የሚያስጨንቃችሁን ነገር ሁሉ በይሖዋ ላይ ጣሉ
“የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ [በይሖዋ] ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”—1 ጴጥ. 5:7
1, 2. (ሀ) ጭንቀት የሚሰማን ለምን ሊሆን ይችላል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
የምንኖረው በጣም አስጨናቂ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው። በቁጣ የተሞላው ሰይጣን ዲያብሎስ “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል።” (1 ጴጥ. 5:8፤ ራእይ 12:17) በመሆኑም የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ጭንቀት ቢሰማቸው የሚያስገርም አይደለም። እንደ ንጉሥ ዳዊት ያሉ በጥንት ጊዜ የኖሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው የይሖዋ አገልጋዮች ‘በጭንቀት የተዋጡበት’ ወቅት ነበር። (መዝ. 13:2) ሐዋርያው ጳውሎስም “የሚያስጨንቀኝ የጉባኤዎች ሁሉ ሐሳብ ነው” እንዳለ ታስታውስ ይሆናል። (2 ቆሮ. 11:28) ታዲያ በጭንቀት ስንዋጥ ምን ማድረግ እንችላለን?
2 በሰማይ የሚኖረው አፍቃሪ አባታችን፣ በጥንት ዘመን የኖሩ አገልጋዮቹን ረድቷቸዋል፤ እኛም በጭንቀት በምንዋጥበት ወይም በምንረበሽበት ጊዜ ሊያሳርፈን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያስጨንቃችሁንም [“የሚያሳስባችሁንም፣” ግርጌ] ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል” በማለት ይመክረናል። (1 ጴጥ. 5:7) ይሁንና ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምትችልባቸው አራት መንገዶች አሉ፤ እነሱም (1) ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረብ፣ (2) የአምላክን ቃል ማንበብና ባነበብከው ነገር ላይ ማሰላሰል፣ (3) ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጥህ መጠየቅ፣ (4) ጭንቀትህን ለምትቀርበው ሰው ማካፈል ናቸው። እነዚህን አራት መንገዶች ስንመረምር ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልግህ በየትኞቹ አቅጣጫዎች እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር።
“ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል”
3. በጸሎት አማካኝነት ‘ሸክምህን በይሖዋ ላይ መጣል’ የምትችለው እንዴት ነው?
3 ጭንቀትን ለማቅለል ልንወስደው የምንችለው የመጀመሪያው እርምጃ ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ነው። የሚረብሽ፣ የሚያስፈራ ወይም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥምህ በሰማይ ላለው አፍቃሪ አባትህ የልብህን አውጥተህ ንገረው። መዝሙራዊው ዳዊት “አምላክ ሆይ፣ ጸሎቴን ስማ” ሲል ይሖዋን ተማጽኗል። በዚያው መዝሙር ላይ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 55:1, 22) አንድን ችግር ለመፍታት የቻልከውን ያህል ጥረት ካደረግህ በኋላ፣ የተሻለ የሚሆነው ስለ ጉዳዩ መጨነቅ ሳይሆን ወደ ይሖዋ ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረብ ነው። ይሁንና ጸሎት፣ በሚያስጨንቁና እረፍት በሚነሱ ሐሳቦች እንዳትዋጥ የሚረዳህ እንዴት ነው?—መዝ. 94:18, 19 ግርጌ
4. በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜ ጸሎት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ። ይሖዋ ደጋግመን ለምናቀርበው ከልብ የመነጨ ምልጃ ምላሽ ይሰጣል። እንዴት? አእምሯችንንና ልባችንን፣ ከሚረብሹ ስሜቶች የሚያሳርፍ ውስጣዊ ሰላም በመስጠት ነው። በርካታ ሰዎች ይህን በሕይወታቸው ተመልክተዋል። አምላክ ጭንቀታቸውና ስጋታቸው ተወግዶ፣ ከመረዳት ችሎታ በላይ የሆነ ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። አንተም እንዲህ ዓይነት ሰላምና መረጋጋት ልታገኝ ትችላለህ። “የአምላክ ሰላም” የሚያጋጥምህን ማንኛውንም ተፈታታኝ ሁኔታ መቋቋም እንድትችል ይረዳሃል። ይሖዋ “እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ” በማለት በገባልን ርኅራኄ የተንጸባረቀበት ቃል ላይ ሙሉ በሙሉ መተማመን ትችላለህ።—ኢሳ. 41:10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውስጣዊ ሰላም
5. የአምላክ ቃል ውስጣዊ ሰላም የሚያስገኝልን እንዴት ነው?
5 ውስጣዊ ሰላም ማግኘት የምንችልበት ሁለተኛው መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማንበብና ባነበብነው ላይ ማሰላሰል ነው። ይህን ማድረጋችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ጭንቀትን ለመከላከል፣ ለመቀነስ አሊያም ለመቋቋም የሚረዳ ጠቃሚ መንፈሳዊ ምክር ይዟል። የአምላክ ቃል፣ ጥበብ የተንጸባረቀበትን የፈጣሪያችንን መልእክት የያዘ በመሆኑ ሊረዳህና ሊያረጋጋህ ይችላል። በአምላክ ቃል ላይ ቀንም ሆነ ሌሊት ማሰላሰልህ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጠቃሚ ምክር እንዴት ተግባራዊ እንደምታደርግ ማሰብህ ትልቅ ብርታት ይሰጥሃል። ይሖዋ፣ ቃሉን ማንበብን “ደፋርና ብርቱ” ከመሆን እንዲሁም ‘ካለመሸበርና ካለመፍራት’ ጋር አያይዞ ገልጾታል።—ኢያሱ 1:7-9
6. የኢየሱስ ትምህርቶች ሊጠቅሙህ የሚችሉት እንዴት ነው?
6 የአምላክን ቃል ስናነብ ኢየሱስ የተናገራቸውን የሚያጽናኑ ሐሳቦች እናገኛለን። ኢየሱስ ያስተማረው ነገር ለአድማጮቹ እረፍት የሚሰጥ ነበር። ክርስቶስ ልባቸው የተጨነቀውን ያረጋጋ፣ የደከሙትን ያበረታ እንዲሁም መንፈሳቸው የተደቆሰውን ያጽናና ስለነበር በርካታ ሰዎች ወደ እሱ ይመጡ ነበር። (ማቴዎስ 11:28-30ን አንብብ።) ኢየሱስ ለሰዎች ፍቅር ስለነበረው ለመንፈሳዊ፣ ለስሜታዊና ለአካላዊ ፍላጎታቸው ትኩረት ይሰጥ ነበር። (ማር. 6:30-32) ኢየሱስ ሰዎችን እንደሚደግፍ የገባውን ቃል በዛሬው ጊዜም ይፈጽማል። አብረውት ይጓዙ እንደነበሩት ሐዋርያት ሁሉ አንተም የዚህን ቃል እውነተኝነት በገዛ ሕይወትህ ልትመለከት ትችላለህ። የኢየሱስን እርዳታ ለማግኘት በአካል ከእሱ ጋር መሆን አያስፈልግህም። በሰማይ ሆኖ የሚገዛው ይህ ንጉሥ ስሜታችንን በመረዳት የሚያስፈልገንን ያደርግልናል። በመሆኑም በምትጨነቅበት ጊዜ ‘ሊደርስልህ’ እንዲሁም ‘እርዳታ በሚያስፈልግህ ጊዜ’ ሊረዳህ ይችላል። በእርግጥም ኢየሱስ አስጨናቂ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚያስችልህ ከመሆኑም ሌላ ልብህ በተስፋና በድፍረት እንዲሞላ ይረዳሃል።—ዕብ. 2:17, 18፤ 4:16
የአምላክ መንፈስ የሚያስገኛቸው ባሕርያት
7. የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ማግኘትህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?
7 በሰማይ ያለው አባታችን ለሚጠይቁት መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጣቸው ኢየሱስ ቃል ገብቷል። (ሉቃስ 11:10-13) በመሆኑም ጭንቀትን ለማቅለል የሚረዳህ ሦስተኛው መንገድ የአምላክን መንፈስ ፍሬ ማፍራትህ ነው። የአምላክ መንፈስ የሚያስገኛቸው እነዚህ መልካም ባሕርያት፣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ማንነት ነጸብራቅ ናቸው። (ገላትያ 5:22, 23ን አንብብ፤ ቆላ. 3:10) የዚህን መንፈስ ፍሬ ስታፈራ ከሌሎች ጋር ያለህ ዝምድና ይሻሻላል። ይህ ደግሞ ጭንቀት ሊያስከትሉ የሚችሉ የተለያዩ ሁኔታዎችን ለማስቀረት ይረዳሃል። የመንፈስ ፍሬ ማፍራትህ እንዴት ሊረዳህ እንደሚችል እስቲ እንመልከት።
8-12. የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ፍሬ ማፍራትህ የሚያስጨንቁ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ወይም ለማስወገድ የሚረዳህ እንዴት ነው?
8 “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም።” ሌሎችን በአክብሮት ለመያዝ ጥረት የምታደርግ ከሆነ በውስጥህ ያሉ አሉታዊ ስሜቶችን ማስወገድ ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የወንድማማች ፍቅር ካለህ እንዲሁም ሌሎችን ከልብ የምትወድና አክብሮት የምታሳያቸው ከሆነ ጭንቀት ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ማስቀረት ትችላለህ።—ሮም 12:10
9 “ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት።” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን “አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ . . . እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ይኖርሃል። (ኤፌ. 4:32) ይህም ጭንቀት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩ ለማድረግ ይረዳሃል። በተጨማሪም ፍጽምና የሚጎድለን በመሆኑ ምክንያት የሚመጡ ችግሮችን በተሻለ መንገድ መፍታት ትችላለህ።
10 “እምነት።” ብዙውን ጊዜ ጭንቀት የሚፈጥርብን ከገንዘብና ከቁሳዊ ነገሮች ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው። (ምሳሌ 18:11) ይሖዋ በፍቅር እንደሚንከባከብህ ጠንካራ እምነት ካለህ ግን እንዲህ ያለውን ጭንቀት መቋቋም አሊያም ማስወገድ ትችላለህ። እንዴት? ሐዋርያው ጳውሎስ “ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ” በማለት በመንፈስ መሪነት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግህ ከብዙ ጭንቀት ያድንሃል። ጳውሎስ አክሎም እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “[አምላክ] ‘ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም’ ብሏልና። ስለዚህ በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?’ እንላለን።”—ዕብ. 13:5, 6
11 “ገርነት፣ ራስን መግዛት።” እነዚህን ባሕርያት ማዳበር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ እስቲ አስበው። እነዚህ ባሕርያት ጭንቀት ሊፈጥሩብህ ከሚችሉ ድርጊቶች እንድትርቅ ይረዱሃል፤ ‘የመረረ ጥላቻን፣ ቁጣን፣ ንዴትን፣ ጩኸትንና ስድብን’ ማስወገድህም እንደሚጠቅምህ ምንም ጥያቄ የለውም።—ኤፌ. 4:31
12 “ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች” ራስህን ዝቅ ለማድረግም ሆነ ‘የሚያስጨንቅህን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ለመጣል’ ትሕትና እንደሚያስፈልግህ ግልጽ ነው። (1 ጴጥ. 5:6, 7) ትሕትና ካዳበርክ ደግሞ የአምላክን ሞገስና ድጋፍ ታገኛለህ። (ሚክ. 6:8) አካልህ፣ አእምሮህና ስሜትህ መቋቋም የሚችለው ነገር ውስን እንደሆነ ከተገነዘብክ በአምላክ ትታመናለህ፤ ይህም ከልክ በላይ እንዳትጨነቅ ይረዳሃል።
“ፈጽሞ አትጨነቁ”
13. ኢየሱስ “ፈጽሞ አትጨነቁ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
13 ኢየሱስ በማቴዎስ 6:34 (ጥቅሱን አንብብ) ላይ “ፈጽሞ አትጨነቁ” የሚል ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጥቷል። ይሁንና ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ከባድ ሊመስል ይችላል። ኢየሱስ “ፈጽሞ አትጨነቁ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? አንድ የአምላክ አገልጋይ በሕይወቱ ውስጥ የሚያስጨንቅ ነገር ጨርሶ እንደማይገጥመው መናገሩ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ዳዊትና ጳውሎስ የተጨነቁበት ጊዜ እንደነበር ቀደም ሲል ተመልክተናል። ኢየሱስ ይህን ሲል፣ አላስፈላጊ ወይም ከልክ ያለፈ ጭንቀት ችግሮችን ለመፍታት እንደማይረዳ ለደቀ መዛሙርቱ ማስተማሩ ነበር። እያንዳንዱ ቀን የራሱ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉት፤ በመሆኑም ክርስቲያኖች አሁን ያላቸው ጭንቀት እንዳይበቃቸው፣ ስላለፈው ወይም ስለ ወደፊቱ ጊዜ እያሰቡ መጨነቅ አያስፈልጋቸውም። ሆኖም የኢየሱስን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ከከባድ ጭንቀት እፎይታ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?
14. ቀደም ሲል የፈጸምከው ነገር የሚፈጥርብህን ጭንቀት ማስወገድ የምትችለው እንዴት ነው?
14 አንዳንዶች ቀደም ሲል ባደረጉት ነገር ወይም በፈጸሙት ስህተት የተነሳ ይጨነቁ ይሆናል። ከዚህ ቀደም ምናልባትም ከብዙ ዓመታት በፊት በሠሩት ነገር የተነሳ የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። ንጉሥ ዳዊት ‘የፈጸማቸው ስህተቶች በራሱ ላይ እንደሚያንዣብቡ’ የተሰማው ጊዜ ነበር። “በጭንቀት ከተዋጠው ልቤ የተነሳ እጅግ እቃትታለሁ” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 38:3, 4, 8, 18) በዚያ ወቅት ጥበብ የሚሆነው ምን ማድረግ ነበር? ዳዊትስ ምን አድርጓል? ይሖዋ ምሕረት እንደሚያደርግለትና ይቅር እንደሚለው ተማምኗል። ዳዊት “በደሉ ይቅር የተባለለት . . . ሰው ደስተኛ ነው” በማለት በእርግጠኝነት የተናገረው ለዚህ ነበር።—መዝሙር 32:1-3, 5ን አንብብ።
15. (ሀ) አሁን ያለህበት ሁኔታ ሊያስጨንቅህ የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) ጭንቀትን ለመቀነስ የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ? (“ጭንቀትን ለመቀነስ የሚረዱ አንዳንድ ጠቃሚ ዘዴዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
15 ሌሎችን የሚያስጨንቃቸው ደግሞ አሁን ያሉበት ሁኔታ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ዳዊት መዝሙር 55ን በጻፈበት ወቅት ለሕይወቱ ሰግቶ ነበር። (መዝ. 55:2-5) ያም ቢሆን የነበረበት አስጨናቂ ሁኔታ በይሖዋ እንዳይተማመን እንዲያደርገው አልፈቀደም። ዳዊት ስላጋጠመው ችግር አጥብቆ በመጸለይ ብቻ ሳይወሰን የጭንቀቱን መንስኤ ለማስወገድ እርምጃ ወስዷል። (2 ሳሙ. 15:30-34) አንተም ከዳዊት ትምህርት ማግኘት ትችላለህ። ጭንቀት እንዲቆጣጠርህ ከመፍቀድ ይልቅ ችግሩን ለመፍታት የቻልከውን ያህል ጥረት አድርግ፤ ከዚያም ይሖዋ እንደሚረዳህ በመተማመን ጉዳዩን ለእሱ ተወው።
16. የአምላክ ስም ትርጉም በእሱ ላይ ያለህን እምነት የሚያጠናክረው እንዴት ነው?
16 አንድ ክርስቲያን ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን እያሰበ የሚብሰለሰል ከሆነ ሳያስፈልግ ሊጨነቅ ይችላል። ይሁን እንጂ ስለማታውቀው ሁኔታ እያሰብክ በጭንቀት ወይም በስጋት መዋጥ ምንም ፋይዳ የለውም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ፣ የፈራነውን ያህል መጥፎ ነገር ላይደርስ ይችላል። በተጨማሪም የሚያስጨንቅህን ነገር ሁሉ ልትጥልበት ከምትችለው አምላክ ቁጥጥር ውጪ የሆነ ምንም ነገር የለም። ስሙ ራሱ “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም አለው። (ዘፀ. 3:14) የአምላክ ስም እንዲህ ያለ ትልቅ ትርጉም ያዘለ መሆኑ፣ ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ጋር በተያያዘ ዓላማውን ከማሳካት ምንም ነገር እንደማያግደው ማረጋገጫ ይሰጠናል። አምላክ ታማኞቹን እንደሚባርክ ብሎም ከቀድሞ ሕይወታቸው እንዲሁም አሁን ካሉበትና ወደፊት ሊያጋጥማቸው ከሚችለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ የሚሰማቸውን ጭንቀት ለመቋቋም እንደሚረዳቸው እርግጠኛ ሁን።
ጭንቀትህን ለምትቀርበው ሰው አካፍል
17, 18. ስሜትህን ለሌላ ሰው መናገር ጭንቀትን ለመቋቋም የሚረዳህ እንዴት ነው?
17 ጭንቀትን ለማቅለል የሚረዳህ አራተኛው መንገድ ደግሞ ለምትቀርበው ሰው ስሜትህን አውጥተህ መናገር ነው። ለትዳር ጓደኛህ፣ ለቅርብ ወዳጅህ አሊያም ለጉባኤህ ሽማግሌ ስሜትህን መናገርህ ስላለህበት ሁኔታ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖርህ ሊረዳህ ይችላል። “በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።” (ምሳሌ 12:25) ስሜትህን በግልጽና በሐቀኝነት መናገርህ ያለህበትን ሁኔታ ለመረዳትና መፍትሔ ለመፈለግ በእጅጉ ይረዳሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “መመካከር ከሌለ የታቀደው ነገር ሳይሳካ ይቀራል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል” ይላል።—ምሳሌ 15:22
18 ይሖዋ፣ በየሳምንቱ በሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አማካኝነትም አገልጋዮቹ ጭንቀትን መቋቋም እንዲችሉ ይረዳቸዋል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ፣ ስለ አንተ ከሚያስቡና ሊያበረታቱህ ከሚፈልጉ የእምነት ባልንጀሮችህ ጋር መገናኘት ትችላለህ። (ዕብ. 10:24, 25) በዚህ መንገድ ‘እርስ በርስ መበረታታታችሁ’ በመንፈሳዊ የሚያጠነክርህ ከመሆኑም በላይ ያለብህን ማንኛውንም ጭንቀት መቋቋም ቀላል እንዲሆንልህ ያደርጋል።—ሮም 1:12
ከአምላክ ጋር ያለህ ዝምድና —ከሁሉ የላቀ የብርታት ምንጭ
19. ከአምላክ ጋር ያለህ ዝምድና ብርታት እንደሚሰጥህ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው?
19 በካናዳ ያለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ጭንቀቱን በይሖዋ ላይ መጣል ስለሚያስገኘው ጥቅም ምን እንደተማረ እስቲ እንመልከት። መምህርና የተማሪዎች አማካሪ በመሆኑ ሥራው ከፍተኛ ውጥረት ይፈጥርበታል፤ በዚያ ላይ ደግሞ ጭንቀቱ ከሚፈጥርበት የስሜት መቃወስ ጋር ይታገላል። ታዲያ ይህ ወንድም ሁኔታውን መቋቋም የቻለው እንዴት ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና ለማጠናከር ጥረት ማድረጌ፣ ስሜቴ በሚረበሽበት ወቅት ትልቅ ብርታት እንደሚሰጠኝ አስተውያለሁ። እውነተኛ ጓደኞቼና መንፈሳዊ ወንድሞቼ የሚያደርጉልኝ ድጋፍም በጣም ጠቅሞኛል። የሚሰማኝን ነገር ለባለቤቴ ምንም ሳልሸሽግ በሐቀኝነት እነግራታለሁ። አብረውኝ የሚያገለግሉት የጉባኤ ሽማግሌዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ስላለሁበት ሁኔታ ሚዛናዊ አመለካከት እንዳዳብር በጣም ረድተውኛል። በተጨማሪም የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጥረት አደረግኩ፤ እንዲሁም ጊዜዬን በምጠቀምበት መንገድ ላይ ማስተካከያ በማድረግ ዘና የምልበትና ስፖርት የምሠራበት ፕሮግራም አወጣሁ። ውሎ አድሮ ይበልጥ መረጋጋት ቻልኩ። ከቁጥጥሬ ውጭ የሆነ ሁኔታ ካጋጠመኝ ጉዳዩን ለይሖዋ እተወዋለሁ።”
20. (ሀ) ጭንቀታችንን በአምላክ ላይ መጣል የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
20 ለማጠቃለል ያህል፦ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ እንዲሁም የአምላክን ቃል በማንበብና ባነበብነው ላይ በማሰላሰል ጭንቀታችንን በአምላክ ላይ መጣላችን ያለውን ጥቅም በዚህ ርዕስ ላይ ተመልክተናል። ከዚህም ሌላ የአምላክን መንፈስ ፍሬ ማፍራት፣ ስሜታችንን ለምንቀርበው ሰው መናገር እንዲሁም በሚያንጹት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት የሚያስገኘውን ጥቅም አይተናል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ደግሞ ይሖዋ ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማወቃችን እንዴት እንደሚያበረታታን እንመለከታለን።—ዕብ. 11:6