ከአምላክ መጽሐፍ ጋር በሚስማማ መልኩ መደራጀት
“ይሖዋ በጥበብ ምድርን መሠረተ። በማስተዋል ሰማያትን አጸና።”—ምሳሌ 3:19
1, 2. (ሀ) አንዳንዶች ‘አምላክ ድርጅት አለው’ ለሚለው ሐሳብ ምን አመለካከት አላቸው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
አምላክ ድርጅት አለው? አንዳንዶች “አመራር የሚሰጥ ድርጅት አያስፈልግም፤ ከአምላክ ጋር በግለሰብ ደረጃ ወዳጅነት ከመሠረትን በቂ ነው” ይላሉ። ይህ አመለካከት ትክክል ነው? እውነታው ምን ያሳያል?
2 የሥርዓት አምላክ የሆነው ይሖዋ ወደር የማይገኝለት አደራጅ ነው እንድንል የሚያደርገንን ማስረጃ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም ከይሖዋ ድርጅት ለምናገኘው መመሪያ ምን ምላሽ መስጠት እንዳለብን እንማራለን። (1 ቆሮ. 14:33, 40) በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሆነ በዘመናችን፣ የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ምሥራቹን የመስበኩን ሰፊ ሥራ እያከናወነ ያለው ቅዱሳን መጻሕፍት የሚሰጡትን አመራር በመከተል ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ስለምንከተል እንዲሁም ድርጅቱ የሚሰጠንን መመሪያ ተግባራዊ ስለምናደርግ የጉባኤውን ንጽሕና፣ ሰላምና አንድነት ለመጠበቅ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን።
ይሖዋ—ወደር የማይገኝለት አደራጅ
3. ይሖዋ ወደር የሌለው አደራጅ መሆኑን እንድታምን የሚያደርግህ ምንድን ነው?
3 አምላክ ወደር የማይገኝለት አደራጅ መሆኑን የፍጥረት ሥራው ያረጋግጣል። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ በጥበብ ምድርን መሠረተ። በማስተዋል ሰማያትን አጸና” ይላል። (ምሳሌ 3:19) እኛ የምናውቀው የአምላክን ‘መንገድ ዳር ዳር’ ብቻ ነው፤ “ስለ እሱ የሰማነው የሹክሹክታ ያህል ብቻ ነው!” (ኢዮብ 26:14) ስለ ፕላኔቶች፣ ከዋክብትና ጋላክሲዎች ያለን ውስን እውቀት እንኳ አጽናፈ ዓለም አስደናቂ በሆነ መንገድ እንደተደራጀ እንድንገነዘብ ያደርገናል። (መዝ. 8:3, 4) ጋላክሲዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዋክብትን ያቀፉ ሲሆን ሁሉም በሕዋ ውስጥ በተደራጀ መንገድ ይንቀሳቀሳሉ። በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ያሉ ፕላኔቶች፣ የትራፊክ ሕግ አክብረው እንደሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ምሕዋራቸውን ጠብቀው በፀሐይ ዙሪያ ይሽከረከራሉ! በጽንፈ ዓለም ውስጥ የሚታየው አስደናቂ ሥርዓት “ሰማያትን” እና ምድርን ‘በጥበብ የሠራውን’ ይሖዋን ልናወድሰው፣ ታማኝ ልንሆንለት እንዲሁም ልናመልከው እንደሚገባ ያሳያል።—መዝ. 136:1, 5-9
4. ሳይንስ ለበርካታ ጥያቄዎች መልስ ሊሰጥ ያልቻለው ለምንድን ነው?
4 ሳይንስ ስለ ጽንፈ ዓለምና ስለ ምድር ብዙ ነገር ያሳወቀን ከመሆኑም ሌላ በተለያዩ የሕይወታችን ዘርፎች ጥቅም አስገኝቶልናል። ይሁንና ሳይንስ የማይመልሳቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ጽንፈ ዓለም ወደ ሕልውና የመጣው እንዴት እንደሆነ ወይም የሰው ልጆችም ሆኑ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ሕያዋን ፍጥረታት በምድር ላይ ሊኖሩ የቻሉት ለምን እንደሆነ ሊነግሩን አይችሉም። በተጨማሪም የሰው ልጆች ለዘላለም የመኖር ጉጉት እንዲኖራቸው ያደረገው ምን እንደሆነ አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም። (መክ. 3:11) በጣም አስፈላጊ ቢሆኑም መልስ ያላገኙ በርካታ ጥያቄዎች ሊኖሩ የቻሉት ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት፣ ብዙ የሳይንስ ሊቃውንትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ‘አምላክ የለም’ የሚለውን አስተሳሰብና የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ስለሚያራምዱ ነው። ይሖዋ ግን በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ ለሚፈጠሩት ጥያቄዎች በቃሉ ይኸውም እሱ ባስጻፈው መጽሐፍ አማካኝነት መልስ ሰጥቷል።
5. ከተፈጥሮ ሕግጋት ውጭ ሕይወታችንን መምራት አንችልም የምንለው ለምንድን ነው?
5 ይሖዋ ካወጣቸው የማይለዋወጡና አስተማማኝ የተፈጥሮ ሕግጋት ውጭ ሕይወታችንን መምራት አንችልም። የኤሌክትሪክና የቧንቧ ሠራተኞች፣ መሐንዲሶች፣ አውሮፕላን አብራሪዎችና የቀዶ ጥገና ሐኪሞች ሥራቸውን የሚያከናውኑት በተፈጥሮ ሕጎች ተማምነው ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች የሰውነት ክፍሎች የሚገኙበት ቦታ ከሰው ሰው እንደማይለያይ እርግጠኞች ናቸው። በመሆኑም አንድ ሐኪም የሕመምተኛው ልብ የቱ ጋ እንዳለ መፈለግ አይጠበቅበትም። ሁላችንም ብንሆን ለተፈጥሮ ሕጎች መገዛት አለብን። የስበት ሕግን አለመታዘዝ ሕይወታችንን ሊያሳጣን ይችላል!
አምላክ ያደራጃቸው ነገሮች
6. የይሖዋ አገልጋዮች የተደራጁ እንደሚሆኑ መጠበቅ ምክንያታዊ የሚሆነው ለምንድን ነው?
6 ጽንፈ ዓለም የተደራጀው በእርግጥም አስገራሚ በሆነ መንገድ ነው። ከዚህ አንጻር ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ በሚገባ የተደራጁ እንዲሆኑ መፈለጉ የሚያስገርም አይደለም። እንዲያውም ይህን ማድረግ እንድንችል አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። የአምላክ ድርጅት የሚሰጠንን መመሪያዎችና የይሖዋን መሥፈርቶች ችላ ማለት ሕይወታችን ደስታ የራቀውና በመከራ የተሞላ እንዲሆን ያደርጋል።
7. መጽሐፍ ቅዱስ በሚገባ የተደራጀ መጽሐፍ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?
7 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ተያያዥነት የሌላቸው የአይሁድና የክርስትና ቅዱሳን መጻሕፍት ስብስብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሚገባ የተደራጀና በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት እርስ በርስ ተያያዥነት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ድረስ ጭብጡ አንድ ነው፤ ይኸውም ተስፋ በተሰጠበት ‘ዘር’ ማለትም በክርስቶስ በሚመራው የአምላክ መንግሥት አማካኝነት የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክል መሆኑ መረጋገጡና እሱ ለምድር ያለው ዓላማ መፈጸሙ ነው።—ዘፍጥረት 3:15ን፣ ማቴዎስ 6:10ን እና ራእይ 11:15ን አንብብ።
8. እስራኤላውያን በሚገባ የተደራጁ ነበሩ የምንለው ለምንድን ነው?
8 የጥንቶቹ እስራኤላውያን፣ በመደራጀት ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። ለአብነት ያህል፣ በሙሴ ሕግ ሥር “በተደራጀ መልክ [የሚያገለግሉ] ሴት አገልጋዮች” ነበሩ። (ዘፀ. 38:8) እስራኤላውያን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚጓጓዙት ሥርዓታማ በሆነ መንገድ ነበር፤ የማደሪያ ድንኳኑን የሚያጓጉዙትም በተደራጀ መልኩ ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ንጉሥ ዳዊት ሌዋውያኑንና ካህናቱን ሥራቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን በሚያስችል ሁኔታ አደራጅቷቸዋል። (1 ዜና 23:1-6፤ 24:1-3) እስራኤላውያን ይሖዋን ሲታዘዙ አንድነት የሚኖራቸው ከመሆኑም ሌላ አኗኗራቸው ሥርዓትና ሰላም የሰፈነበት ይሆን ነበር።—ዘዳ. 11:26, 27፤ 28:1-14
9. የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ የተደራጀ እንደነበረ የሚያሳየው ምንድን ነው?
9 በአንደኛው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ የተደራጀ ነበር፤ መጀመሪያ ላይ በሐዋርያት የተዋቀረው የበላይ አካል ለጉባኤው አመራር ይሰጥ ነበር። (ሥራ 6:1-6) ከጊዜ በኋላ ተጨማሪ ወንድሞች የበላይ አካሉ አባል ሆኑ። (ሥራ 15:6) ለጉባኤዎች ምክርና መመሪያ የሚተላለፈው በወቅቱ የነበረው የበላይ አካል አባላት አሊያም ከበላይ አካሉ ጋር በቅርበት የሚሠሩ ወንድሞች በሚልኳቸው በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ደብዳቤዎች አማካኝነት ነበር። (1 ጢሞ. 3:1-13፤ ቲቶ 1:5-9) ታዲያ ጉባኤዎች የበላይ አካሉ የሚሰጠውን መመሪያ መታዘዛቸው ምን ጥቅም አስገኝቶ ነበር?
10. የጥንቶቹ ጉባኤዎች የበላይ አካሉን ውሳኔዎች መታዘዛቸው ምን ውጤት አስገኝቷል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
10 የሐዋርያት ሥራ 16:4, 5ን አንብብ። የበላይ አካሉን ወክለው የሚሄዱ ወንድሞች “በኢየሩሳሌም ያሉት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች” ለጉባኤዎች ያሳውቁ ነበር። ጉባኤዎች እነዚህን ውሳኔዎች ሲታዘዙ ደግሞ “በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ” ይሄዱ ነበር። ታዲያ ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ፣ በዛሬው ጊዜ በአምላክ ድርጅት ውስጥ ተግባራዊ ልናደርገው የሚገባ ጠቃሚ ትምህርት እናገኝ ይሆን?
መመሪያዎችን ትከተላላችሁ?
11. የተሾሙ ወንድሞች ከአምላክ ድርጅት መመሪያ ሲሰጣቸው ምን ሊያደርጉ ይገባል?
11 በዘመናችን የቅርንጫፍ ወይም የአገር ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ ሽማግሌዎች ከአምላክ ድርጅት መመሪያ ሲደርሳቸው ምን ሊያደርጉ ይገባል? የአምላክ መጽሐፍ ሁላችንም መታዘዝና መገዛት እንዳለብን ይናገራል። (ዘዳ. 30:16፤ ዕብ. 13:7, 17) ነቃፊነት ወይም የዓመፀኝነት መንፈስ በአምላክ ድርጅት ውስጥ ቦታ የላቸውም፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ዝንባሌ በጉባኤያችን ውስጥ ያለውን ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት ያናጋል። እርግጥ ማንኛውም ታማኝ ክርስቲያን፣ ዲዮጥራጢስ የነበረው ዓይነት መንፈስ ማሳየት አይፈልግም፤ ዲዮጥራጢስ አክብሮትና ታማኝነት የጎደለው ሰው ነበር። (3 ዮሐንስ 9, 10ን አንብብ።) እንግዲያው እንደሚከተለው ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘በዙሪያዬ ያሉትን ሰዎች መንፈሳዊነት ለማጠናከር አስተዋጽኦ አደርጋለሁ? ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የሚሰጡትን መመሪያ ለመቀበልና ለመደገፍ ፈጣን ነኝ?’
12. ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ከሚሾሙበት መንገድ ጋር በተያያዘ ምን ማስተካከያ ተደርጓል?
12 የበላይ አካሉ በቅርቡ ያደረገውን ውሳኔ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በኅዳር 15, 2014 መጠበቂያ ግንብ ላይ ያለው “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ከሚሾሙበት መንገድ ጋር በተያያዘ የተደረገውን ማስተካከያ አብራርቶ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል፣ ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን የመሾሙን ኃላፊነት ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሰጥቶ እንደነበር ርዕሱ ጠቁሟል። ይህን አካሄድ በመከተል ከመስከረም 1, 2014 ጀምሮ ሽማግሌዎችንና አገልጋዮችን የሚሾሙት የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ናቸው። የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ ለሹመት የታጩትን ወንድሞች ይበልጥ ለማወቅና ከተቻለም ከእነሱ ጋር በመስክ አገልግሎት ለመካፈል ጥረት ያደርጋሉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ለሹመት የታጨውን ወንድም ቤተሰብ ሁኔታም ይመለከታል። (1 ጢሞ. 3:4, 5) ከዚያም የሽማግሌዎች አካልና የወረዳ የበላይ ተመልካቹ አንድ ላይ በመሆን፣ የጉባኤ አገልጋዮችና ሽማግሌዎች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን በጥንቃቄ ይመረምራሉ።—1 ጢሞ. 3:1-10, 12, 13፤ 1 ጴጥ. 5:1-3
13. ሽማግሌዎች የሚሰጡንን መመሪያ እንደምንደግፍ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
1 ጢሞ. 6:3 ግርጌ) ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ ሥርዓት በጎደለው መንገድ የሚሄዱ ሰዎችን አስመልክቶ የሰጠውን ምክር እንመልከት። አንዳንድ የጉባኤው አባላት “ሥራ ፈት በመሆን በማይመለከታቸው ጉዳይ ጣልቃ [ይገቡ]” ነበር። በወቅቱ የነበሩት ሽማግሌዎች ለእነዚህ ክርስቲያኖች ምክር ሳይሰጧቸው አልቀሩም፤ ይሁንና እነዚህ ሰዎች ምክሩን ችላ ብለው በድርጊታቸው ቀጥለዋል። ታዲያ ጉባኤው እንዲህ በሚያደርግ ግለሰብ ላይ ምን እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል? ጳውሎስ “ይህን ሰው ምልክት አድርጉበት፤ . . . ከእሱ ጋር አትግጠሙ” ብሏል። ሆኖም ጳውሎስ፣ ግለሰቡን እንደ ጠላት እንዳይመለከቱት አስጠንቅቋቸዋል። (2 ተሰ. 3:11-15) በዛሬው ጊዜም አንድ ሰው የጉባኤውን መልካም ስም የሚያጎድፍ ጎዳና መከተሉን ለማቆም ፈቃደኛ ባይሆን ለምሳሌ ከማያምን ሰው ጋር መጠናናቱን ቢቀጥል፣ ሽማግሌዎች ይህን በተመለከተ ለጉባኤው የማስጠንቀቂያ ንግግር እንዲቀርብ ሊያደርጉ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 7:39) አንተስ ሽማግሌዎች እንዲህ ያለ ንግግር እንዲቀርብ ቢያደርጉ ምን እርምጃ ትወስዳለህ? በንግግሩ ላይ የተጠቀሰውን አካሄድ የሚከተለውን ግለሰብ የምታውቀው ከሆነ ከእሱ ጋር ባለህ ቅርርብ ላይ ገደብ ታበጃለህ? በዚህ መንገድ ፍቅር ማሳየትህና ቁርጥ አቋም መውሰድህ፣ ሥርዓት በጎደለው መንገድ የሚሄደው ሰው አቋሙን እንዲያስተካክል ይረዳው ይሆናል። [1]
13 ሁላችንም ሽማግሌዎች የሚሰጡንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ አለብን። በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያሉት እነዚህ ታማኝ እረኞች የሚከተሉት በአምላክ ቃል ውስጥ የሰፈሩትን “ትክክለኛ” ወይም “ጤናማ” እና “ጠቃሚ” መመሪያዎች ነው። (የጉባኤውን ንጽሕና፣ ሰላምና አንድነት ጠብቁ
14. ለጉባኤው ንጽሕና የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?
14 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መመሪያ በመከተል ለጉባኤው መንፈሳዊ ንጽሕና የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን። በጥንቷ ቆሮንቶስ የነበረውን ሁኔታ እንመልከት። ጳውሎስ በዚህች ከተማ ራሱን ሳይቆጥብ ሰብኳል፤ እንዲሁም በዚያ የሚኖሩትን “ቅዱሳን” ይወዳቸው ነበር። (1 ቆሮ. 1:1, 2) በመሆኑም በዚያ በነበረው ጉባኤ ውስጥ በቸልታ የታለፈውን የፆታ ብልግና አስመልክቶ ሲጽፍ ምንኛ አዝኖ ይሆን! ጳውሎስ፣ ሽማግሌዎቹ የፆታ ብልግና የፈጸመውን ሰው ለሰይጣን አሳልፈው እንዲሰጡት በሌላ አባባል እንዲያስወግዱት መመሪያ ሰጠ። የጉባኤውን ንጽሕና ለመጠበቅ ከፈለጉ በመካከላቸው የነበረውን “እርሾ” ማጽዳት ነበረባቸው። (1 ቆሮ. 5:1, 5-7, 12) እኛም ሽማግሌዎች ንስሐ የማይገባ ኃጢአተኛን ለማስወገድ ያደረጉትን ውሳኔ ስንደግፍ የጉባኤው ንጽሕና እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ እናደርጋለን፤ በተጨማሪም እንዲህ ማድረጋችን ግለሰቡ ንስሐ እንዲገባና የይሖዋን ይቅርታ እንዲፈልግ ያነሳሳው ይሆናል።
15. የጉባኤው ሰላም እንዳይደፈርስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
15 በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ መስተካከል የሚያሻው ሌላም ችግር ነበር። አንዳንድ ወንድሞች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ፍርድ ቤት ያቀርቡ ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ ጉዳዩን ቆም ብለው እንዲያስቡበት ለመርዳት ሲል “እናንተ ራሳችሁ ብትበደሉ አይሻልም?” ሲል ጠይቋቸዋል። (1 ቆሮ. 6:1-8) በዛሬው ጊዜም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟል። አንዳንዶች ከወንድሞቻቸው ጋር የንግድ ስምምነት ካደረጉ በኋላ ገንዘብ ስለከሰሩ ወይም ወንድሞቻቸው እንዳጭበረበሯቸው ስለተሰማቸው በመካከላቸው ያለው ሰላም ደፍርሷል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ወንድሞቻቸውን ፍርድ ቤት ከስሰዋል፤ ይሁንና የአምላክ ቃል፣ የይሖዋን ስም ከማስነቀፍ ወይም የጉባኤውን ሰላም ከማደፍረስ ይልቅ እኛ ብንጎዳ እንደሚሻል ይናገራል። [2] እርግጥ ከበድ ያሉ ችግሮች ወይም አለመግባባቶች ሲያጋጥሙ ኢየሱስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ አለብን። (ማቴዎስ 5:23, 24ን እና 18:15-17ን አንብብ።) እንዲህ ስናደርግ በይሖዋ አገልጋዮች መካከል አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ እናበረክታለን።
16. የአምላክ ሕዝብ አንድነት እንዲኖራቸው መጠበቁ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?
መዝ. 133:1) እስራኤላውያን ይሖዋን እስከታዘዙ ድረስ የተደራጀና አንድነት ያለው ሕዝብ ነበሩ። አምላክ፣ ሕዝቡ ወደፊት የሚኖረውን ሁኔታ አስመልክቶ ሲናገር “በጉረኖ ውስጥ እንዳለ በግ . . . በአንድነት አኖራቸዋለሁ” ብሏል። (ሚክ. 2:12) በተጨማሪም ይሖዋ በነቢዩ ሶፎንያስ በኩል እንዲህ ሲል ተንብዮአል፦ “በዚያን ጊዜ ሰዎች ሁሉ የይሖዋን ስም እንዲጠሩና እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲያገለግሉት [ወይም “በአንድነት እንዲያመልኩት፣” ግርጌ] ቋንቋቸውን ለውጬ ንጹሕ ቋንቋ [የቅዱሳን መጻሕፍትን እውነት] እሰጣቸዋለሁ።” (ሶፎ. 3:9) ይሖዋን በአንድነት የማምለክ መብት በማግኘታችን ምንኛ አመስጋኞች ነን!
16 መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ ሕዝብ አንድነት እንዲኖረው መጠበቃችን ምክንያታዊ የሆነው ለምን እንደሆነ ያሳያል። መዝሙራዊው “እነሆ፣ ወንድሞች በአንድነት አብረው ቢኖሩ ምንኛ መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” ሲል ዘምሯል። (17. አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት በሚፈጸምበት ጊዜ ሽማግሌዎች የጉባኤውን አንድነትና ንጽሕና ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
17 የጉባኤው አንድነትና ንጽሕና እንዲጠበቅ ሽማግሌዎች የፍርድ ጉዳዮችን በአፋጣኝና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ እልባት ሊያገኙላቸው ይገባል። ጳውሎስ፣ አምላክ አፍቃሪ ቢሆንም የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ስሜታዊነት የሚንጸባረቅባቸው እንዳልሆኑ እንዲሁም መጥፎ ተግባርን በቸልታ እንደማያልፍ ተገንዝቦ ነበር። (ምሳሌ 15:3) ጠንከር ያለ ምክር ያዘለውን ሆኖም ፍቅር የሚንጸባረቅበትን የአንደኛ ቆሮንቶስን መልእክት የጻፈው ለዚህ ነው። ከተወሰኑ ወራት በኋላ የተጻፈው የሁለተኛ ቆሮንቶስ ደብዳቤ፣ የጉባኤው ሽማግሌዎች ጳውሎስ የሰጣቸውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረጋቸው ለውጥ እንደታየ ይጠቁማል። አንድ ክርስቲያን፣ ሳያውቅ የተሳሳተ ጎዳና ቢከተል ብቃት ያላቸው ወንድሞች በገርነት መንፈስ ሊያስተካክሉት ይገባል።—ገላ. 6:1
18. (ሀ) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ምክር በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ጉባኤዎችን የጠቀማቸው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን ይብራራል?
18 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ምክር፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የነበሩ ክርስቲያኖች የጉባኤያቸውን ንጽሕና፣ ሰላምና አንድነት ለመጠበቅ እንደረዳቸው ግልጽ ነው። (1 ቆሮ. 1:10፤ ኤፌ. 4:11-13፤ 1 ጴጥ. 3:8) በዚህም ምክንያት በወቅቱ የነበሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአገልግሎት ብዙ ማከናወን ችለዋል። እንዲያውም ጳውሎስ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ ተሰብኳል” በማለት ተናግሯል። (ቆላ. 1:23) ዛሬም ቢሆን አንድነት ያለው የአምላክ ድርጅት አባላት ምሥራቹን ስለሚሰብኩ አስደናቂ የሆነው የአምላክ ዓላማ በምድር ዙሪያ ሊታወቅ ችሏል። የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህ ክርስቲያኖች ለመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡና ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን ለማክበር ቆርጠው እንደተነሱ የሚያሳዩ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ይዟል።—መዝ. 71:15, 16
^ [1] (አንቀጽ 13) የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ ከገጽ 150-151 ተመልከት።
^ [2] (አንቀጽ 15) አንድ ክርስቲያን በእምነት ባልንጀራው ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንዲወስን ሊያደርጉ ስለሚችሉት ሁኔታዎች ለማወቅ ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ ገጽ 223ን እና የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።