በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሞት የሚያመልጥ የለም

ከሞት የሚያመልጥ የለም

አንድ ፊልም እያየህ ነው እንበል፤ ፊልሙ የሚያጠነጥነው በጣም በምታደንቃት አንዲት ታዋቂ ሙዚቀኛ ሕይወት ዙሪያ ነው። ፊልሙ ሲጀምር ስለ ሙዚቀኛዋ አስተዳደግ፣ ስላገኘችው የሙዚቃ ሥልጠናና ሌት ተቀን ታደርግ ስለነበረው ልምምድ ይገልጻል። ከዚያም ሲቀጥል በተለያዩ አገሮች እየዞረች የሙዚቃ ሥራዋን በማቅረብ ዓለም አቀፍ ተወዳጅነት ማትረፏን ይናገራል። ብዙም ሳይቆይ ስለ እርጅና ዘመኗ ያሳያል፤ ከዚያም በፊልሙ መጨረሻ ላይ ሙዚቀኛዋ ትሞታለች።

ይህ ፊልም ልብ ወለድ ሳይሆን በአንድ ወቅት በሕይወት የኖረች ሴት እውነተኛ ታሪክ ነው። ስለ የትኛውም ሙዚቀኛ፣ የሳይንስ ምሁር፣ አትሌትም ሆነ ሌላ ታዋቂ ሰው ፊልም ቢዘጋጅ ታሪኩ ከዚህ ብዙም የተለየ አይሆንም። ግለሰቡ በሕይወት ሳለ ብዙ ነገር አከናውኖ ሊሆን ይችላል፤ እርጅናና ሞት ባይኖር ኖሮ ደግሞ ምን ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል እስቲ አስበው!

የሚያሳዝነው የሁላችንም መጨረሻ ይኸው ነው። (መክብብ 9:5) የሰው ልጅ የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርግ እርጅናንና ሞትን ማስቀረት አልቻለም። ይባስ ብሎ ደግሞ በድንገተኛ አደጋ ወይም በከባድ ሕመም ምክንያት ሕይወታችን በአጭሩ ሊቀጭ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው “ለጥቂት ጊዜ ታይቶ እንደሚጠፋ እንፋሎት” ነን።—ያዕቆብ 4:14

አንዳንዶች “ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ” የሚል መርሕ ይከተላሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:32) ሰዎች ሕይወታቸውን በዚህ መንገድ የሚመሩት፣ ሕይወት አጭርና ተስፋ ቢስ ስለሚሆንባቸው ነው። አንተም በሆነ ወቅት ላይ በተለይም ከባድ መከራ ሲያጋጥምህ ‘ሕይወት በቃ ይኸው ነው?’ ብለህ መጠየቅህ አይቀርም። ለመሆኑ የዚህን ጥያቄ መልስ ከየት ማግኘት ይቻላል?

ብዙዎች ሳይንስ ለዚህ ጥያቄ መልስ እንደሚሰጥ ይሰማቸዋል። እርግጥ በሳይንስና በሕክምና መስክ እየታየ ያለው እድገት የሰዎች የዕድሜ ጣሪያ ከፍ እንዲል አድርጓል። አንዳንድ ሳይንቲስቶች ደግሞ የሰዎችን ሕይወት ከዚህም ይበልጥ ለማራዘም እየሞከሩ ነው። የእነዚህ ሳይንቲስቶች ሙከራ የሚያስገኘው ውጤት ምንም ሆነ ምን ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልገናል፦ የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው? ጠላታችን የሆነው ሞት የሚጠፋበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ቀጣዮቹ ርዕሶች እነዚህን ነጥቦች የሚያብራሩ ከመሆኑም ሌላ ‘ሕይወት በቃ ይኸው ነው?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣሉ።