት የፍርድ ቀን’ ሲመጣ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:3, 7) አምላክን የሚወዱ ሰዎች ግን ከዚህ ጥፋት ተርፈው ‘የዘላለም ሕይወት’ ያገኛሉ።—ማቴዎስ 25:46

ኢየሱስ የመጣው “በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት” ነው።​—ማርቆስ 10:45

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ከሞት ተነስተው ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ያገኛሉ። ኢየሱስ ወደ ናይን ከተማ በሄደበት ወቅት ትንሣኤ አከናውኗል። ኢየሱስ አንድ ልጇ የሞተባት መበለት አግኝቶ ነበር፤ ስለዚህ “በጣም አዘነላትና” ልጁን ከሞት አስነሳው። (ሉቃስ 7:11-15) ሐዋርያው ጳውሎስም “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል። ይህ አስተማማኝ ተስፋ አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር በማያሻማ ሁኔታ ያሳያል።—የሐዋርያት ሥራ 24:15

በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ይከፈትላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል። (መዝሙር 37:29) በዚያ ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ ከ2,000 ዓመት በፊት የጻፈው አጽናኝ ሐሳብ ሲፈጸም በዓይናቸው ያያሉ፤ ጳውሎስ “ሞት ሆይ፣ ድል አድራጊነትህ የት አለ? ሞት ሆይ፣ መንደፊያህ የት አለ?” ብሎ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:55) ያን ጊዜ የሰው ልጆች ዋነኛ ጠላት የሆነው ሞት ይሸነፋል!