በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተፈጠርነው ለዘላለም እንድንኖር ነው

የተፈጠርነው ለዘላለም እንድንኖር ነው

ረጅምና አስደሳች ሕይወት መኖር የማይፈልግ ማን አለ? ጤናማና ደስተኛ ሆኖ ለዘላለም መኖር ቢቻል ሕይወት ምን እንደሚመስል አስበው! ከቤተሰቦቻችንና ከጓደኞቻችን ጋር የምንዝናናበት፣ ዓለምን የምንዞርበት፣ አዳዲስ ነገሮችን የምንማርበት፣ ጥበብ የምናካብትበትና ስለፈለግነው ነገር እውቀት የምንቀስምበት በቂ ጊዜ ይኖረናል።

እንዲህ ያለው ምኞት የማይጨበጥ ሕልም ነው? በጭራሽ! መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህን ምኞት በውስጣችን ያኖረው አምላክ እንደሆነ ይናገራል። (መክብብ 3:11) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 4:8) ታዲያ አፍቃሪ የሆነ አምላክ ለዘላለም የመኖር ፍላጎት በውስጣችን ከፈጠረ በኋላ ይህ ምኞት የሕልም እንጀራ ሆኖ እንዲቀር የሚያደርግ ይመስልሃል?

መሞት የሚፈልግ ማንም የለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን “ጠላት” በማለት ይጠራዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:26) ፈጠነም ዘገየ ሞት የሁላችንንም በር ማንኳኳቱ አይቀርም። ብዙዎች ስለ ሞት ማሰብ እንኳ አይፈልጉም፤ እንዲያውም ያስፈራቸዋል። ታዲያ ይህ ጠላት የሚጠፋበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

ተስፋ እንዳለን የሚያሳይ ማስረጃ

የአምላክ ዓላማ የሰው ልጆች እንዲሞቱ እንዳልነበር ታውቃለህ? የዘፍጥረት መጽሐፍ የአምላክ ዓላማ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ እንደነበር የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ይዟል። ይሖዋ አምላክ ምድርን ያዘጋጃት ለሰው ልጆች ምቹ መኖሪያ እንድትሆን አድርጎ ነው። ከዚያም የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ፈጥሮ በኤደን ገነት ውስጥ አኖረው። “ከዚያ በኋላ አምላክ የሠራውን እያንዳንዱን ነገር ተመለከተ፤ እነሆ፣ እጅግ መልካም ነበር!”—ዘፍጥረት 1:26, 31

በአምላክ መልክ የተፈጠረው አዳም ፍጹም ሰው ነበር። (ዘዳግም 32:4) የአዳም ሚስት የሆነችው ሔዋንም ምንም ዓይነት እንከን የሌለባት፣ ፍጹም አካልና ፍጹም አእምሮ ያላት ሴት ነበረች። ይሖዋ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም። እንዲሁም የባሕር ዓሣዎችን፣ በሰማያት ላይ የሚበርሩ ፍጥረታትንና በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረታትን በሙሉ ግዟቸው።”—ዘፍጥረት 1:28

አዳምና ሔዋን ምድርን በዘሮቻቸው ለመሙላት ረጅም ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ነው። ሔዋን ልጆች ትወልዳለች፤ ልጆቿም ልጆች ይወልዳሉ፤ በዚህ መልኩ በአምላክ ዓላማ መሠረት ምድር ትሞላለች። (ኢሳይያስ 45:18) ታዲያ ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን የፈጠራቸው ምድር በዘሮቻቸው ስትሞላ ሳይመለከቱ ልጆችና የልጅ ልጆች አይተው እንዲሞቱ ብቻ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ዓይነት ተስፋ ይሰጣቸው ነበር?

በተጨማሪም አዳምና ሔዋን እንስሳትን እንዲገዙ አምላክ አዝዟቸዋል። አዳም ለእንስሳቱ ስም እንዲያወጣ ተነግሮት ነበር፤ ይህ ጊዜ እንደሚፈልግ ጥያቄ የለውም። (ዘፍጥረት 2:19) ሆኖም አዳም እነዚህን እንስሳት ለመግዛት ስለ እነሱ መማርና እንዴት እንደሚንከባከባቸው ማወቅ ያስፈልገው ነበር። ይህ ደግሞ ስም ከማውጣት የበለጠ ጊዜ ይፈልጋል።

አምላክ ምድርን እንዲሞሉና እንስሳትን እንዲገዙ የሰጠው መመሪያ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የተፈጠሩት ረጅም ዕድሜ እንዲኖሩ እንደሆነ ያመለክታል። ለነገሩ አዳም በጣም ረጅም ዕድሜ ኖሯል።

የአምላክ ዓላማ የሰው ልጆች ምድር ላይ በገነት ለዘላለም እንዲኖሩ ነው

በጣም ረጅም ዕድሜ ኖረዋል

አዳም፣ 930 ዓመት

ማቱሳላ፣ 969 ዓመት

ኖኅ፣ 950 ዓመት

በዘመናችን፣ ከ70-80 ዓመት

መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ወቅት ሰዎች በጣም ረጅም ዕድሜ ይኖሩ እንደነበር ይናገራል። “አዳም በአጠቃላይ 930 ዓመት ኖረ” ይላል። ከዚያም ከ900 ዓመት በላይ የኖሩ ሌሎች ስድስት ሰዎችን ስም ይጠቅሳል፤ እነሱም ሴት፣ ሄኖስ፣ ቃይናን፣ ያሬድ፣ ማቱሳላ እና ኖኅ ናቸው። ሁሉም የኖሩት በኖኅ ዘመን የደረሰው የጥፋት ውኃ ከመምጣቱ በፊት ሲሆን ኖኅ የጥፋት ውኃው ከመምጣቱ በፊት 600 ዓመት ኖሯል። (ዘፍጥረት 5:5-27፤ 7:6፤ 9:29) እነዚህ ሰዎች ይህን ያህል ረጅም ዕድሜ ሊኖሩ የቻሉት እንዴት ነው?

እነዚህ ሰዎች የኖሩት፣ አዳምና ሔዋን ፍጹም ሆነው ከኖሩበት ዘመን ብዙም ሳይርቅ ነው። ረጅም ዕድሜ እንዲኖሩ ያደረጋቸው ዋነኛው ነገር ይህ ሳይሆን አይቀርም። ይሁንና ፍጽምና ረጅም ዕድሜ ከመኖር ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? ሞት የሚጠፋውስ እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ የምናረጀውና የምንሞተው ለምን እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል።